👉 “የሴናፍ ዋቁማ በቀይ ካርድ መውጣት ትንሽ ተፅዕኖ ፈጥሮብናል”
👉 “በሚታሰበው ልክ ቡድናችን ሄዷል ብዬ አልናገርም”
👉 “ዳኛዋ እኛን ስሜታዊ እንድንሆን አድርጋናለች”
👉 “በእርግጠኝነት የምናገረው በቀጣይ ቡድናችንን አስተካክለን መጥተን እናሸንፋለን”
በ2024 በሞሮኮ አስተናጋጅነት ለሚደረገው የሴቶች አፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የአንደኛ ዙር ማጣሪያውን ከብሩንዲ አቻው ጋር አድርጎ 1-1 የተለያየው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል ከጨዋታው በኋላ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ተከታዮቹን ምላሾች ሰጥተዋል።
ስለ ጨዋታው…
“ጨዋታው እንደታየው ተመጣጣኝ እግርኳስ የታየበት ነበር። የቁጥር ጎዶሎ ማድረግ እኛን እንደፈለግን እንድንጫወት አላደረገንም። የዳኛን ሕግ እናከብራለን ግን ሴናፍ ዋቁማ በቀይ መውጣትዋ ትንሽ እኛ ላይ ተፅዕኖ ፈጥሮብናል። በጎዶሎ ቢሆንም ጨዋታውን ተቆጣጥሮ መውጣት ግን ትልቅ ነገር ነው ፤ ተጫዋቾቹም ሊመሰገኑ ይገባል። በቀይ የወጣችው ተጫዋችም በዚ ልክ ቀይ ካርድ ትመለከታለች ብዬ እንደ እግር ኳስ ባላምንም የዳኛን ውሳኔ ግን የመቀበል ግዴታ አለብን።”
ከቀይ ካርዱ በኋላ ስለተደረጉ ለውጦች…
“ከዕረፍት በፊት አማራጮች አግኝተናል ፤ የተሻለ ለመንቀሳቀስም ጥረናል። ምንም እንኳ እዚ ቢጫወቱም ዛሬ ባለሜዳ ነበሩ ፤ ለኛ ጥሩ ነው ብዬ ነው የማምነው። አቻ መውጣታችን በቀጣይ ላለብን ጨዋታ ብዙ የምናስብበት ነው። በሚታሰበው ልክ ግን ቡድናችን ሄዷል ብዬ አልናገርም ፤ የሚቀረን ነገር አለ ቀጣይ ደግሞ እናስተካክላለን። ቡድኑን እና ሀገራቸውን ከፍ ለማድረግ ካላቸው ጉጉት አኳያ ይህ ነገር ተፈጥሯል። በቀጣይ ግን በስነልቦና ረገድ ተዘጋጅተን ቡድናችንን አስተካክለን በዕርግጠኝነት ውጤት ይዘን እንወጣለን።”
ስለ ጨዋታ ዕቅዳቸው…
“ይዘን የመጣነው እቅድ በሙሉ ቡድን ሆነን ለመጫወት ነው ፤ ግን አንዳንዴ ከታክቲክ የሚያወጣህ ነገር አለ። ቀይ ካርዱ ለውጥ እንድናደርግ አስገድዶናል። እንደዛም ሆኖ ግን በጎዶሎ ተጫዋች እነሱ የፈጠሩት ነገር የለም እኛ ግን አርባ አምስቱን ደቂቃ እጅግ በተሻለ መንገድ ዕድሎችን አግኝተናል። ያባከነውን ነገርም በቀጣይ አስተካክለን እንመለሳለን።”
ከቀጣይ ጨዋታ ምን እንጠብቅ…
“ከቀጣይ ጨዋታ እርግጠኛ ሆኜ የምናገረው ማሸነፍ እና ማሸነፍ ነው።”
ዝግጅታችሁ በዛሬው ጨዋታ የፈጠረው ተፅዕኖ ይኖር ይሆን…
“ዝግጅት አድርገናል ግን የነበረው ሁኔታ የአየር ሁኔታው ሜዳዎችን እንደፈለግን እንዳንገለገል አድርጎናል።”
የሴናፍ ዋቁማ በቀይ ካርድ መውጣት ስለፈጠረው ተፅዕኖ…
“ቀይ ካርዱ ባይመጣ ኖሮ አሰላለፍ ለመቀየር ነበር ያሰብነው። እነሱ የመጡት ተጠጋግተው ለመጫወት ነው የአምስት ተከላካይ ቅርፅ ይዘው ነው የገቡት ያንን ጨዋታ አንብበነዋል። የኛ ተጫዋቾች ደግሞ 4-3-3 ለመተግበር ነበር ያሰብነው። ያ ነገር ሲቆረጥ አጥቂዎቻችንን ጨምረን 4 ለ 5 አደረግነው። በእግርኳስ ደግሞ የቁጥር ብልጫ ካልወሰድክ በጣም አስቸጋሪ ነው። ስለዚህ የሚከላከሉት በዝተው ስለሆነ እኛ ደግሞ ያንን ቁጥር መጨመር ፈልገን ነበር። የማጥቃት ባሕርይ ያላቸውን ተጫዋቾችን ከመሃል ማስነሳት ነው የፈለግነው። ያ ነገር ባይከሰት ግን ለምሳሌ ንቦኝን ቢጫ ስላለባት ነው እንጂ ደክማ አይደለም። ንቦኝን ሳስወጣ ደግሞ ቢጫ ካርድ አየች እንጂ ከዕረፍት በኋላ መሃል ላይ የተሻለ ነገር ነበር። እሷን ያስወጣሁበት ምክንያት ደግሞ እሷም ቀን ካርድ ልታይ ትችላለች ፤ ያንን ከማሰብ ነው። ዳኛዋም እኛን ስሜታዊ እንድንሆን አድርጋናለች። እግርኳስ ነው መቀበል ግዴታችን ነው። በቀጣይ ግን በእርግጠኝነት መናገር የምችለው ቡድናችንን አስተካክለን መጥተን እንደምናሸንፍ በድጋሚ መናገር እፈልጋለሁ።”