መቻል ሲዳማ ቡናን 1-0 በማሸነፍ የዘንድሮው ሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ አሸናፊ ሆኗል።
በሲዳማ ክልል እግርኳስ ፌድሬሽን እና በጎፈሬ የትጥቅ አምራች ተቋም አማካኝነት ከመስከረም 5 ጀምሮ በሰባት የፕሪምየር ሊግ እና በአንድ ተጋባዥ ክለቦች መካከል ሲደረግ የነበረው የሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ በመቻል አሸናፊነት ተጠናቋል። ከፍፃሜ ጨዋታ አስቀድሞ ሀዋሳ ከተማ ወላይታ ድቻን መደበኛው ደቂቃ 1ለ1 ተጠናቆ በተሰጠ መለያ ምት በማሸነፍ የሦስተኛ ደረጃን ይዞ ሲያጠናቅቅ ምሽቱን ደግሞ በሲዳማ ቡና እና መቻል መካከል የፍፃሜ ጨዋታ ተከናውኖ መቻል በበረከት ደስታ ብቸኛ ግብ የውድድሩ የዋንጫ አሸናፊ ሆኖ አጠናቋል።
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የተለያዩ የሽልማት ሥነ ስርዓቶች ተካሂደዋል። በመርሀግብሩ ላይ ለተሳታፊ ክለቦች ፣ ለውድድሩ መሳካት አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት እና በውድድሩ ላይ በኮከብነት ላጠናቀቁ ሽልማት ተበርክቷል። ምርጥ ተጫዋች ከነዓን ማርክነህ ከመቻል ፣ የውድድሩ ኮከብ ግብ አግቢ ቢኒያም ፍቅሬ በ4 ጎል ከወላይታ ድቻ ፣ ኮከብ ግብ ጠባቂ አሊዮዚ ናፊያዝ ከመቻል እንዲሁም የመቻሉ አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ የውድድሩ ምርጥ አሰልጣኝ ሆነዋል።
በምድብ ጨዋታ የዩጋንዳው ክለብ ኪያንዳ ቦይስ ተጫዋች ከወላይታ ድቻ ተጫዋች ጋር ግጭት ባስተናገደበት ወቅት ሜዳ ላይ የተጫዋቹን ህይወት መመለስ ለቻለው የሲዳማ ቡናው የህክምና ባለሙያ ብሩክ ደበበ ልዩ የዋንጫ እና የ10 ሺህ ብር ሽልማት ተበርክቶለታል። ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ ያጠናቀቀው ሀዋሳ ከተማ የነሀስ ፣ ሲዳማ ቡና የብር እና መቻል የወርቅ ሜዳሊያ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። የውድድሩ የፀባይ ዋንጫ ሽልማት ለወላይታ ድቻ ከተበረከተ በኋላ የውድድሩ አሸናፊ መቻል አሸናፊ የሆነበት ዋንጫ ተበርክቶ ሥነ ስርዓቱ በልዩ ድባብ ተጠናቋል።