ከሲዳማ ቡና ጋር የሙከራ ጊዜ ያሳለፈው ጋናዊው ግብ ጠባቂ ወደ አዲስ አዳጊው ክለብ አምርቷል።
በ2016 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ በታሪክ የመጀመሪያ ተሳትፎውን የሚያደርገው ሀምበሪቾ ዱራሜ ከሌሎች የሊጉ ክለቦች በዘገየ መልኩ በአሰልጣኝ ደጉ ዱባሞ በመመራት በሀዋሳ ከተማ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ሲያከናውን ሰንብቶ ከቀናት በፊት ወደ አዳማ አምርቷል። ከከፍተኛ ሊጉ ማናዬ ፋንቱ ፣ ንጋቱ ጎዴቦ ፣ አፍቅሮት ሰለሞን ፣ አብዱሰላም የሱፍ እና የኋላሸት ፍቃዱን ከፕሪምየር ሊጉ ደግሞ ብሩክ ቃልቦሬ ፣ ፀጋሰው ድማሙ እና አቤል ከበደን ያስፈረመው ቡድኑ አሁን ደግሞ ፊቱን ከሀገር ውጪ በማዞር የጋና ዜግነት ያለውን ግብ ጠባቂ ፓጆ ፓሎምን የግሉ ማድረጉን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።
የእግርኳስ ሕይወቱን ጋና ውስጥ በሚገኙ አካዳሚዎች በይበልጥ ያሳለፈው እና በመቀጠል በጋና 1ኛ ዲቪዚዮን በሚሳተፈው ቱዴ ማይቲ ፣ ተማ ዩዝ እና የመጨረሻ ክለቡ በሆነው ኦኮር ኖኦሚ የተጫወተ ሲሆን ከወራቶች በፊት ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ከሲዳማ ቡና ጋር የሙከራ እና የሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ ላይ ተሳትፎን ካደረገ በኋላ በይፋ ሀምበሪቾን ተቀላቅሏል።
በቀጣዮቹ ቀናትም ተጨማሪ ተጫዋቾችን እንደሚያስፈርም የሚጠበቀው ክለቡ የሊጉ የመጀመሪያ ጨዋታውን የፊታችን ዓርብ መስከረም 25 ድሬዳዋ ከተማን በማስተናገድ የውድድር ጉዞውን ይጀምራል።