የ2016 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ጨዋታ በአዳማ ከተማ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መካከል ተከናውኖ 0-0 ተቋጭቷል።
የ2016 የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመክፈቻ ጨዋታ ከመጀመሩ አስቀድሞ የባህል እና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት እና የፕሪምየር ሊጉ አክሲዮን ማህበር የቦርድ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞን ጨምሮ ሌሎች የክብር እንግዶች ተገኝተው ጨዋታውን አስጀምረዋል።
አዳማ ከተማ በክረምቱ ካስፈረማቸው አዳዲስ ተጫዋቾች አራቱን ፣ ንግድ ባንኮች በበኩላቸው ዘጠኙን በቋሚ አሰላለፋቸው ውስጥ ተጠቅመዋል። የጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ በጥቅሉ ንግድ ባንክ ጫናን በመፍጠሩ አዳማ ደግሞ ጥንቃቄ አዘል ጨዋታን መርጠው ሲንቀሳቀሱ ተመልክተናል። 4ኛው ደቂቃ ላይ በአዳማ የግብ ክልል ጠርዝ ላይ ኳስ በእጅ በመነካቱ ባሲሩ ዑመር በቀጥታ ወደ ጎል መቶ ሰይድ ሀብታሙ የያዛት አጋጣሚ በጨዋታው ቀዳሚዋ ሙከራ ሆናለች። ሜዳውን በመለጠጥ አማካይ ክፍላቸውን ከሁለቱ የመስመር ተጫዋቾች ጋር በማጣመር ቢኒያምን ለመጠቀም ያለመ የጨዋታ ቅርፅን በመያዝ ንግድ ባንኮች ሲጫወቱ ብናስተውልም በሚታይባቸው የአፈፃፀም ድክመት አኳያ የሚያገኞቸውን ዕድል ሲጠቀሙ አልተስተዋለም።
ጥንቃቄ ላይ ትኩረት በማድረግ የእንቅስቃሴ መነሻቸውን ከግብ ጠባቂው ሰይድ ሀብታሙ አድርገው ፣ ለመጫወት ይሞክሩ የነበሩት ባለሜዳዎቹ አዳማዎች ወደ ተጋጣሚ ሦስተኛ የሜዳ ክፍል በተለይ ባመዛኙ በቀኝ በኩል በድግግሞሽ በጀሚል አማካኝነት መድረስ ቢችሉም የመጨረሻ የኳሱ መድረሻ ፍሬያማ አልነበረም። የዕለቱ ዳኛ በላይ ታደሰ ጨዋታውን ሊያገባድዱ ጥቂት ሰከንዶች ብቻ ሲቀሩ ዮሴፍ ታረቀኝ በአዳማ በኩል ያለቀለትን አጋጣሚ ቢያገኝም ከአጨራረስ ድክመት አኳያ ፍሬው ጌታሁን ሳይቸገር ይዞበታል። ከሚንሸራሸሩ ኳሶች ውጪ በሙከራዎች ያልደመቀው አጋማሽ ያለ ጎል ወደ መልበሻ ክፍል አምርቷል።
ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ሲቀጥል ተመጣጣኝ የሜዳ ላይ ፉክክሮችን ያየንበትን ሒደት አስተውናል። ንግድ ባንኮች የመጀመሪያዎቹን 10 ደቂቃዎች በፈጣን ሽግግር በሲሞን ፒተር እና በቢኒያም ጌታቸው አማካኝነት አከታትለው ዕድሎችን ፈጥረዋል። በተለይ ቢኒያም ከመሐል ክፍሉ የደረሰውን ኳስ ወደ ጎል በቀዘቀዘ ምት ወደ መቶ ሰይድ ያወጣበት ጠጣር ያለችዋ ሙከራ ሆናለች። ደቂቃዎች እየገፉ ሲመጡ ከወገብ በላይ ለውጥን ያስፈለጋቸው ንግድ ባንኮች አዲስ ግደይ እና ኪቲካ ጀማን በማስገባት ይበልጥ ከጎል ጋር ራሳቸውን ለማገኘት ታትረዋል።
በአንፃሩ በመስመር በኩል ያመዘነ እንቅስቃሴ ላይ ትኩረት ለማድረግ አሸናፊ ኤልያስ እንዲሁም አብዲሳ ጀማልን ወደ ሜዳ ያስገቡት አዳማዎች አቀራረባቸውን ወደ መስመር አጋድለው ጨዋታቸውን ቀጥለዋል። አሸናፊ ኤልያስ ተቀይሮ እንደገባ በሁለት አጋጣሚዎች ሙከራዎች ፈጥሮ ተስተውሏል። የመጨረሻዎቹን 15 ደቂቃዎች በተሻለ የማጥቃት ቅርፅ ንግድ ባንኮች ለመጫወት ጥረዋል። 76ኛው ደቂቃ ላይ በረከት ግዛቸው ከቢኒያም ያገኘውን በቀጥታ ሞክሮ የወጣበት እና ከሁለት ደቂቃዎች መልስ ራሱ በረከት ከቀኝ ወደ ሳጥን አሻምቶ አዲስ ግደይ በግንባር ገጭቶ የግቡ ቋሚ ብረት መልሶበት። በእንቅስቃሴ ይበለጡ እንጂ የሚያገኟቸውን ኳሶች ከግብ ጋር ለማገናኘት የማይሳሱት አዳማዎች 83 እና 85ኛው ደቂቃ ላይ በፉዓድ እና ሱራፌል አማካኝነት ጠንካራ ሙከራን ቢያደርጉም ፍሬው ጌታሁን በጥሩ ቅልጥፍና አውጥቷቸዋል። ጨዋታው ግብ ሳያስመለክተን 0ለ0 ፍፃሜን አግኝቷል።
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የንግድ ባንኩ አሰልጣኝ በፀሎት ልዑልሰገድ ለማሸነፍ ወደ ሜዳ እንደገቡ ጠቁመው እንደ አዲስ ቡድን መጥፎ እንዳልሆነ እና በጨዋታውም የግብ ዕድልን ፈጥረው ማባከን እንደቻለ ይህም በቀጣይ ሊሻሻል እንደሚገባ በንግግራቸው ገልፀዋል። የአዳማ አቻቸው ይታገሱ እንዳለ በአንፃሩ የመጀመሪያውን አጋማሽ በጥንቃቄ እንደተጫወቱ ፣ በመልሶ ማጥቃትም ለመጫወት እንደጣሩ ተጋጣሚያቸውም ጥሩ ቡድን እንደሆነ ከዕረፍት መልስ ተጭነዋቸው መጫወታቸው ከጠቆሙ በኋላ በቡድናቸው ውስጥ ችግሮች እንዳሉ በቀጣይም እንደሚቀረፉ ተናግረዋል።