‹‹ እራስን ብቁ ለማድረግ ካልጣርክ ለተጨዋቾችህ ታንስባቸዋለህ ›› አሰልጣኝ ውበቱ አባተ

 

አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ኢትዮጵያ በቅርብ ጊዜ ካፈራቻቸው ድንቅ አሰልጣኞች አንዱ ናቸው፡፡ አሰልጣኙ ስላሳለፉት የእግርኳስ ህይወት እና ስለወደፊቱ አላማቸው ለሶከር ኢትዮጵያው ኦምና ታደለ ነግረውታል፡፡ እኛም እናንተ በሚመች መልኩ እንዲህ አቅርበነዋል፡፡

የውበቱ አባተ የእግርኳስ ህይወት በሰዎች ጭንቅላት ውስጥ መታተም የጀመረው ከአዲሱ ሚሌንየም ወዲህ ቢሆንም ግማሽ ደርዘን በሚሆኑ ክለቦች ውስጥ በተጫዋችነት አሳልፈዋል፡፡ በአዳማ ከነማ ፣ ወንጂ ስኳር ፣ ፐልፕ እና ወረቀት ፣ ኪራይ ቤቶች ፣ ጉምሩክ እና አየር መንገድ የተጫወቱት ውበቱ የአባታቸው አሰልጣኝ መሆን እና በልጅነታቸው የመንገድ ላይ እግርኳስ ማዘውተራቸው ኋላ ላይ ተጫዋች እንዲሆኑ መንገድ እንደከፈተላቸው ያምናሉ፡፡

‹‹ እግርኳሰን መጫወት የጀመርኩት በሰፈር ውስጥ ከህጻናት ጓደኞችና የሰፈር ልጆች ጋር ነው፡፡ ከአብዛኛው ታዳጊ የተለየ ስልጠና ወይም አስተዳደግ አልነበረኝም፡፡ ምናልባት ወላጅ አባቴ አሰልጣኝ የነበረ በመሆኑ ከሱ ጋር ወደ ልምምድ ሜዳ በመሄድ ከአዋቂዎች ጋር ያለ እድሜዪ እንድጫወት አልፎ አልፎ እድሉን አገኝ ነበር ፣ በተጨማሪም ጨርቅ ኳስ (በአሮጌ ካልሲ) ሰፍተን ፣ በፓሎኒ ወይም ፕላስቲክ ኳስ በየመንደሩ ትንንሽ ቡድን መስርተን እንጫወት ነበር፡፡ እንደ ቀልድ ለስሜት የተጀመረ የሰፈር ተሞክሮ እያደገ ወደ ተለያዩ ከለቦች እንድገባና ለበርካታ አመታት ለተለያዩ ቡድኖች በመጫወት እንዳሳልፍ የራሱን አስተዋጽኦ አድርጎልኛል፡፡ ››

ውበቱ በአየር መንገድ በ1990ዎቹ አጋማሽ ጫማቸውን ከሰቀሉ በኋላ በቀጥታ ወደ አሰልጣነት ሙያ ተሳቡ፡፡ ነገር ግን በፍጥነት ወደ አሰልጣኝነቱ የተሳቡት ጨዋታ በማቆማቸው ብቻ እንዳልሆነ በልበ ሙሉነት ይናገራሉ፡፡

‹‹ ተጨዋች ሆኜ ባሳለፈኩባቸው ጊዜያቶች ሁሉ ቶሎ የመረዳት ፣ የመጠየቅ ፣ የማስተባበር እና የመሪነት ተግባራት መገለጫዎቼ ነበሩ፡፡ በውስጤ አቅም እንዳለኝ ይሰማኝ ነበር ፣ የአሰልጣኝነት ኮርስ የወሰድኩትም ተጫዋች እያለሁ ነበር፡፡ አሰልጣኝ እንድሆን የረዱኝ ሰዎች በርካቶች ናቸው፡፡ አቶ ገዛኸኝ ለማ እና አቶ ተድላ በላቸው በኔ ውስጥ የተለየ ድርሻ አላቸው። እዚህ ጋር ሊሰመርበት የሚገባው ማንም ሰው አሰልጣኝ እንድትሆን ሊረዳህ ይችላል፡፡ ነገር ግን አፍ ጎበዝ አሰልጣኝ ሊያደርግህ አይችልም፡፡ ሁሉም ነገር ያለው በራስህ እጅ ነው፡፡ የሌሎች ድጋፍ ውጤት የሚኖረው ያንተ የግል ጥረት ከታከለበት ብቻ ነው።

‹‹ እግርኳስ መጫወት እንዳቆምኩ በ1996 ውበት ተስፋ የሚባል የራሴን ቡድን አቋቁሜ ማሰልጠን ጀመርኩ፡፡ ለ2 አመት ወጣቶችን ሰብስቤ በወረዳ ውድድር ላይ እንሳተፍም ነበር፡፡ ከዛ በኋላ በተጓዳኝ የአዳማ ፖሊስን ያለ ምንም ክፍያ ማሰልጠን ጀመርኩ፡፡ ››

የውበቱ የአሰልጣኝነት ህይወት ብሩህ መሆን የጀመረው በፍጥነት ነበር፡፡ በፖሊስ ያሳዩት ተስፋ ሰጪ ውጤት የአዳማ ከነማን ትኩረት ሳበ፡፡በ2000 በፕሪሚየር ሊጉ ታሪክ ከታዩ አስደናቂ ቡድኖች አንዱ ከነበረው አዳማ ከነማ ጀርባ የአሰልጣኝ ውበቱ ድንቅ አመራር ነበር፡፡

ውበቱ በኢትዮጵያ የተለመደው ታሪክ አካል ናቸው፡፡ ውጤታማ ቢሆኑም በአንድ ክለብ ለረጅም ጊዜ መቆየት አልቻሉም፡፡ በአዳማ በአነስተኛ በጀት ድንቅ ቡድን የሰሩት ውበቱ በ2002 ከደደቢት ጋር መልካም አጀማመር ቢያደርጉም ከአንድ የውድድር ዘመን በላይ በሰማያዊዎቹ ቤት አልቆዩም፡፡ በ2003 ኢትዮጵያ ቡናን ተረክበው አደገኞቹን ከ13 አመታት ጥበቃ በኋላ የሃገሪቱን ትልቅ ዋንጫ አስገኝተዋል፡፡ በቀጣዩ የውድድር ዘመን ፍፁም የተዳከመ የውድድር ዘመን ካሳለፉ በኋላ ቡናን ለቀው ወደ ባንክ አመሩ፡፡ ነገር ግን በሃምራዊዎቹ ቤትም አንድ የውድድር ዘመን መጨረስ አልቻሉም፡፡ በአጠቃላይ ከአዲሱ ሚሌንየም ወዲህ ውበቱ 5 ክለቦችን አሰልጥነዋል፡፡ ለአሰልጣኞች ፈተና የሆነው ነገር ምን ይሆን? ውበቱ አጠቃላዩን የእግርኳስ ሲስተም ፣ የክለብ አመራሮችን እና ራሳቸው አሰልጣኞችን በምክንያትነት በማስቀመጥ አስተያየታቸውን ይሰጣሉ፡፡

webetu

‹‹ በሁሉም ክለቦች የገጠሙኝ ችግሮች ተመሳሳይ ናቸው ፣ የማቴሪያል አቅርቦት ፣ የተጨዋች እጥረት ወይም የባጀት ችግር ባለበት ሁኔታ ውስጥ ቡድን ማሰልጠን ሊያስቸግር ይችላል፡፡ ለኔ እነዚህን ችግሮች የወደፊቱን በማየት የማልፋቸው ናቸው፡፡ ለእኔ ትልቁ ችግር የስልጣን ተዋረድ መፋለስ ሲያጋጥም ነው፡፡ ተጨዋቾች ከአንተ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ትተው ከክለብ መሪዎች ጋር ቀጥተኛና አላስፈላጊ ግንኙነት ማድረግ ሲጀምሩ ፣ አለቆችም አሰልጣኙን ዘለው ወደ ታች ከወረዱ ሥራህ ይበላሻል ፣ ያንተም አቅም የኮሰሰ ይሆናል፡፡

‹‹ ስልጠና የ2 ወይም 3 ሰአት ስራ አይደለም፡፡ ጫናው ከፍተኛ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ፣ ልፋት እና ጥረት ይፈልጋል፡፡ በየጊዜው እራስን ብቁ ለማድረግ መጣርና ከጊዜው ጋር አብሮ ለመጓዝ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ አለበለዚያ ተጨዋቾች አንዳንዴ ታንስባቸዋለህ፡፡ ዛሬ ዛሬ በቴክኖሎጂ ምክንያት በርካታ እግርኳስ መደበኛ ስራቸው ያልሆነ ሰዎችም ከበቂ በላይ ግንዛቤ አላቸው፡: ይህን ስታይ ባለሞያው ከሌላውአንድ ደረጃ መቅደም ይገባዋል፡፡ ወደኛ ስትመጣ በርካታ ባለሞያዎች ጥሩ እውቀት ያላቸው ፣ ከጊዜው ጋር ለመራመድ የሚተጉ እንዳሉ አውቃለሁ፡፡ እንደዚህ ያሉ በቁጥርም በጥራትም ማብዛት ለኳሱ እድገት ወሳኝ እንደሆነ አምናለሁ፡፡ ከዚህ በዘለለ አልፎ አልፎም ቢሆን በኮርስ ወቅት ሽርጉድ ብቻ ሰርተፊኬት ለመያዝ የሚደረግ ሩጫ ብዙ ርቀት ያራምዳል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ስልጠና በአቋራጭ የምትሄድበት ስራ አይደለም፡፡ ከውስጥህ ወደኸው ካላዳበርከው ከጊዜው ጋር መራመድ አይደለም መሮጥ ካልቻልክ አስቸጋሪ ነው፡፡

‹‹ የኢትዮጵያ እግርኳስ ችግርን ለመናገር ሰፊ ጥናት ቢያስፈልገውም በርካታ ችግሮችን መዘርዘር ይቻላል:: ትልቁና መሰረታዊ ችግር ሆኖ የሚታየኝ በእቅድ ላይ ተመስርተን መስራት ያለመቻላችን ይመስለኛል:: መፍትሄውም ያለንበትን ተጨባጭ ሁኔታ ከግምት የሚያስገባና ልንደርስበት የምንችለው ግልፅ ግብ ያስቀመጠ እቅድ ማዘጋጀት ለተገባራዊነቱም በትጋት መስራት አንዱ መፍትሄ ነው ብዪ አምናለሁ:፡አለበለዛ በይድረስ ይድረስ መረሀ ግብር ለማሟላት ብቻ የሚደረግ ሩጫ ያልተዘራን ለማጨድ እንደማሰብ ነው፡፡ ›› ሲሉ የአሰልጣኞች ያለመረጋጋት መንስኤዎች እና አጠቃላይ የኢትዮጵያ እግርኳስ ችግር የሚሉትን ያስቀምጣሉ፡፡

ባለፈው የውድድር ዘመን ሰውነት ቢሻው ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝነታቸው መሰናበታቸውን ተከትሎ አዲስ ለተቀጠሩት ማርያኖ ባሬቶ ምክትልነት መመረጣቸው ተወርቶ ነበር፡፡ በጊዘው ዜናውን ቢያስተባብሉም አሁንም ድረስ ውዥንብሩ አለመጥራቱ እንዳስገረማቸው ይናገራሉ፡፡

‹‹ ከተለያዩ ግለሰቦች እና መገናኛ ብዙሃን መመረጤን ብሰማም ማንም ጠርቶ ያነጋገረኝ አካል የለም፡፡ ሱፐር ስፖርት ድረ-ገጽ የፌዴሬሽኑን ፕሬዝደንት ዋቢ አድርጐ መሾሜን ቢዘግብም እውነታው ግን ከዛ ውጪ ነበር፡፡ ለዚህ እኔ መልስ የለኝም ፤ አለመምረጥ መብታቸው ቢሆንም ዜናውን በይፋ ባለማስተባበላቸው ወይም ተገቢውን መረጃ ለህዝብ ባለማሳወቃቸው አሁንም ድረስ ውዥንብር እንደዲፈጠር በር ከፍቷል። ›› ይላሉ፡፡

ውበቱ አሁን የብሄራዊ ቡድን ምክትል አሰልጣኝ ባይሆኑም በቡድኑ ወቅታዊ ሁኔታ እና የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ላይ አስተያየታቸውን ይሰጣሉ፡፡

‹‹ በመጀመሪያ 3 የምድብ ጨዋታዎች ያሰመዘገብነው ውጤት እና የቡድኑ አጠቃላይ እንቅስቃሴ ብዙ የሚያስደስት አልነበረም፡፡ ቡድኑ አንዳንድ ለውጦችን ለማድረግ እየሞከረ በመሆኑ ዋጋ እየከፈለ እንዳለ ይሰማኛል፡፡ ለጊዜው የማሊ የሜዳ ውጪ ጨዋታን ባልተጠበቀ መልኩ ማሸነፋችን ሂሳባዊ ስሌቱን ክፍት አድርጎታል፡፡ ስለዚህ እድሉ አሁንም አለ፡፡በተለይ የአልጄሪያ ጨዋታ ለኛ እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ ያን ማሳካት ከተቻለ በሜዳችን የምናደርገው የማላዊ ጨዋታ በማሽነፍ ማሳካት ይቻላል፡፡››

ውበቱ በአህሊ ሼንዲ በምክትል አሰልጣኝነት ጀምረው አሁን የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ሆነዋል፡፡ ሼንዲ በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ 3ኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን በቀጣይ የውድድር ዘመንም በአፍሪካ ውድድሮች ላይ ይካፈላል፡፡

‹‹ በአንድ አጋጣሚ ኢትዮጵያ ቡናን ይዤ ከሱዳን ብሄራዊ ቡድን ጋር የወዳጅነት ጨዋታ አድርገን ነበር፡፡ በዚሁ ከአንድ በኢትዮጵያ የሚኖር ሱዳናዊ ጋር ተዋወቅን፡: እዚህ ያለኝን ሁኔታ ይከታተል ስለነበር ወደዛ ሄጄ እንድሰራ ሁኔታዎችን አመቻቸልኝ፡፡ በአህሊ ሼንዲበምክትል አሰልጣኝነት እንድሰራም መንገዱ ተከፈተልኝ::

‹‹ ዋና አሰልጣኝ የሆንኩበት አጋጣሚ እጅግ ከባድ ነበር፡፡ ውድድር ለመጨስ 10 ጨዋታ እየቀረን ቢሆንም በሊጉ 3ኛ በመሆን ለማጠናቀቅ ከሌሎች 4 ቡድኖች ጋር ከፍተኛ ትንቅንቅ ማድረግ ይጠበቅብን ነበር፡፡ አሁን ውድድሩ ሊጠናቀቅ 2 ጨዋታ ቢቀረውም 3ኛ ደረጃ መያዛችንን አረጋግጠናል፡፡ በመሆኑም በ2015 ኮንፌደሬሽንስ ዋንጫ ላይ ተካፋይ መሆን ችለናል:: በቀጣይ ከቡድኑ ጋር ስለሚኖረን አጠቃለይ ሁኔታ እየተነጋገርኩ ነው:: ››

ሱዳን ከቅርብ አመታት ወዲህ ለእግርኳስ ከፍተኛ መዋእለ ንዋይ ከሚያፈሱ የምስራቅ አፍሪካ ሃገሮች አንዷ ሆናለች፡፡ ብሄራዊ ቡድኗ በቅርቡ ለአፍሪካ ዋንጫ የተሳተፈ ሲሆን ሁለቱ የኦምዱርማን ክለቦችም በአፍሪካ ከሚጠቀሱ ክለቦች መካከል ናቸው፡፡ ውበቱም የሁለቱ ሃገራት እግርኳስ ለማነፃፀር ትክክለኛው ሰው ይመስላሉ፡፡

‹‹ ሁለቱምሃገራት የሚያመሳስላቸው በርካታ ነገሮች ቢኖሩም እዚህ በርካታ ክለቦች የራሳቸው ሜዳ ያላቸው መሆኑ በተለይ የፋይናንስ አቅማቸው ከፍተኛ መሆኑ ከኢትዮጵያ ይለያቸዋል፡፡ የበርካታ አፍሪካዊ ተጨዋቾች በየቡድኑ መኖርም ልዩነት የሚፈጥር ይመስለኛል፡፡ ››

ውበቱ ለረጅም ጊዜያት በተጫዋችነት እና በአሰልጣኝነት ከበርካታ ተጫዋቾች ጋር ሰርተዋል፡፡ የእሳቸውን አንድ ምርጥ ተጫዋች ምረጡ ቢሏቸው በፍጥነት አንድ ተጫዋች ይጠሩልዎታል፡፡ የቀድሞው አሁን ለሀዋሳ ከነማ እየተጫወተ የሚገኘው ዳንኤል ደርቤ ለውበቱ የምርጥ ችሎታና የመልካም ስብእና ባለቤት ነው፡፡

‹‹ በርካታ ምርጥ ወጣትና ባለ ብዙ ልምድ ባለቤት ተጨዋቾች አብረውኝ አልፈዋል፡፡ ሁሉም ለዛሬ ማንነቴ ጉልህ አስተዋፅኦ በማበርከታቸው ሁሉንም አደንቃለሁ:: ነገር ግን በእስካሁን ቆይታዬ አንድ ተጨዋች መምረጥ ካለብኝ በደደቢት እና በኢትዮጵያ ቡና ያሰለጠንኩት ዳንኤል ደርቤ ለኔ ተመራጭ ነው፡፡ ዳንኤል ስራውን በጣም የሚወድ ፣ ታታሪ ፣ሁሌም ለማሸነፍ የሚተጋ ፣ ራሱን ለማሻሻል የሚጥር ፣ በተጫዋቾች የሚከበር ፣ ትሁት እና ተግባቢ ሲሆን ለቦታው የሚያስፈልገው በርካታ ኳሊቲዎች ባለቤት ከመሆኑ ባሻግር በሜዳ ላይ ያለውን ሁሉ ያለ ስስት የሚሰጥ በመሆኑ ትልቅ ቦታ እሰጠዋለሁ፡፡ ሲሉ ስለ ዳንኤል ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ፡፡ በመጨረሻም ስለወደፊቱ ይናገራሉ፡፡

‹‹ አሰልጣኝነትን በክለብ ደረጃ የጀመርኩት በ1998 ዓ.ም. ነው፡፡ አሁን የደረስኩበትን ደረጃ ስመለከት እጅግ ፈጣን እርምጃ የተራመድኩ ያህል ይሰማኛል፡፡ የወደፊት ህልሜ ብዙ ነው፡፡ ወደፊት አሁን ካለሁበት የተሻለ ደረጃ የመድረስ ምኞቴን አምላክ እንደሚያሳካልኝ ሙሉ እምነቴ ነው፡፡ ››

 

ያጋሩ

Leave a Reply