የ2005 ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ቻምፒዮኖቹ በአዲስ መልክ ተመልሰዋል።
በ1989 ከተመሰረቱ በኋላ ለሀያ ስምንት ዓመታት በተለያዩ ሊጎች ሲሳተፉ የቆዩት ደደቢቶች ላለፉት ዓመታት ተቀማጭነታቸው ወደ መቐለ በመቀየር በትግራይ እግርኳስ ፌደሬሽን ስር ሲወዳደሩ መቆየታቸው ይታወቃል።
ሶከር ኢትዮጵያ ባገኘችው አዲስ መረጃ መሰረት ደግሞ ክለቡ ወደ ቀድሞ መቀመጫው አዲስ አበባ እንደተመለሰ እና ምዝገባውም በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 ማጠናቀቁን አረጋግጠናል። ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ የስፖርት ማሕበራት ማደራጃ ፍቃድ እንደተሰጠውም ለማወቅ ተችሏል።
በተያያዘ ዜናም በ2006 ክለቡ ከምስርታው ጀምሮ ካስተዳደሩት ኮሎኔል ዐወል አብዱራሂም ባለቤትነት ወደ ደራ ትሬዲንግ የተባለ ተቋም ከተዘዋወረ በኋላ ላለፉት ዓመታት በደራ ስር ሲተዳደር ቆይቶ አሁን ወደ ቀድሞ ባለቤቱ ኮሎኔል አወል አብዱራሂም መዞሩ ታውቋል።