👉 “መደበቂያ እንዲሆን አንፈልግም”
👉 “ሁልጊዜ ራሴን ፣ ሙያየን ፣ ተጫዋቾቼን እና ሀገሬን አስከብሬ ነው የምሄደው”
👉 “በግምት የምናገረው በግምት የምሄደው ነገር አይኖረኝም”
👉 “በእኔ መቀጠል አለመቀጠል የሚወስን አካል….”
ለ2024 የዓለም ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ዋንጫ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከኢኳቶርያል ጊኒ ጋር የፊታችን ዓርብ ማላቦ ላይ በሚያደርገው የማጣርያ ጨዋታ ዙርያ የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል በፌዴሬሽኑ መሰብሰቢያ አዳራሽ ቀትር ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። አሰልጣኙ በመግቢያ ንግግራቸው ባለው ጥቂት ቀናት ውስጥ ከዋናው ብሔራዊ ቡድን እንዲሁም አብዛኛውን ከ18 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾችን ጥሪ በማድረግ ዝግጅት መጀመራቸውን አንስተው ሙሉ ትኩረታቸውን ባለው አጭር ጊዜ ውስጥ ቡድኑን ለማዋሃድ ሲሠሩ መቆየታቸውን እና በተጫዋቾቹ ላይ ጥሩ መነሳሳት መኖሩን ተናግረው ስለ ተጋጣሚያቸው ኢኳቶርያል ጊኒ ምንም አይነት መረጃ አለማግኘታቸውን ገልጸው ያም ቢሆኑ ጥሩ ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
በማስከተል በቦታው ከተገኙት መገናኛ ብዙኀን የተለያዩ ጥያቄዎች የቀረቡ ሲሆን በዋናነት በተጠየቁት እና በተሰጡት ምላሾች ዙሪያ ተከታዩን ጽሑፍ አዘጋጅተናል።
ከወቅታዊ ውጤት ማጣት አንጻር ራስህን ከኃላፊነት ታነሳለህ…?
“ይህ ጥያቄ ለመልስ ብዙ ምቹ ነገር ይኖረዋል ብዬ አላምንም። እኔ ባለሙያ ነኝ ከ20 ዓመት በታችም በዋናው ቡድን ውጤታማ መሆኔ ሊዘነጋ አይገባም። የእግርኳስ የመጀመርያ መለኪያም ውጤት ነው። በአራት ዓመት የብሔራዊ ቡድን ቆይታየ ውስጥ ሁለቴ ነው ሽንፈት ያስተናገድኩት። ይሄን የሚመለከቱት ደግሞ የፌዴሬሽን አካላት አሉ ስለዚህ በእኔ መቀጠል አለመቀጠል የሚወስን አካል ስላለ ይሄ ወደ ፊት የሚታይ ይሆናል።”
ስላላቸው የሥራ ነጻነት…?
“የትም ቦታ ላይ የሥራ ነጻነት ሳይኖረኝ አልሠራም። መልካምም የሆኑ መልካምም ያልሆኑ ሀሳቦች ይኖራሉ። በእግርኳስ አሰልጣኝነት ሜዳ ላይ ያለውን እንቅስቃሴ መቆጣጠር ብቻ ሳይሆን ከሜዳ ውጭ ያሉ ነገሮችን በሚገባ ተቆጣጥሮ ማስኬድ ሲቻል ነው። ሀገርን እንደማሰልጠኔ ደግሞ ትልቅ ኃላፊነት በመውሰድ እንደሆነ ሊዘነጋ አይገባም። ስለዚህ ሁልጊዜ ራሴን ሙያዬን ተጫዋቾቼን እና ሀገሬን አስከብሬ የምሄድ መሆኑ እንዲታወቅ እፈልጋለሁ።”
የዝግጅት ጊዜ አናሳ ስለመሆኑ እና ስለተጫዋቾች ድካም…?
“በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ሁለት ነገር ነው ማለት የሚቻለው። አንደኛው ለምሳሌ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ከዚህ ቀደም የነበረው ብሔራዊ ቡድን ይጠራሉ ሠርተው ይሄዳሉ ከዛ ቀጥታ ወደ ክለባቸው ውድድር ነበር የሚሄዱት ይህ ጥሩ የነበረ አካሄድ በመሆኑ አብረው ብዙ ጊዜ የቆዩ ተጫዋቾች በመሆናቸው ውጤታማ ነበርን። ለእንደዚህ ዓይነት ስብስብ ይዞ ከሆነ አስር ቀን ቢሆንም ችግር አልነበረውም። አሁን በቅርቡ በነበረው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ስብስብ ላይ የነበረው የዝግጅት ጊዜ የአስር ቀን ዝግጅት የሚለው ነገር ይቀመጥ እና እነዚህ ተጫዋቾች ከየት ነው የመጡት ሲባል የሴቶች ሊግ ያለቀው በግንቦት ወር ነው። ለአራት ወር አርፈው የመጡ ተጫዋቾች እንዲሁም ኦሎምፒክ ተጫውተው አንድ ወር ያረፉ ተጫዋቾች ስብስብ ነው። በተጨማሪም ከንግድ ባንክ ጋር የሴካፋ ዋንጫን ከመቶ ሃያ ደቂቃ በላይ ተጫውተው የመጡ በርከት ያሉ ተጫዋቾች አሉ። በተጫዋቾቹ ላይ ድካሞች ነበሩ። ይሄን ከሙያ አንጻር መመልከት ተገቢ ነው። በአጠቃላይ ከእነዚህ የተለያዩ ሁኔታዎች ውስጥ የመጡ ተጫዋቾችን አቻችለን ሄደናል። የአፍሪካ ዋንጫ የመግባት ዕቅዳችን ሳይሳካ ቀርቷል። ዞሮ ዞሮ ይህ መደበቂያ እንዲሆን አንፈልግም። መሸነፍ መማርያ ነው ብዬ አምናለሁ። ይሄን ያህል ተበልጠን ከውድድሩ ውጭ የሆንበት ምክንያት የለም። አሁን ከፊት ለፊታችን ስላለው ጨዋታ ስሠራም ሳደራጅም የቆየሁት ለማሸነፍ ነው። በነበሩን ስድስት ቀናት በመስክም ሆነ በክፍል ውስጥ የምናሳያቸው ነገሮች በሙሉ በሰው ሜዳ እንዴት ውጤት ይዞ መምጣት እንደሚቻል ነው ስንሠራ የቆየነው።”
የውል ቆይታቸውን በተመለከተ…?
“በዚህ ጉዳይ አጭር ምላሽ ነው የምሰጠው። ውሌን በተመለከተ የሁለት ወር ቆይታ አለኝ። የምሠራው ሁለቱን ቡድን ነው። በቀጣይ ላሉብኝ ውድድሮች ውሌ በአግባቡ ታድሶ እንደባለሙያ ቀጥዬ ብዙ የምሠራቸው ሥራዎች ይኖራሉ። ከስራ አስፈጻሚው ጋር በዚህ መልኩ ነው ውይይት ያደረኩት። ስለዚህ ውል በሚለው ጉዳይ አንድም ወር ይቅረኝ ሁለት ወር ውል ውል ነው ይሄ እንዲታወቅ እፈልጋለሁ።”
ከፌዴሬሽኑ ድጋፍ እየተደረገ ስለመሆኑ…?
“ይህ የአስተዳደር ጉዳይ በመሆኑ ከእነርሱ ቢመለስ መልካም ነው። ለእግርኳሱ ምን ያስፈልጋል የሚለው የሚታወቅ ስለሆነ ከዚህ በፊት ከፌዴሬሽኑ ጋር ተናበን የሠራናቸው ሥራዎች አሉ ሳይሠሩም የቀሩ ነገሮች አሉ። አሁን ይሄ አልተደረገም ተደረገ የሚለው ሳይሆን የእኔ ዋናው ትኩረት ከፊታችን ያለውን የዓለም ዋንጫ እንዴት ማለፍ እንደሚገባን ማሰብ ነው። አምና ለዓለም ዋንጫ የመጨረሻው ጫፍ ደርሰን ያልተሳካው ለምንድን ነው የሚል እሳቤ ላይ ነን ፤ ምክንያቱም ሀገራችን ውጤት ያስፈልጋታል። ስለዚህ ከዚህ ተነስተን ሌሎች የምስራቅ አፍሪካ ሀገሮች ያሳኩትን የአለም ዋንጫ መግባት እኛም ለማድረግ እየሠራን ነው።”
ስምህ ከተለያዮ ክለቦች ጋር እየተነሳ ስለመሆኑ…?
“እኔ እስካሁን የማውቀው የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ መሆኔን ነው። ስለዚህ የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ነኝ አሁን ላይ ቀጣይ ስላለብኝ የብሔራዊ ቡድን ጨዋታ ነው የማስበው። በግምት የምናገረው በግምት የምሄደው ነገር አይኖረኝም።”