ሻምፒዮኖቹ አራት ተጫዋቾችን ወደ ዋናው ቡድን ቀላቅለዋል።
ሁለት የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫዎችን በተከታታይ ያሳኩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከሃያ ዓመት በታች ቡድናቸው አራት ተጫዋቾችን ወደ ዋናው ቡድን ማሳደጋቸውን አሳውቀዋል።
ወደ ዋናው ቡድን ያደጉት ተጫዋቾች ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ጥሩ እንቅስቃሴ ያደረገው እና ከክቡር አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ውድድር የተገኘው ፈጣኑ አጥቂ ሀሮን አንተር፣ በወዲሁ ብዙ ተስፋ የተጣለበት አማካዩ አቤሰሎም ዘመንፈስ እና በተመሳሳይ በታዳጊ ውድድሮች ጥሩ እንቅስቃሴ ስያደርጉ የነበሩት ተከላካዮቹ ቢኒያም እንዳለ እና አሸናፊ ሞሼ ናቸው። አራቱ ተጫዋቾችም በዛሬው ዕለት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በመገኘት ለሶስት ዓመት የሚያቆያቸውን ፊርማ ማኖራቸውን ክለቡ አስታውቋል፡፡
በክቡር ይድነቃቸው ተሰማ አካዳሚ ዝግጅታቸውን በማድረግ ላይ የሚገኙት ፈረሰኞቹ እሁድ ወልቂጤ ከተማን በመግጠም አዲሱ የውድድር ዘመን ይጀምራሉ።