የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ነገ የሚያስተናግዳቸውን ጨዋታዎች በመንተራስ አራቱ ተጋጣሚዎችን የተመለከቱ መረጃዎችን አሰናድተናል።
ሀዋሳ ከተማ ከ ፋሲል ከነማ
በሊጉ ላይ ከጅምሩ አንስቶ እየተሳተፈ የሚገኘው ሀዋሳ ከተማን ከፋሲል ከነማ የሚያገናኘውን የነገ ጨዋታ እንመለከተዋለን። የተጠናቀቀውን የውድድር ዘመን በፕሪምየር ሊጉ ላይ ሲሳተፍ የወጥነት ችግሮች ይስተዋሉበት የነበረው ሀዋሳ ከተማ በዓመቱ መጨረሻ በሰበሰባቸው 42 ነጥቦች በደረጃ ሰንጠረዡ 7ኛ ላይ በመቀመጥ ማጠናቀቁ ይታወሳል። ቡድኑ በውድድር ዓመቱ በየጨዋታው የወጥነት ችግሮች ይንፀባረቁበት የነበረ ሲሆን በተለይ ጨዋታዎች ወደ መቀመጫ ከተማው ባመራበት ወቅትም የሜዳ ዕድሉን መጠቀም አለመቻሉ በቡድኑ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖዎች እንዲያርፉ ሲያደርግም አስተውለናል። የማሸነፍ እና አቻ ውጤቶቾቹ በንፅፅር በተቀራራቢ ቦታ ላይ በማስቀመጥ ዓመቱን የቋጨ ሲሆን ቡድኑ ለዘንድሮው የውድድር ዘመን ራሱን ለማጠናከር በክረምቱ በርካታ ዝግጅቶችን ሲያደርግ ቆይቷል። ክለቡ በዝውውር ገበያው ከመሳተፉ አስቀድሞ ውላቸው የተጠናቀቀውን አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉን ውል በማራዘም በመቀጠል ደግሞ ባለፈው ዓመት በነበሩበት ክፍተቶች ላይ አልፎም ባጣቸው ተጫዋቾች ምትክ ሊሆኑ የሚችሉትን አዳዲስ ተጫዋቾች ወደ ስብስቡ በማካተት ጉዞውን ጀምሯል። አማኑኤል ጎበና ፣ ፂዮን መርዕድ ፣ ታፈሰ ሰለሞን ፣ እንየው ካሳሁን ፣ ሚሊዮን ሰለሞን እንዲሁም የውጪ ዜጋ ተጫዋች የሆኑትን ቻርለስ ሉክዋንጎ እና ሚካኤል ኦቶውን ከነባሮቹ ጋር በመያዝ ከነሐሴ 12 ጀምሮ የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን ሲሠሩ ሰንብተዋል። ቡድኑ በዝግጅት ወቅት ካደረጋቸው የወዳጅነት ጨዋታዎች በተጨማሪ በሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ ላይ ተሳትፎን ያደረገ ሲሆን በምድብ ጨዋታዎች ወቅት በፈጣን የሽግግር አጨዋወት ተጋጣሚዎቹ ላይ ብልጫን ወስዶ ሲጫወት ያየን ቢሆንም በግማሽ ፍፃሜው መርሐ-ግብር ላይ ግን ለማጥቃትም ሆነ ለመከላከል የነበራቸው የስልነት ችግር ለፍፃሜ ሳያበቃቸው ቀርቷል። ቡድኑ በነገው የፋሲል ጨዋታ በዚህ ውድድር ላይ በማጣሪያ ጨዋታዎች ላይ ያደረገውን እንቅስቃሴ ከደገመ በሜዳ ላይ አንዳች ነገርን ሊፈጥር እንደሚችል ይገመታል።
ባለፈው የውድድር ዓመት ወደ ሊጉ ካደጉ በኋላ ደካማ የሚባል የውድድር ዓመት ያሳለፉት ዐፄዎቹ ዘንድሮ ያደረጓቸው ለውጦች ከወዲሁ ለዋንጫ ከታጩ ቡድኖች ውስጥ እንዲካተቱ አድርጓቸዋል። አምና በአሰልጣኝ ኃይሉ ነጋሽ የኋላ ኋላ ደግሞ በአሸናፊ በቀለ ስር እየተመሩ ዓመቱን ያገባደዱ ሲሆን ክለቡ ከለመደው የውጤት ጉዞ አንፃር መዳከሙን ተከትሎ በመጨረሻዎቹ የሊግ ጨዋታዎች ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር ውላቸው የተጠናቀቁትን የቀድሞው አሰልጣኛቸው ውበቱ አባተን በድጋሚ መልሰው በመቅጠር በርካታ ትልልቅ ዝውውሮችን ፈፅመው ዘንድሮ በሊጉ ከተጠባቂ ክለቦች ዝርዝር ውስጥ ገብተዋል። የ2015 የሊግ ተሳትፏቸውን በደረጃ ሰንጠረዡ 5ኛ ላይ በ43 ነጥቦች ተቀምጠው የፈፀሙት ዐፄዎቹ በቀድሞው አሰልጣኛቸው የዝውውር መስኮቱ ላይ በንቃት ተሳታፊ ነበሩ። እንደ ጌታነህ ከበደ ፣ አማኑኤል ገብረሚካኤል ፣ ኤልያስ ማሞ ፣ እዮብ ማቲያስ ፣ ጋቶች ፓኖም ፣ ዮናታን ፍሰሀ እና ቃልኪዳን ዘላለምን እንዲሁም የውጪ ዜጋ ተጫዋቾችንም ጭምር በማካተት በተጨማሪነትም ረዳት አሰልጣኝ እና የቪዲዮ ተንታኝን ጭምር በመቅጠር ክለቡ በሀዋሳ ዝግጅቱን ለወራት ሲሠራ ቆይቷል። በሀዋሳ ክለቡ በቆየበት ወቅት ካደረጋቸው የአቋም መለኪያ ጨዋታዎች ባሻገር በሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ ላይ ተሳትፎም ነበር። በዚህ ውድድር ላይ ቡድኑ የቅንጅት ችግሮች ፍንትው ብለው ሲንፀባረቁበት የነበረ ቢሆንም ቡድኑ በሒደት በጌታነህ ከበደ በጥልቀት ለመጫወት ሲጥር ግን የተለየ መልክን ተላብሶ ያስተዋልን ሲሆን ምን አልባት በነገው ጨዋታ የነበሩበትን ችግሮች በነበሩት የዝግጅት ቀናት ካስተካከለ በማያጠራጥር መልኩ በርካቶቹ ተጫዋቾች ልምድ ያላቸው ከመሆኑ አንፃር ውጤታማ ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል።
ሀድያ ሆሳዕና ከ መቻል
በዝውውር መስኮቱ በርከት ያሉ ተጫዋቾች አስፈርመው በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ሲሳተፉ የቆዩት ሀድያዎች በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ እስከ ፍፃሜ ድረስ መጓዝ ችለው ተመልክተናል። በአሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ እየተመሩ የ2015 የውድድር ዘመንን ያገባደዱት ሀድያ ሆሳዕናዎች በክለቡ ታሪክ 43 ነጥብ ለመጀመሪያ ጊዜ ተመዝግቦ በ6ኛ ደረጃ ላይ በመቀመጥ ውድድራቸውን ፈፅመዋል። አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌን ባሳለፈው ዓመት የመጨረሻ ሳምንት ላይ በያሬድ ገመቹ በመተካት ለዘንድሮው ዓመት መዘጋጀት የጀመረው ቡድኑ ተጨማሪ ረዳት አሰልጣኞችን በማካተት በዝውውሩ እንደ ምህረተአብ ገብረህይወት ፣ ዳዋ ሆቴሳ ፣ በረከት ወልደዮሐንስ ፣ አስጨናቂ ፀጋዬ ፣ ስንታየው ዋለጬ ፣ ከድር ኩሊባሊ ፣ ታፔ ኤልዛየር እና ከአካባቢው የተመለመሉ ወደ አምስት ተጨማሪ ተጫዋቾችን በክለቡ ካሉ ነባሮች ጋር በማቀናጀት ከነሐሴ 5 በኋላ ባሉት ቀናቶች የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን በክለቡ መቀመጫ ከተማ በማድረግ ጀምረዋል። ቡድኑ በዝግጅቶቹ ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ላይ ተሳትፎን ያደረገ ሲሆን በውድድሩም ላይ ጠንካራ ተፎካካሪ በመሆን ምንም እንኳን የፍፃሜው ጨዋታ መደረግ ባይችልም ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ለዋንጫ ቀርቧል። ካለፉት ዓመታት አንፃር ሻል ያለ ቦታ ላይ ለመቀመጥ አልሞ እየሰራ የሚገኘው ክለቡ ከነገው ጨዋታው በሲቲ ካፑ የነበረው አጨዋወት ከደገመ በሜዳ ላይ ተጋጣሚውን ሊፈትን እንደሚችል ይጠበቃል።
ባለፈው የውድድር ዓመት አስቸጋሪ ጊዜ አሳልፈው እስከ መጨረሻዎቹ ሳምንታት ድረስ ላለመውረድ ለመጫወት የተገደዱት መቻሎች አዲሱን የውድድር ዘመን የጀመሩት ፋሲል ተካልኝን በአዲስ አሰልጣኝ በመተካት ነበር። አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራን በመቅጠር ዝውውሮችን ፈፅመው በሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ ላይ ተሳትፈው የተሳካ ጊዜን በማሳለፍ ውድድሩን በአሸናፊነት አጠናቀዋል። ያለፈውን ዓመት አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝን ቀጥረው በበርካታ ወሳኝ ዝውውሮች ላይ ተሳትፎ የነበራቸው መቻሎች ምንም እንኳን በርካታ ዝውውርን ቢፈፅሙም ከተጠበቀው በታች በሆነ ጎዳና ተጉዘው በመጨረሻም በ40 ነጥቦች 9ኛ ላይ ተቀምጠው ፈፅመዋል። የዘንድሮውን ዓመት ጅምራቸውን አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራን ፣ እንዲሁም ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱን ጨምሮ አዳዲስ ረዳት አሰልጣኞችን ከቪዲዮ ተንታኝ ባለሙያ ጭምር ቀጥረው የአሰልጣኝ ቡድናቸውን አደላድለዋል። በማስከተል እንደ አስቻለው ታመነ ፣ ሽመልስ በቀለ ፣ አቤል ነጋሽ ፣ ያሬድ ከበደ ፣ ሙሀባ አደምን ከውጪ ሀገር ቺጂኦኬ ናምዲ ፣ አሊዮዚ ናፊያን ፣ ስቴፈን ባዱን በመያዝ በክለቡ ያሉ ነባሮችን በማቀናጀት በቢሾፍቱ ከተማ ዝግጅታቸውን ሲከውኑ ከርመው በከተማው ቆይታቸውን የአቋም መለኪያ ጨዋታዎች ላይ ከተሳተፉ በኋላ ወደ ሀዋሳ መጥተው በሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ ላይ ተሳትፈው አመርቂ ስኬት አስመዝግበዋል። በውድድሩ ላይ በማጥቃቱም ሆነ በመከላከሉ ጠጣርነት የሚታይባቸው ሲሆን በተለይ ለማጥቃት ሲያስቡ የሽመልስ በቀለ እና ከነዓን ማርክነህን ጥምረት ተጠቅመው በተጋጣሚ ላይ የበላይ ለመሆን ይጥሩ የነበረበትን ወጥ መንገድ ያስተዋልን ሲሆን ውድድሩንም በአሸናፊነት አጠናቀዋል። ክለቡ በነገው የሊግ የመክፈቻ ጨዋታው ይህንኑ የጨዋታ መንገድ ከደገመ ምን አልባትም ነጥብን ይዞ ሊወጣ እንደሚችል ይጠበቃል።