ነገ በሚከናወኑት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሁለተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዙሪያ ተከታዮቹን መረጃዎች አሰናድተናል።
ሊጉ ነገ በሁለተኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች ሲቀጥል በመክፈቻው ድል ያደረጉት ድሬዳዋ ከተማ እና ኢትዮጵያ ቡና እንዲሁም ድል ያልቀናቸው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ሀድያ ሆሳዕናን የሚያገናኙ ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
ድሬዳዋ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ቡና
አዲስ አዳጊዎቹ ሀምበሪቾ ዱራሜዎችን በገጠሙበት የመጀመርያ ሳምንት ጨዋታ ከኋላ ተነስተው ሁለት ግቦችን አስቆጥረው ሊጉን የጀመሩት ብርቱካናማዎቹ ወደ ካደጉበት ዓመት ጀምሮ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ያላቸውን መጥፎ ክብረ-ወሰን ለማሻሻል እና አጀማመራቸውን ለማሳመር ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ይጠበቃል።
በመጀመርያው ሳምንት ሁለት መልክ የነበረው ጨዋታ ያሳለፉት ድሬዎች በጨዋታው የመጀመርያ አጋማሽ ላይ ከኳስ ውጭ የነበሩባቸው ክፍተቶች በሁለተኛው አጋማሽ መጠነኛ መሻሻል አድርገው ጨዋታውን ማሸነፍ ቢችሉም በነገው ጨዋታ የሚገጥሙት ቡድን ከኳስ ውጭ ከፍ ባለ ጫና የሚጫወት ቡድን እንደመሆኑ መሰል ክፍተቶችን ማስወገድ ይጠበቅባቸዋል። ከዚህ በተጨማሪ በሁለተኛው አጋማሽ የመስመር ተጫዋቾቹን መሰረት ያደረገ የማጥቃት አጨዋወት የተከተሉት አሰልጣኝ አስራት አባት በነገው ጨዋታም በተመሳሳይ ውጤታማ ያደረጋቸውን አጨዋወት ይተገብራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በሀምበሪቾ ፍፁም ብልጫ በተወሰደባቸው አጋማሽ ወደ መሀል ሜዳ ተጠግተው ለመከላከል በሚያደርጉት ጥረት የጨዋታውን መልክ የሚቀይሩ ስህተቶች ሲሰሩ የተስተዋሉት የድሬ ተከላካዮች በነገው ጨዋታ ከተከላካይ ጀርባ የሚፈጠረውን ክፍተት በተሻለ ንቃት መሸፈን ይጠበቅባቸዋል። በተለይም የነገው ተጋጣምያቸው ቡና ፈጣን አጥቂዎች የሚጠቀም ቡድን እንደመሆኑ ፈተናው ቀላል አይሆንላቸውም።
በሊጉ መክፈቻ ጨዋታ ሲዳማ ቡናን አንድ ለባዶ በሆነ ውጤት ረተው ከሦስት ዓመታት በኋላ ሊጉን በድል የጀመሩት ቡናማዎቹ ከሊጉ መክፈቻ ጨዋታ የተለየ አቀራረብ ይኖራቸዋል ተብሎ አይጠበቅም። ሲዳማን ባሸነፉበት ጨዋታ የተለጠጠ እና የቀኝ መስመሩን ዋነኛ የማጥቅያ መሳርያ አድርጎ የሚጫወት ቡድን ያስመለከቱን ሰርብያዊ አሰልጣኝ ኒካላ ካቫዞቪች በነገው ጨዋታም ተመሳሳይ አቀራረብ ይኖራቸዋል ተብሎ ይገመታል።
ድሬዳዋ ከተማ በመጀመርያ ጨዋታ ሁለተኛ አጋማሽ ላይ ኤፍሬም አሻሞ እና ኤልያስ አሕመድ መሰረት ያደረገና ይበልጥ መስመሮችን የሚጠቀም የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ለመተግበር መሞከሩ ይታወሳል። ኢትዮጵያ ቡናም በተመሳሳይ ሲዳማን ባሸነፈበት ጨዋታ ጫላ ተሺታ በተሰለፈበት የቀኝ መስመር ጫና ለመፍጠር ሞክሯል። በሁለቱም ቡድኖች የመጨረሻ ጨዋታ አቀራረብ መሰረት የነገው ጨዋታ ትልቅ የመስመር አጨዋወቶች ፍጥጫ እንደሚያሳየን ይጠበቃል።
በጨዋታው በድሬዳዋ ከተማ በኩል ያሲን ጀማል በጉዳት አይሰለፍም። በሲዳማ ጎፈሬ ዋንጫ ጉዳት አስተናግዶ መጠነኛ ልምምድ የጀመረው ተመስገን ደረስም የመሰለፉ ነገር አጠራጣሪ ሆኗል። በኢትዮጵያ ቡና በኩል በረዥም ጊዜ ጉዳት ላይ ካለው ሮቤል ተክለሚካኤል እና ከሳምንታት በኋላ ወደ ልምምድ ይመለሳል ተብሎ ከሚጠበቀው መሐመድ ኑር ናስር ውጭ ሙሉ ቡድን በሙሉ ጤንነት ይገኛል።
ሁለቱ ክለቦች እስካሁን 22 ጊዜ ሲገናኙ ኢትዮጵያ ቡና 13 ድሬዳዋ ከተማ 4 ድሎችን አስመዝግበው አምስት ጊዜ ነጥብ ተጋርተዋል። በዚህም ኢትዮጵያ ቡና 39 ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ 20 ግቦችን አስቆጥረዋል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ ሀድያ ሆሳዕና
የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ድል ለማግኘት አልመው የሚገቡ ሁለት ቡድኖች የሚያገናኘው ጨዋታ 12:00 ሲል ይጀምራል።
ከዓመታት በኋላ በተመለሱበት ሊግ የመጀመርያ ጨዋታቸውን አካሂደው ባዶ ለባዶ የተለያዩት ንግድ ባንኮች የመጀመርያ ሦስት ነጥብ ለማግኘት ሀድያን ይገጥማሉ። በመጀመርያው ሳምንት ጨዋታ ላይ ጠጣር ሆኖ ከቀረበው አዳማ ከተማ ባደረጉት ጨዋታ በአንፃራዊነት የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ድርሻ ለመውሰድ ያልተቸገሩት ባንኮች ንፁህ የሚባሉ የግብ ዕድሎች በመፍጠር ረገድ ግን ብዙ ክፍተት ተስተውሎባቸዋል። በነገው ጨዋታም በተመሳሳይ በራሱ የግብ ክልል ብዙ ክፍተቶች የማይሰጠው የአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ቡድን እንደመግጠማቸው ተመሳሳይ ፈተና እንደሚጠብቃቸው እሙን ነው። ይህንን ተከትሎም አማካይ ቦታ ላይ በቁጥር በዛ ያሉ ተጫዋቾችን ያማከለ የማጥቃት አጨዋወት የሚከተሉበት ዕድል የሰፋ ይሆናል ተብሎ ይገመታል። የአሰልጣኝ በፀሎት ቡድን በነገው ጨዋታ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ለመውሰድ ይቸገራል ተብሎ ባይገመትም የተጋጣሚን ፈጣን የመልሶ ማጥቃት በመግታት ረገድ ግን ቀላል ፈተና ይገጥመዋል ተብሎ አይጠበቅም።
በመጀመርያው ጨዋታ በመቻል የሦስት ለሁለት ሽንፈት የገጠማቸው ሀድያዎች ተከታታይ ሽንፈት ላለማስተናገድ እና ወደ የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ድል ለማግኘት አልመው ወደ ሜዳ ይገባሉ። በመጀመርያው ጨዋታ ሰመረ ሀፍታይ በተሰለፈበት መስመርና በፈጣን ሽግግሮች ለማጥቃት የሞከሩት ሀድያዎች በተከታታይ ጨዋታ ነጥብ ላለመጣል ከባለፈው ጨዋታ በተሻለ ጥራት አጨዋወቱን ከመተግበር ባለፈ በተመሳሳይ አጨዋወት ይገባሉ ተብሎ ቢጠበቅም በመጀመርያው ጨዋታ ለሽንፈት የዳረጋቸው የመከላከል አደረጃጀት ላይ ለውጥ ማድረጋቸው አይቀሬ ነው። አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ከጨዋታው በኋላ የሰጡት አስተያየትም ቡድኑ በመከላከል አጨዋወቱ ላይ ለውጥ አድርጎ እንደሚመለስ ጠቋሚ ነው። በመጀመርያው ጨዋታ የታየባቸው የጎል ዕድሎች ወደ ግብነት የመቀየር ችግር መቅረፍም ሌላው የቡድኑ የቤት ስራ ይሆናል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች በጉዳትም በቅጣትም የሚያጡት ተጫዋች የለም። በሀድያ በኩል አዲስ ፈራሚው የኋላሸት ሰለሞን በጉዳት ምክንያት አይሰለፍም። ግርማ በቀለ ፣ ስንታየው ዋለጬ እና እንዳለ ደባልቄ ደግሞ ከጉዳት ተመልሰው ቡድናቸውን ያገለግላሉ።
ሁለቱ ክለቦች 2008 ላይ በተገናኙባቸው የሊግ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የ1-0 እና 2-0 ድል ታሪኮችን አስመዝግቧል።