የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አንደኛ ሳምንት ጨዋታዎች ባለፈው ቅዳሜ እና እሁድ ተካሄደዋል፡፡ ሶከር ኢትዮጵያም የሊጉን እውነታዎች ከአንደኛ ሳምንት ጋር በማዛመድ እንዲህ ቃኝታዋለች፡፡
1… ደደቢት ወልድያ ከነማን 6-1 በሆነ ውጤት አሸንፏል፡፡ ይህ ውጤት በመክፈቻ ጨዋታ የተመዘገበ ከፍተኛው ውጤት በመሆን ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በጋራ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡ የፕሪሚር ሊጉ ውድድር በ1990 በአዲስ መልክ በተጀመረበት አመት መብራት ኃይል የአዳማውን ፐልፕ እና ወረቀት 7-1 በሆነ ሰፊ ውጤት ያሸነፈበት ጨዋታ በመጀመርያ ሳምንት የተመዘገበ እስካሁንም ያልተደፈረ ሪኮርድ ነው፡፡ የእሁዱ የደደቢት ድል እና በ1995 ቅዱስ ጊዮርጊስ አዲስ መጪው ሐረር ቢራ (ሐረር ሲቲ)ን 6-1 የረታበት ጨዋታ በሁለተኝነት ተቀምጠዋል፡፡
2..ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ አዳማ ተጉዞ ነጥብ ቢጥልም በመክፈቻ ጨዋታ ያለ መሸነፍ ሪኮርዱን አስጠብቆ ተመልሷል፡፡ በ1991 ሊጉን የተቀላቀለው ቅዱስ ጊዮርጊስ በ17 የውድድር ዘመናት (የዘንድሮውን ጨምሮ) በመክፈቻ ጨዋታዎች 13 ጨዋታዎችን በድል ሲያጠናቅቅ በ4 ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል፡፡
3.. ዘንድሮ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ የተቀላቀሉት አዳማ ከነማ እና ወልድያ የመጀመርያ ጨዋታቸውን ማሸነፍ አልቻሉም፡፡ ያለፉት የውድድር ዘመናት እውነታዎች የሚያሳዩትም የፕሪሚየር ሊጉ የመክፈቻ ጨዋታዎች ለእንግዳ ቡድኖች አለመመቸቱን ነው፡፡ የዘንድሮውን ጨምሮ ከ1991 ጀምሮ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ካደጉ 29 ክለቦች መካከል የመጀመርያ ጨዋታቸውን ያሸነፉ ከለቦች ቁጥር 8 ብቻ ነው፡፡ እነሱም ቅዱስ ጊዮርጊስ (1991) ፣ ሙገር (1991) ፣ ድሬደዋ ምድር ባቡር (1991) ፣ ትራንስ ኢትዮጵያ (1992) ፣ አርባምንጭ ጨጨ (1994) ፣ አየር ኃይል (1998) ፣ ሲዳማ ቡና (2002) እና ወላይታ ድቻ (2006) ናቸው፡፡
4..የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ3 የውድድር ዘመናት በኋላ አጀማመሩን አሳምሯል፡፡ ሃምራዊዎቹ ከ2003 በኋላ ባሉት ሶስት የውድድር ዘመናት የመክፈቻ ጨዋታዎች ከድል ርቀው ቆይተዋል፡፡
5..ኢትዮጵያ ቡና በ1ኛ ሳምንት ፕሮግራም ሽንፈት ሲደርስበት ከ16 አመታት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ነው፡፡ በ1991 ከብሄራዊ ሊግ ባደገው ቅዱስ ጊዮርጊስ 4-1 በሆነ ሰፊ ውጤት የተረቱበት ውጤት ኢትዮጵያ ቡና በመጀመርያ ሳምንት ያስተናገደው ብቸኛ ሽንፈት ነበር፡፡