ሁለተኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ነገ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ይቀጥላል ፤ ጨዋታዎቹን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አዘጋጅተናል።
ሀምበሪቾ ዱራሜ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ
በሊጉ መክፈቻ ጨዋታ የተለያየ ውጤት ያስመዘገቡትን ክለቦች የሚያገናኘው ጨዋታ የዕለቱ ቀዳሚው ጨዋታ ነው።
በታሪካቸው የመጀመርያው የፕሪምየር ሊግ ጨዋታቸው ላይ በድሬዳዋ ከተማ ሽንፈት የገጠማቸው አዲስ አዳጊዎቹ የመጀመርያ የሊግ ነጥብ ለማግኘት ወደ ሜዳ ይገባሉ። ቡድኑ ብርቱካናማዎቹን በገጠመበት ጨዋታ ከፍ ያለ ጫና ፈጥሮ በመጫወት ጥሩ አጀማመር ቢያደርግም ትልቅ የወጥነት ችግር ታይቶበታል። በተለይም በሁለተኛው አጋማሽ የነበረው ዝግ ያለ የጨዋታ ፍጥነት እንደ ትልቅ ክፍተት የሚነሳ ድክመታቸው ነበር። በነገው ጨዋታም ይህንን የወጥነት ችግር እና በተከላካይ መስመር ላይ የታዩባቸው ውስን ክፍተቶች መቅረፍ ይጠበቅባቸዋል። በጨዋታው ጥሩ ተስፋ የታየበት እንቅስቃሴ አድርገው በረከት ወንድሙ በተሰለፈበት የቀኝ መስመር በርካታ ዕድሎች የፈጠሩት አሰልጣኝ ደጉ ዱባሞ የግብ ዕድሎችን የመጠቀም ጥራታቸው ከፍ አድርገው መመለስ ቀዳሚው የቤት ሥራቸው ይሆናል ተብሎ ይገመታል።
ቻምፒዮኖቹ እንደ ባለፈው ዓመት ዘንድሮም በርካታ ግቦች አስቆጥረው ሊጉን ጀምረዋል። በነገው ጨዋታም የድል መንገዳቸውን ለማስቀጠል ወደ ሜዳ ይገባሉ።
ወልቂጤ ላይ አራት ግቦች አስቆጥረው ሊጉን የጀመሩት ፈረሰኞቹ በጨዋታው ሁለተኛ አጋማሽ ላይ ያሳዩት እንቅስቃሴ በውድድር ዓመቱ ሊከተሉት የሚችሉትን የማጥቃት አጨዋወት ፍንጭ የሰጠ ነበር። በአጋማሹም በፈጣን ሽግግር ለመጫወት ሞክረዋል። በነገው ጨዋታም ያንን ውጤታማ ያደረጋቸው አጨዋወት ይተገብራሉ ተብሎ ሲጠበቅ ተጋጣምያቸው በረከት ወንድሙ የመሳሰሉ ፈጣን ተጫዋቾች ያሉበት መስመሩን አብዝቶ የሚጠቀም ቡድን እንደመሆኑ የመስመር ተከላካዮቻቸውን እንቅስቃሴ መገደባቸው አይቀሬ ይመስላል።
በሀምበሪቾ በኩል ቃልአብ ጋሻው በቅጣት አይሰለፍም በተቃራኒው ኤፍሬም ዘካርያስ ከጉዳት ተመልሶ ቡድኑን ያገለግላል ተብሎ ይጠበቃል። በፈረሰኞቹ በኩል ደግሞ ቢንያም በላይ በጉዳት ምክንያት አይሰለፍም። ግብ ጠባቂው ባህሩ ነጋሽ እና አጥቂው ዳግማዊ አርአያም መጠነኛ ልምምድ ቢጀምሩም ለዚህ ጨዋታ የመድረሳቸው ጉዳይ አጠራጣሪ ነው። በተያያዘ ዜና በወረቀት ጉዳዮች የመጀመሪያው ጨዋታ ያልተሰለፈው ሞሰስ አዶ ለጨዋታው ዝግጁ መሆኑ ታውቋል።
ጨዋታውን እያሱ ፈንቴ በመሐል ዳኝነት ፣ ለዓለም ዋሲሁን እና ዘመኑ ሲሳዬነው በረዳትነት ፣ ተካልኝ ለማ ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት ይመሩታል።
ፋሲል ከነማ ከ ኢትዮጵያ መድን
ኢትዮጵያ መድን ወደ ሊጉ በተመለሰበት የአምናው የውድድር ዓመት ሁለት ጊዜ ያለ ግብ የተለያዩት ፋሲል እና መድን ነገ ምሽት ይገናኛሉ።
ከሀዋሳ ከተማ ጋር ነጥብ ተጋርተው ወደ ነገው ወሳኝ ጨዋታ የሚቀርቡት ዐፄዎቹ በተከታታይ ጨዋታዎች ነጥብ ላለመጣል ከበድ ፉክክር ያደርጋሉ።
ሀዋሳን በገጠሙበት ጨዋታ ወደ ግብነት ያልተቀየሩ በርካታ የግብ ዕድሎች የፈጠሩት ፋሲሎች ይህንን ጨዋታ ለማሽነፍ በአጥቂ ክፍላቸው ላይ መጠነኛ መሻሻሎች ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ለወትሮው አስፈሪ የመስመር አጨዋወት የነበራቸው አሰልጣኝ ውበቱ አባተ በባለፈው ጨዋታ በአማኑኤል እና ሽመክት ውጤታማ የማጥቃት አጨዋወት መተግበር አልቻሉም። በነገው ጨዋታም ይህንን ችግራቸው መቅረፍ ይጠበቅባቸዋል።
ሌላው የአሰልጣኝ ውበቱ ትልቅ የቤት ሥራ የተከላካይ መስመሩ ላይ ማስተካከያ ማድረግ ነው። ግልፅ የመከላከል ስህተቶች በተስተዋሉበት የባለፈው ሳምንት ጨዋታ ሦስት ግቦች ለማስተናገድ የተገደዱት ፋሲሎች በነገው ጨዋታ ላይ መሰል ስህተቶት ማስወገድ ይገባቸዋል።
ከባለፈው የውድድር ዓመት አጨዋወታቸው ተመሳሳይ የሚባል አቀራረብ ይዘው ሊጉን የጀመሩት አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ዘንድሮም አስፈሪ የማጥቃት ሽግግር ያለው ቡድን ይዘው ቀርበዋል። የጣና ሞገዶቹን በገጠሙበት ጨዋታ የተጠቀሰው አጨዋወት የተከተሉት መድኖች በነገው ጨዋታም የተለመደው አቀራረብ ይኖራቸዋል ተብሎ ይጠበቃል። ሆኖም በሊጉ መክፈቻ ላይ እንደ ተጋጣምያቸው በተመሳሳይ ለስህተቶች ተጋላጭ የነበረው የመከላከል አደረጃጀታቸው መጠነኛ ማስተካከያ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
ኢትዮጵያ መድኖች በነገው ጨዋታ በጉዳት እና ከወረቀት ጋር በተያያዘ ሦስቱን የውጭ ሀገር ዜግነት ያላቸው ተጫዋቾቻቸውን የማይጠቀሙ ሲሆን በተጨማሪነት የመስመር አጥቂው መሐመድ አበራ እና ግብ ጠባቂያቸው ጆርጅ ደስታም በጉዳት ምክንያት ከነገው ጨዋታ ስብስብ ውጭ መሆናቸው ተረጋግጧል። ዐፄዎቹም በቅርቡ ቡድኑን ከተቀላቀለውና የወረቀት ጉዳዮች ካላጠናቀቀው ተከላካዩ ዥረሚ ፕዮት ውጪ በቅጣትም በጉዳትም የሚያጡት ተጫዋች የለም።
የምሽቱ ጨዋታ አዲሱ የፊፋ ኢንተርናሽናል ዳኛ ኤፍሬም ደበሌ በዋና ዳኝነት ፣ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ሙስጠፋ መኪ እና ሸረፈዲን አልፈኪ በረዳትነት ፣ ተፈሪ አለባቸው ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት ተመድበውበታል።