የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የወቅቱ ቻምፒዮን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሁለት ወሳኝ ተጫዋቾቹን ውል ሲያራዝም የአንድ ተጫዋች ዝውውርን ፈፅሟል።
በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ላይ በተከታታይ ዓመታት ሻምፒዮን በመሆን በአፍሪካ መድረክ እየተሳተፈ የሚገኘው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በቀጣይም በሊጉ ላይ ተፎካካሪነቱን ለማጠናከር ከወራት በፊት ወደ አፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ የሴካፋ ማጣሪያ ውድድር ከማምራቱ በፊት አዳዲስ ተጫዋቾች አስፈርሟል። አሁን ደግሞ ክለቡ የሁለት ወሳኝ ተጫዋቾች ውል ሲራዘም የአንድ አዲስ ተጫዋች ዝውውርን ፈፅሟል።
ውል ካራዘሙት ተጫዋቾች መካከል አንዷ ሎዛ አበራ ሆናለች። እግርኳስን ከሀዋሳ ከተማ ከጀመረች በኋላ በደደቢት በመቀጠል በአዳማ እና በማልታው ቢርኪርካራ መጫወት የቻለችው አጥቂዋ ወደ ሀገር ውስጥ ከተመለሰችም በኋላ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያለፉትን አራት ዓመታት ቆይታለች። በአዲሱ ውሏ መሰረትም ለተጨማሪ ዓመት በንግድ ባንክ ለመቆየት ፊርማዋን አኑራለች።
ሌላኛዋ ውሏን ያደሰችው አንጋፋዋ አማካይ ብርቱካን ገብረክርስቶስ ነች። ለረጅም ዓመታት በደደቢት ፣ ዳሽን ቢራ እና ያለፉትን ተከታታይ ዓመታት ደግሞ በንግድ ባንክ እየተጫወተች የምትገኘው ተጫዋቿ ውሏን ለተጨማሪ ዓመት በክለቡ ማራዘሟ ታውቋል።
ቡድኑ ከሁለቱ ተጫዋቾች በተጨማሪ ለይላ ሸሪፍ የተባለች ግብ ጠባቂን ከንፋስ ስልክ ላፍቶ ወደ ስብስቡ ቀላቅሏል።