በዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር ወልቂጤ ከተማ እና ሲዳማ ቡና በመጨረሻ ደቂቃ ግቦች 1-1 ተለያይተዋል።
በዕለቱ ቀዳሚ ጨዋታ ወልቂጤ ከተማ እና ሲዳማ ቡና ሲገናኙ በመጀመሪያ የሊጉ ጨዋታቸው ሽንፈት ያስተናገዱት ሁለቱም ቡድኖች በዛ ያሉ የቋሚ አሰላለፍ ለውጦችን አድርገዋል። በዚህም መሠረት ወልቂጤ ከተማ ስድስት ሲዳማ ቡና አምስት ለውጦችን ለማድረግ ተገደዋል። ወልቂጤዎች ፋሪስ አለዊን በመሳይ አያኖ ፣ ሙሉዓለም መስፍንን በዳንኤል ደምሱ ፣ ዳንኤል መቀጫን በጌቱ ኃይለማርያም ፣ራምኬል ሎክን በስንታየሁ መንግስቱ ፣ አብርሀም ኃይሌን በበቃሉ ገነነ ፣ አሜ መሐመድን በጋዲሳ መብራቴ ቦታ ተክተው ሲገቡ በአንፃሩ ሲዳማ ቡናዎች ብርሀኑ በቀለ ፣ ሙሉቀን አዲሱ ፣ ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን ፣ ፊሊፕ አጃህ እና ይስሀቅ ካኖን በማስወጣት ደግፌ አለሙ ፣ ማይክል ኪፖሩል ፣ ዮሴፍ ዮሐንስ ፣ አበባየው ዮሐንስ እና እንዳለ ከበደን ተጠቅመዋል።
ቀን 9 ሰዓት ላይ በዋና ዳኛው ተፈሪ አለባቸው ፊሽካ በተጀመረው ጨዋታ ቀዝቃዛ በነበረው የመጀመሪያ አጋማሽ በመጀመሪያዎቹ 20 ደቂቃዎች በተሻለ የኳስ ቁጥጥር ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በቁጥር በዝተው በመግባት የተሻሉ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት ያደረጉት ወልቂጤዎች የመጨረሻ ኳሳቸው ግን ውጤታማ አልነበረም። የጨዋታው የመጀመሪያ ሙከራም 11ኛው ደቂቃ ላይ ሲደረግ የሲዳማ ቡናው አጥቂ ማይክል ኪፖሩል ይዞት በገባው ኳስ ከሳጥኑ የግራ ጠርዝ ላይ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ፋሪስ አለዊ መልሶበታል።
ከራሳቸው የሜዳ ክፍል ተደራጅተው ለመውጣት የተቸገሩት ሲዳማዎች መጠነኛ ማሻሻል እያሳዩ ቢሄዱም 29ኛው ደቂቃ ላይ ግን ግብ ሊያስተናግዱ ተቃርበው ነበር። አሜ መሐመድ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ አቡበከር ሳኒ በግንባሩ ሳያገኘው ቀርቶ የግብ ዕድሉን ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ሠራተኞቹ በኳስ ቁጥጥሩ የነበራቸው ብልጫ እየተቀዛቀዘ ቢመጣም በማጥቃት እንቅስቃሴያቸው በርትተው 39ኛው ደቂቃ ላይም የተሻለ ዕድል ፈጥረው ነበር። ሄኖክ ኢሳያስ ከግራ መስመር ያሻገረው እና ተከላካኖች በትክክል ያላራቁትን ኳስ ያገኘው አምበሉ ሳምሶን ጥላሁን ዒላማውን ባልጠበቀ ሙከራ አባክኖታል።
በሁለቱም በኩል የሚቆራረጡ ቅብብሎች ታጅቦ የቀጠለው ጨዋታ ይበልጥ እየተቀዛቀዘ ሄዶ አጋማሹ ሊጠናቀቅ በተጨመሩ ደቂቃዎች ውስጥ ግን የወልቂጤው ራምኬል ሎክ ከሳጥኑ የግራ ጠርዝ ላይ የተገኘውን የቅጣት ምት በግሩም ሁኔታ ቢመታውም የግቡ አግዳሚ ገጭቶ መልሶበታል። በዚህም አጋማሹ ያለ ግብ ተጠናቋል።
ከዕረፍት መልስ ሲዳማዎች ሀብታሙ ገዛኸኝን በእንዳለ ከበደ ፣ ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃንን በበዛብህ መለዩ እንዲሁም ሙሉቀን አዲሱን በአበባየሁ ዮሐንስ ቀይረው በማስገባት መሃል ሜዳው ላይ የተወሰደባቸውን ብልጫ ማስመለስ ችለዋል። ሆኖም ግን 54ኛው ደቂቃ ላይ ሠራተኞቹ በጥሩ የማጥቃት እንቅስቃሴ በራምኬል ሎክ አማካኝነት ሙከራ ቢያደርጉም ግብ ጠባቂው መክብብ ደገፉ መልሶባቸዋል።
ደቂቃዎች በሄዱ ቁጥር ይበልጥ እየተቀዛቀዘ እና ለተመልካች አሰልቺ እየሆነ በሄደው ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች ለጥቂት ደቂቃዎች እየተፈራረቁ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ቢያደርጉም በወልቂጤ በኩል 70ኛው ደቂቃ ላይ ሄኖክ ኢሳያስ ከቀኝ መስመር ከቅጣት ምት አሻምቶት ኳሱ አቅጣጫ ቀይሮ በግቡ የግራ ቋሚ በኩል ለጥቂት የወጣበት በሲዳማዎች በኩል ደግሞ ማይክል ኪፖሩል ሳጥን ውስጥ መትቶት የወልቂጤው የመሃል ተከላካይ ተስፋዬ መላኩ የመለሰበት ሙከራ ተጠቃሾች ናቸው።
ሆኖም ጨዋታው ሊጠናቀቅ በተጨመሩ አራት ደቂቃዎች ውስጥ ድራማዊ ትዕይንት ታይቶበታል። በቅድሚያም 91ኛው ደቂቃ ላይ ደስታ ዮሐንስ በቀኝ መስመር ከተገኘ የማዕዘን ምት ያሻማውን ኳስ ደስታ ደሙ በግንባሩ በመግጨት አስቆጥሮ ሲዳማን መሪ ቢያደርግም 94ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው ተመስገን በጅሮንድ ከሳጥኑ የግራ ጠርዝ ላይ ድንቅ የቅጣት ምት አስቆጥሮ ጨዋታው አቻ እንዲጠናቀቅ አስችሏል። ለቅጣት ምቱ መገኘትም ምክንያት የነበረው የሲዳማው ሙሉቀን አዲሱ በሁለት ቢጫ ከሜዳ ተወግዷል።