በተጠባቂው ጨዋታ ባህርዳር ከተማ በፍሬው ሰለሞን እና ሀብታሙ ታደሰ ግቦች መቻልን 2-1 ረቷል።
9 ሰዓት ላይ በሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ ባህርዳር ከተማ እና መቻል ሲገናኙ መቻሎች ባለፈው ባስመዘገቡት ድላቸው ላይ የተጠቀሙትን ቋሚ አሰላለፍ ለውጥን ሳያደርጉበት ወደ ሜዳ ገብተዋል። ከመድኑ ሽንፈት አንፃር ባህርዳር ከተማ አላዛር ማርቆስ ፣ ሳዓአምላክ ተገኝ እና አብዱላዚዝ ሲአሆኔን አሳርፈው ፔፕ ሰይዶ ፣ ፍፁም ፍትህአለው እና መሳይ አገኘሁን ለውጠው ለጨዋታው ቀርበዋል።
መጠነኛ ፉክክር እየተደረገበት በተጀመረው ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች በአጫጭር ቅብብሎች ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ተደራጅተው ለመግባት ጥረት አድርገዋል። ሆኖም 11ኛው ደቂቃ ላይ የጣና ሞገዶቹ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ፍሬው ሰለሞን በቀኝ መስመር የተገኘውን የቅጣት ምት ለማሻማት በሚመስል መልኩ ሲያሻግረው ኳሱ አቅጣጫውን ቀይሮ የግብ ጠባቂው አልዌንዚ ናፍያንን ደካማ የጊዜ አጠባበቅ ብቃት ተጨምሮበት መረቡ ላይ አርፏል።
የጣና ሞገዶቹ ከአንድ ደቂቃ በኋላም ከፍ ባለ ሞራል ተጨማሪ ግብ የሚያስቆጥሩበት አጋጣሚ አግኝተው ነበር። ቸርነት ጉግሣ ከግራ መስመር ያሻገረለትን ኳስ ያገኘው ሀብታሙ ታደሰ በግንባሩ ገጭቶ ያደረገው ሙከራ ዒላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል።
ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ትዕግሥት የተሞላበት የማጥቃት እንቅስቃሴ ማድረግ የቀጠሉት መቻሎች 19ኛው ደቂቃ ላይ በምንይሉ ወንድሙ ሳጥን ውስጥ ጥሩ የግብ ዕድል ፈጥረው ተከላካዩ ፍሬዘር ካሳ በድንቅ ቅልጥፍና አስወጥቶበታል። በተለይ በግራ የመከላከል መስመራቸው በፍጹም ፍትሕዓለው ድንቅ ብቃት እንዲሁም በጠንካራ የመከላከል አደረጃጀታቸው ለመቻል የማጥቃት እንቅስቃሴ ፈተና የነበሩት ባህርዳሮች 36ኛው ደቂቃ ላይም የተሻለ የግብ ዕድል መፍጠር ችለው ነበር። ፍሬው ሰለሞን ግብ ካስቆጠረበት የቀኝ መስመር ላይ ተመሳሳይ የቅጣት ምት አግኝቶ ቢያሻግረውም ኳሱን ቸርነት ጉግሣ እና ፍሬዘር ካሳ ሳያገኙት ቀርተው የግብ ዕድሉን ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል።
ደቂቃዎች በሄዱ ቁጥር ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በቁጥር በዝተው መግባት የቀጠሉት መቻሎች 40ኛው ደቂቃ ላይ በአጋማሹ የተሻለውን ለግብ የቀረበ ሙከራቸውን አድርገዋል። ከነዓን ማርክነህ በግራው የሳጥኑ ክፍል ይዞት በገባው ኳስ ጥሩ ሙከራ ቢያደርግም የግቡ አግዳሚ መልሶበታል። ያንኑ ኳስ ሲመለስ ሽመልስ በቀለ ሊጠቀምበት ሲልም የጣና ሞገዶቹ ተከላካዮች ተረባርበው አስወጥተውታል።
ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ተጋግሎ ሲቀጥል በርካታ የግብ ዕድሎችም ተፈጥረዋል። አጋማሹ በተጀመረበት ደቂቃም መቻሎች ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ በማድረግ የባህርዳርን ሳጥን ፈትነው ነበር። ከነዓን ማርክነህ በግሩም ብቃት ተከላካዮችን አታልሎ በማለፍ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ሆኖ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ፔፔ ሰይዶ መልሶበታል።
መቻሎች ኳስ በሚቀባበሉ ሰዓት በሠሩት ስህተት ኳስ ያገኙት ባህርዳሮች 49ኛው ደቂቃ ላይ መሪነታቸውን አጠናክረዋል። ሀብታሙ ታደሰ በጥሩ ዕይታ ለፍጹም ጥላሁን በማቀበል እና ወደ ሳጥን በመሮጥ ኳሱን ተቀብሎት የነበረው ፍጹም ጥላሁን ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ሆኖ ያሻገረለትን ኳስ በተረጋጋ አጨራረስ መረቡ ላይ አሳርፎታል። ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላም በተረጋጋ የማጥቃት እንቅስቃሴ ምላሽ ለመስጠት የሞከሩት መቻሎች 53ኛው ደቂቃ ላይ በምንይሉ ወንድሙ አማካኝነት ከሳጥን ውጪ ጥሩ ሙከራ ቢያደርጉም በግብ ጠባቂው ፔፔ ሰይዶ ተመልሶባቸዋል።
ባህርዳር ከተማዎች መሪነታቸውን ካጠናከሩ በኋላ ወደ ራሳቸው የግብ ክልል በመጠጋት ውጤቱን ለማስጠበቅ ጥረት ሲያደርጉ በአንጻሩ መቻሎች የመጨረሻ ኳሳቸው ውጤታማ አይሁን እንጂ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በተደጋጋሚ መድረስ ችለው ነበር። በዚሁ እንቅስቃሴያቸው 61ኛው ደቂቃ ላይ በረከት ደስታ በቀኙ የሳጥኑ ክፍል ላይ ጥሩ ሙከራ አድርጎ በግቡ አግዳሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል።
በሚያገኙት ኳስ ሁሉ የማጥቃት እንቅስቃሴያቸውን የቀጠሉት መቻሎች 71ኛው ደቂቃ ላይ ተሳክቶላቸው ግብ አስቆጥረዋል። ከነዓን ማርክነህ ከቀኙ የሳጥኑ ጠርዝ ላይ ሆኖ ያሻገረለትን ኳስ ያገኘው ሽመልስ በቀለ በግሩም አጨራረስ መረቡ ላይ አሳርፎታል።
ደቂቃዎች እየገፉ በሄዱ ቁጥር ጨዋታው በኳስ ቁጥጥሩ ጥሩ ፉክክር ቢታይበትም በግብ ሙከራዎች በኩል እየተቀዛቀዘ ሄዷል። ሆኖም ግን በባከኑ ደቂቃዎች ውስጥ 94ኛው እና 96ኛው ደቂቃ ላይ የጣና ሞገዶቹ አጥቂ ሀብታሙ ታደሰ በሁለት አጋጣሚዎች ከግብ ጠባቂ ጋር አንድ ለአንድ ቢገናኝም ቢገናኝም በደካማ አጨራረስ ወርቃዎቹኝ የግብ ዕድሎች አባክኗቸዋል። ጨዋታውም በባህርዳር ከተማ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።