“ወደምንፈልገው ነገር እንመጣለን ፤ አሁን ላይ ግን ቡድኔን በጥሩ ደረጃ ላይ ነው ለማለት ጊዜው ገና ነው” አሰልጣኝ ውበቱ አባተ
“ይሄን ያህል የሚያሰጉ ነገሮች የሉም” አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ
የሦስተኛ ሳምንት የምሽቱ ሁለተኛ ጨዋታ ፋሲል ከነማ የሲዳማ ቡናው ተከላካይ ጊት ጋትኩት በራሱ ላይ ባስቆጠራት ጎል ማሸነፍ ከቻሉት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ አሰልጣኞች ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ ነበራቸው።
አሰልጣኝ ውበቱ አባተ – ፋሲል ከነማ
ስለ ጨዋታው …
“ሁለታችንም ማሸነፍ አልቻልንም ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ላይ አቻ ነው የወጣነው ፣ እነርሱም አጥተው ነው የመጡት ፣ ጠንካራ ጨዋታ እንደሚሆን ገምተን ነበር። ጥብቅ ጨዋታ ነበር ፣ በሁለታችንም በኩል ዕድሎችን ማግኘት ችለናል ከዕረፍት በፊትም ከዕረፍት በኋላም እነርሱን በአግባቡ አለመጠቀም ደግሞ በይበልጥ ሰዓቱ በሄደ ቁጥር መሰላቸት ውስጥ ገብተን እንደነበር ዐይቻለሁ መጨረሻ ግን ሦስት ነጥብ ማሳካት መቻላችን ጥሩ ነው።”
የዛሬው ድል በቀጣይ በቡድኑ ውስጥ ስለሚኖረው ስሜት …
“ማሸነፍ ለቡድንህ የሚሰጠው ስነ ልቦና አለ ፣ የፈለገ ስትንቀሳቀስ ብትውል ማሸነፍ እስካልቻልክ ድረስ በራስህ ላይ ያለህ እምነት ሁልጊዜም ጥርጣሬ ውስጥ ነው የሚቆየው ፣ ስታሸንፍ ለተጫዋቾች የሚሰጠው በራስ መተማመን ትልቅ ነገር ነው። ትልቁ ነገር በተለይ ከመጀመሪያ 15 ደቂቃ በኋላ ጨዋታውን ለመቆጣጠር የሄድንበት መንገድ በይበልጥ በልበ ሙሉነት እንድንጫወት የተሻለ የቡድናችንን ቅርፅ እንድናይ ረድቶናል ብዬ ነው የማስበው ፣ እንዳልከው ግን ማሸነፍ ትልቅ ነገር ነው። ለቀጣይ ጨዋታዎችም የሞራል ስንቅ ይሆነናል።”
ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ቡድኑን በሚፈለገው ልክ ስለማግኘቱ …
“በጣም ገና ነው በፍፁም ፣ እንደዚህም ቢሆን ጥሩ ነው ማለት እንችላለን ግን የምንፈልገው ነገር ላይ ደርሰናል ብዬ ማለት አልችልም። ብዙ ማስተካከል የሚገባን ነገሮች እንዳሉ ነው ከዕለት ዕለት ከእያንዳንዱ ጨዋታ የምናያቸው ነገሮች አሉ ፣ በተለይ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ላይ አራት ጎል ማስተናገድ ለእኛ በጣም ህመም ነው ፣ አራት ጎል አግብተህ አራት ጎል የምታስተናግድ ከሆነ ፍፁም መከላከል ላይ በደንብ ፍተሻ እንደሚያስፈልገው ነው ያየነው ፣ እርሱን ዕለት በዕለት እያስተካከልን የምንሄድ ከሆነ ወደምንፈልገው ነገር እንመጣለን አሁን ላይ ግን ቡድኔን በጥሩ ደረጃ ላይ ነው ለማለት ጊዜው ገና ነው።”
አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ – ሲዳማ ቡና
ስለ ጨዋታው…
“በእውነት ጨዋታው በጣም ጥሩ ነው በመጀመሪያው አጋማሽም ይሁን በሁለተኛው አጋማሽ ፣ ቡድናችን ካለፉት ሁለት ጨዋታዎች በተሻለ ጥሩ እንቅስቃሴ ነበረው። በተለይ አጨራረስ ላይ የምናስተካክላቸው ነገሮች አሉ። በተለይ ቀደም ሲል የነበረው መሐል ሜዳ ላይ የምንበለጣቸው ነገሮች ተስተካክሏል ፣ ጥሩ ነገር አለው ፣ አሁን የበለጠ ደግሞ ፊት ላይ ያለውን መስመር ለማጠናከር ይገዙ እና አጃህ ሲገቡ ይሄ ቡድን የበለጠ ያድጋል። ለዛሬው ጨዋታ ላደረጉት ትግል ሁሉ በጣም ደስ ብሎኛል ተጫዋቾቼን ላመሰግን እፈልጋለሁ።”
ለቀጣይ ጨዋታ ስለሚኖረው የስነ ልቦና ዝግጅት…
“ይሄ ጨዋታ እየተጀመረ ነው። ገና ብዙ የምናገኛቸው ጨዋታዎች አሉ ስለዚህ እነዚህ ነገሮች እየተሻሻሉ የሚመጡ ናቸው ፣ እና ይሄን ያህል የሚያሰጉ ነገሮች የሉም ግን የእኛን የተሻለውን ነገር እያየን ስለሆነ ያንን አግዝፈን እንቀርባለን ብዬ አስባለሁ።”