ሪፖርት | ቀዝቃዛው ጨዋታ አቻ ተጠናቋል

ብዙ የግብ ዕድሎች ያልተፈጠሩበት የሀዋሳ ከተማ እና የድሬዳዋ ከተማ ጨዋታ ያለ ግብ ተጠናቋል።

ምሽት ላይ ሀዋሳ ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ ሲገናኙ ኃይቆቹ ከሻሸመኔ ድላቸው የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ መድኃኔ ብርሃኔን በበረከት ሳሙኤል ፣ ዳዊት ታደሰን በማይክል ኦቱሉ ሲተኩ በኢትዮጵያ ቡና ሽንፈት በገጠማቸው ብርቱካናማዎቹ በኩል በተደረገ ሦስት ቅያሪ ሲያም ሱልጣን ፣ ዳግማዊ ዓባይ እና ካርሎስ ዳምጠው አርፈው አሰጋኸኝ ጴጥሮስ ፣ አቤል አሰበ እና ያሬድ ታደሰ ወደ ሜዳ ገብተዋል።


12፡00 ሲል በዋና ዳኛው ባሪሶ ባላንጎ ፊሽካ በተጀመረው ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ የመጀመሪያ 30 ደቂቃዎች ሀዋሳዎች ከራሳቸው የግብ ክልል ኳስ መስርተው በመውጣት እና ተደራጅተው ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ ሲሞክሩ ድሬዳዋዎች በአንጻሩ በቁጥር በዝተው ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመግባት እና ተጭነው በመጫወት የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት አድርገዋል።

ቀዝቃዛ በነበረው አጋማሽም የመጀመሪያው ለግብ የቀረበ ሙከራ 22ኛው ደቂቃ ላይ ኤፍሬም አሻሞ በሞከረው እና ግብ ጠባቂው ቻርለስ ሉካጎ በመለሰው ኳስ ተደርጓል። ከራሳቸው የግብ ክልል በርካታ ስኬታማ ቅብብሎችን ቢያደርጉም ጠንካራ የማጥቃት እንቅስቃሴ ያልነበራቸው ሀዋሳዎች የተሻለውን የመጀመሪያ የግብ ዕድላቸውን 29ኛው ደቂቃ ላይ ሲፈጥሩ ዓሊ ሱሌይማን ከመሃል በተሻገረለት ኳስ የተጋጣሚ ሳጥን ቢደርስም ከፍ አደርጎ ለማስቆጠር ያደረገውን ሙከራ በጥሩ የጊዜ አጠባበቅ ከሳጥን ወጥቶ የነበረው ዳንኤል ተሾመ በግንባሩ በመግጨት አግዶበታል።

በመጀመሪያው አጋማሽ የመጨረሻ 15 ደቂቃዎች ለኳስ ቁጥጥር ብልጫ ቅድሚያ እየሰጡ የሄዱት ብርቱካናማዎቹ 40ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። አሰጋኸኝ ጴጥሮስ ከቀኝ መስመር ያሻገረለትን ኳስ ያገኘው ቻርለስ ሙሴጌ ተከላካዮችን ሸፍኖ ኳሱን ቢያመቻችም ያደረገው ሙከራ በግቡ አግዳሚ በኩል ወጥቶበት የግብ ዕድሉን ሳይጠቀምበት ቀርቷል።


ከዕረፍት መልስ በሁለቱም በኩል በየ ጥቂት ደቂቃዎች በሚወሰደው የኳስ ቁጥጥር ብልጫ መሃል ሜዳው ላይ የበላይነቱን ለመውሰድ መጠነኛ ፉክክር ቢደረግበትም በሁለቱም በኩል ያሉ የማጥቃት እንቅስቃሴዎች ግን ደካማ ነበሩ። ሆኖም በዚህ ሂደት በቀጠለው ጨዋታ ብርቱካናማዎቹ 68ኛው ደቂቃ ላይ የመጀመሪያውን የተሻለ የግብ ዕድል ሲፈጥሩ ኤልያስ አህመድ ፣ ቻርለስ ሙሴጌ እና ኤፍሬም አሻሞ ተቀባብለው የወሰዱትን ኳስ ኤልያስ ባደረገው ዒላማውን ያልጠበቀ ሙከራ አባክነውታል።


መሃል ሜዳው ላይ የተጫዋች ለውጥ በማድረግ የማጥቃት እንቅስቃሴያቸውን በመጠኑ ለማነቃቃት የሞከሩት ኃይቆቹ የተሻለውን የግብ ዕድላቸውን 78ኛው ደቂቃ ላይ ፈጥረዋል። ዓሊ ሱሌይማን ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ሙጅብ ቃሲም ሳያገኘው ቀርቶ አባክኖታል። ሆኖም ጨዋታው እየተቀዛቀዘ ሄዶ 89ኛው ደቂቃ ላይ በድሬዳዋ በኩል ተቀይሮ የገባው ካርሎስ ዳምጠው በግንባሩ ገጭቶት ግብ ጠባቂው በቀላሉ ከያዘው ኳስ ውጪ ፈታኝ የማጥቃት እንቅስቃሴ ሳይደረግበት ያለ ግብ ተጠናቋል።