የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር ስለተቋረጠው የሊጉ የቀጥታ ስርጭት ጉዳይ ማብራሪያ ሰጥቷል።
በጉዳዩ ዙርያ ማብራሪያ የሰጡት የአክሲዮን ማህበሩ ሥራ አስኪያጅ አቶ ክፍሌ ሰይፈ የዘንድሮው የውድድር ዘመን ከመጀመሩ አስቀድመው ውድድሩን ከሱፐር ስፖርት ሰዎች ጋር ያለፉትን ዓመታት የስርጭት ሂደት መገምገማቸውን አንስተው ዘንድሮም 180 ጨዋታዎችን በቀጥታ ለማስተላለፍ አቅጣጫ ስለመቀመጡ አንስተዋል። አክለውም የዘንድሮ የቀጥታ ስርጭት ላይ እክል ያገጠመውም ከዚህ ቀደም ባለፉት ሦስት ዓመታት የሊጉን ጨዋታዎች የፕሮዳክሽን ሥራ ለመስራት ከሱፐር ስፖርት ጋር ስምምነት የነበረው “ላይቭ አይ” የተሰኘው መቀመጫውን በኬንያ ያደረገው ተቋም በድንገት መቅረቱን ተከትሎ መሆኑን አንስተዋል።
ታድያ ይህ ተቋም በሊጉ ጅማሮ በድንገት መቅረቱን ተከትሎ የነበረውን ክፍተት ለመሙላት የመጀመሪያውን የጨዋታ ሳምንት ከአንድ የሀገር በቀል የሚድያ ተቋም በተገኙ መሳሪያዎች ጨዋታውን ለማስተላለፍ ጥረት ቢደረግም ስርጭቱ ከጥራት ጋር ተያይዞ በቀረበበት ጥያቄ እንዳይቀጥል ሆኗል ያሉ ሲሆን ተቋሙን በዘላቂነት ለመተካት ከሌሎች የሀገር በቀል ተቋማት ጋር ንግግሮች ቢደረጉም ተቋማቱ የጠየቁት ዋጋ እጅግ የተጋነነ መሆኑን ተከትሎ ሱፐር ስፖርቶች ሌሎች አማራጮችን ሲያማትር እንደቆዩ አቶ ክፍሌ ገልፀዋል።
አቶ ክፍሌ በማጠቃለያቸውም ሱፐር ስፖርቶች በአሁኑ ሰዓት በራሳቸው አንድ ሌላ በደቡብ አፍሪካ መቀመጫውን ካደረገ የፕሮዳክሽን ተቋም ጋር ስምምነት የፈፀሙ ሲሆን በቀጣይነት ከስድስተኛ ሳምንት አንስቶ የሊጉ የቀጣይ ስርጭት ዳግም እንደሚጀምር ማረጋገጫ ሰጥተዋል።