ሪፖርት | ሉሲዎቹ በሜዳቸው ነጥብ ተጋርተዋል

በ2024 የኦሊምፒክ ሴቶች እግርኳስ ሁለተኛ ዙር ማጣርያ የመጀመርያ ጨዋታ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ላይ ናይጄሪያን የገጠመው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አንድ አቻ በሆነ ውጤት ጨዋታውን ፈፅሟል።

በስታዲየሙ በጣለው ያልተጠበቀ ዝናብ ታጅቦ በተደረገው የመጀመሪያ አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተመጣጣኝ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴን የተመለከትንበት ነበር።

ካኑ ኡቼና ከሳጥን ውጭ አክርራ በመታችው እና ታሪኳ በርገና ባዳነችው ኳስ በጀመረው ጨዋታ ሉሲዎቹ በመጀመሪያ ሙከራቸው ግን ቀዳሚ መሆን ችለዋል። በ6ኛው ደቂቃ ሉሲዎች ከማዕዘን ያሻሙት ኳስ ብርቄ አማረ ወደ ግብ ስትገጭ በናይጄሪያ ተጫዋቾች ተጨርፋ የጨዋታው የመጀመርያ ግብ ሆና ተመዝግባለች።

በመጀመሪያ 20 ደቂቃዎች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከተከላካይ ጀርባ በሚጣሉ ኳሶች እንዲሁም ናይጄሪያዎች ደግሞ መንዴይ ጊፍት በተሰለፈችበት የግራ መስመር ያጋደለ ማጥቃትን ለመሰንዘር የሞከሩበት ነበር።

ከግቧ መቀጠር በኋላ በተወሰነ መልኩ የተነቃቁ የሚመስሉት የአሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል ልጆች ጨዋታውን ለመቆጣጠር ቢቸገሩም በንፅፅር የተሻሉ የሚባሉ የግብ እድሎችን መፍጠር የቻሉበት አጋማሽ የነበረ ሲሆን በተለይ በ15ኛው ደቂቃ ላይ መሳይ ተመስገን እና በ16ኛው ደቂቃ አርያት አዶንግ ከሳጥን ውጭ ያደረጓቸው ሙከራዎች እጅግ አደገኛ ነበሩ።

ጨዋታው 20 ደቂቃን ከተሻገረ በኃላ የነበረው እንቅስቃሴ የናይጄሪያዎች የበላይነት የታየበት ነበር ፤ በዚህም እንግዶቹ ከቆሙ ኳሶች እና ከመስመር በሚነሱ ተደጋጋሚ ኳሶች ጫና ፈጥረው መጫወት ችለዋል። በተለይም በ28ኛው ደቂቃ ከቀኝ የሳጥኑ ጠርዝ ወደ ውስጥ የደረሳትን ኳስ ተጠቅማ መንዴይ ጊፍት ለጥቂት ሳትጠቀምበት የቀረችው እንዲሁም በ29ኛው ደቂቃ ኢፊ ፒስ ከሳጥን ውጭ ያደረገችው እና ታሪኳ በርገና የያዘችባት ሙከራ እጅግ አደገኞቹ ነበሩ።

ደቂቃዎች እየገፉ በመጡ ቁጥር በብዙ መመዘኛዎች በጨዋታው ሁለተኛ ቡድን እየሆኑ የመጡት ሉሲዎች በ41ኛው ደቂቃ ሎዛ አበራ ከናይጄሪያ ተጫዋቾች ስህተት ከተነጠቀ ኳስ ከረጅም ርቀት ካደረገችው ሙከራ ውጭ ወደ ራሳቸው ሜዳ ተስበው ለመጫወት የተገደዱበት ነበር።

አርያት ኦዶንግ ከሳጥን ውጭ ባደረገችው ሙከራ የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች የሁለተኛ አጋማሽ ጨዋታ ናይጄሪያዎች በ47ኛ ደቂቃ አቻ ለመሆን እጅጉን ቀርበው ነበር ፤ በረጅሙ የተጣለላትን ኳስ ተጠቅማ በግል ጥረት ከታሪኳ በርገና ጋር የተገናቸው ኦሾላ አሲሳት ያደረገቸው ሙከራ ለጥቂት በግቡ ቋሚ በኩል ወደ ውጭ ወጥቶባታል።

አጋማሹን ጫና በመፍጠር የጀመሩት ናይጄሪያዎች በ51ኛ ደቂቃ ግንየአቻነት ግብ አግኝተዋል ፤ የቡድኑ አምበል የሆነችው አጂቤድ ራሺዳት ከሳጥን ውጭ ከግቡ ትይዩ ያገኘውን ኳስ በግሩም ሁኔታ ተቆጣጥራ ወደ ግብ የላከቻት ኳሶ ታሪኳ በርገናን አላልፋ ቡድኗን አቻ አድርጋለች።

ሉሲዎቹ በጨዋታው በተለይ መሃል ሜዳ ላይ የተወሰደባቸውን ብልጫ ለማስተካከል በማሰብ አሰልጣኝ ፍሬው ግብ ባስተናገዱ በደቂቃዎች ልዮነት ተከላካይዋን ቅድስት ዘለቀን በማስገባት ጨዋታውን በመሀል ተከላካይነት ጨዋታውን የጀመረችውን ብርቄ አማረን ወደፊት በመግፋት ከኝቦኘ የን ጋር ከተከላካይ ፊት በማጣመር መጠነኛ የቅርፅ ለውጥ በማድረግ ቀሪ ደቂቃዎችን ለመጫወት ቢጥሩም የማጥቃት ጨዋታቸው በጥድፊያ የተሞላ መሆኑ ለሉሲዎቹ ጨዋታውን አክብዶባቸዋል።

በአንፃሩ ተደጋጋሚ ቅያሬዎች በማድረግ ጨዋታውን አቅልለው ለመጫወት ሲሞክሩ የነበሩት ናይጄሪያዎች የመልሱን ጨዋታ ከግምት ውስጥ በማስገባት ቀሪዎቹን የጨዋታ ደቂቃዎች በሚዛናዊነት ተጫውተዋል።


በአጋማሹ የመጨረሻዎቹ 20 ደቂቃዎች ላይ ሴናፍ ዋቁማ እና አረጋሽ ካልሳን በማስገባት ይበልጥ ማጥቃቱን በአዲስ ጉልበት ለማነቃቃት ጥረት ያደረጉት ሉሲዎቹ ከለውጦቹ በኋላ በተለይ ከግራ እየተነሳች ትጫወት የነበረችው አረጋሽ ካልሳ ለቡድኑ ማጥቃት የተለየ አድማስን ብታላብስም እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ በቁጥር አንሰው ለማጥቃት የሚያደርጉት ጥረት ውጤት ሳያስገኝላቸው ቀርቷል።

ጨዋታው 1ለ1 በሆነ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ ሉሲዎቹ በቀጣይ ከቀናት በኋላ በሚደረገው የመልስ ጨዋታ አዎንታዊ ውጤትን ብቻ ፍለጋ ወደ ናይጄሪያ የሚያቀኑ ይሆናል።