“በእኛ ልጆች ዘንድ እነሱን አግዝፎ የማየት ነገሩ ጫና ፈጥሮብናል” አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል
“በመልሱ ጨዋታ የሚገባንን ውጤት እንደምናሳካ እርግጠኛ ነኝ” አሰልጣኝ ጀስቲን ማዱጉ
በፓሪሱ የ2024 ኦሊምፒክ ማጣሪያ ሁለተኛ ዙር የመጀመሪያ ጨዋታ ኢትዮጵያ ከናይጄሪያ አቻ ከተለያዩበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኃላ ሁለቱ አሰልጣኞች ተከታዩን ሀሳብ ሰጥተዋል።
አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል – ኢትዮጵያ
ስለጨዋታው
“የዛሬው ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች ጫና ውስጥ ሆነው ያደረጉት ጨዋታ ነበር ፤ ሁለታችንም ውጤት እንፈልግበት የነበረ ጨዋታ ነበር። እነሱ ያላቸውን ልምድ ተጠቅመው ውጤት ይዘው መውጣት ችለዋል። ከልምድ ባለፈ ሜዳው ላይ ይህ ነው የሚባል የሰሩት ነገር የለም በእኛ በኩል በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ እርማቶችን አድርገን የተሻለ ነገር ለመፍጠር ሞክረናል።እነሱ ልምዳቸውን ሲጠቀሙ የእኛ ልጆች ግን በችኮላ ውስጥ ነበሩ እንጂ የተሻለ ነገር ማድረግ እንችል ነበር።”
ስለጨዋታ ዕቅዳቸው
“በሃሳብ ደረጃ ተዘጋጅተን የነበረው ኳሱን ተቆጣጥረን ብንጫወት የተሻለ ነገር ማግኘት እንደምንችል ነበር።እነሱ በተክለ ሰውነት ግዙፍ ስለሆነ ለእኛ የተሻለው የሚሆነው አማራጭ እኛ ከምንሮጥ ኳሱን ብናሮጠው የተሻለ እንደሚሆን አስበን ነበር።ነገርግን በጨዋታው የእኛ ልጆች ከኳሱ ይልቅ ራሳቸው ብዙ ስለሮጡ ከፍተኛ ጉልበት እንድናወጣ ሆኗል።ለመልሶ ጨዋታ ከዛሬው ሂደት በመነሳት የተለየ ዕቅድ እናዘጋጀለን ነገር ግን በዛሬው ጨዋታ በተለይ በእኛ ልጆች ዘንድ እነሱን አግዝፎ የማየት ነገሩ ጫና ፈጥሮብናል።”
ስለብርቄ የሚና ለውጥ እና የአረጋሽ ካልሳ በተጠባባቂነት መጀመር
“ብርቄን በሁለተኛው አጋማሽ ከኝቦኝ ጋር ያጣመርንበት ምክንያት ብዙ ተሻጋሪ ኳሶች ይጣሉ ስለነበር በዚህ ረገድ እሷ ከማዕድን የተሻለች ስለሆነች በዚያ አግባብ ከግቡ በኃላ ለመጠቀም ሞክረናል የተሻለም ውጤት አስገኝቶልናል።በተፈጥሮ አርያት እና ረድኤት ፈጣኖች ናቸው ከዚህ መነሻነት ጨዋታውን በፈጣን ሯጮች በመጀመር በኃላ ላይ ደግሞ በኳስ የሚያደክሙ ልጆች ለመጠቀም በማሰብ የተደረገ ውሳኔ ነው።”
አሰልጣኝ ጀስቲን ማዱጉ – ናይጄሪያ
ስለጨዋታው
“ሁላችሁም እንደተመለከታችሁት ጥሩ ጨዋታ ነበር። ለእኛ ቀላል ጨዋታ አልነበረም ፤ ኢትዮጵያዎች በሚችሉት ሁሉ ከጨዋታው ውጤት ይዘው ለመውጣት ጥረዋል።ከገጠመን ጠንካራ ፈተና አንፃር የቻልነውን ሁሉ ጥረት አድርገናል ፤ ምንም እንኳን ለማሸነፍ ብንመጣም በመጨረሻም አቻ ለመውጣት ተገደናል።ምንም እንኳን በዛሬው ጨዋታ ችግሮች የነበሩብን ቢሆንም ከመልሶ ጨዋታ በፊት አርመን እንቀርባለን።”
በጨዋታው ስለነበራቸው አቀራረብ
“አጥቀን ለመጫወት እና ለማሸነፍ ነበር የመጣነው ነገርግን በተለይ በማጥቃት ወረዳ ውስጥ የነበረን የኳሶች አቅርቦት ፍፁም ደካማ ነበር።ከዚህ አንፃር ከመልሶ ጨዋታ አስቀድመን ይህን ክፍተት ማረም ይኖርብናል።በሁለተኛው አጋማሽ ያደርግናቸው ቅያሬዎች ይበልጥ ጫና እንድናሳድር ረድተውናል ነገርግን የመጨረሻ ኳሶቻችን ጥራት ደካማ መሆን የፈለግነው እንዳናደርግ አግዶናል።”
ስለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከጨዋታው በፊት ስለነበራቸው ግምት
“እንደማንኛውም ጨዋታ ለማሸነፍ አቅደን ነበር የመጣነው ይህ ማለት ግን ሁሌ ታሸንፋለህ ማለት አይደለም። ያቀድነው ባለመሳካቱ ደስተኞች አይደለንም ነገርግን በመልሱ ጨዋታ የሚገባንን ውጤት እንደምናሳካ እርግጠኛ ነኝ።”