ሪፖርት | ሀዋሳ እና መድን ነጥብ ተጋርተዋል

የሀዋሳ ከተማ እና የኢትዮጵያ መድን ጨዋታ ቀዝቃዛ ፉክክር ተደርጎበት 0-0 ተጠናቋል።

በዕለቱ ቀዳሚ መርሐ-ግብር ሀዋሳ ከተማ እና ኢትዮጵያ መድን ሲገናኙ ሀዋሳ ከድሬዳዋ ጋር ነጥብ ሲጋራ ከተጠቀማቸው ተጫዋቾች መካከል በአራቱ ላይ ለውጥ አድርጓል። ሰለሞን ወዴሳን በመድሀኔ ብርሀኔ ፣ እንየው ካሳሁንን በአቤኔዘር ኦቴ ፣ ታፈሰ ሠለሞንን በአቤኔዘር ዮሐንስ ፣ አማኑኤል ጎበናን በተባረክ ሄፋሞ ተክተዋል። በመድኖች በኩል በድቻ ከተረታው ስብሰባቸው ባደረጉት ሦስት ቅያሪዎች ተካልኝ ደጀኔ ፣  ሐቢብ ከማል እና ያሬድ ዳርዛን በማሳረፍ አዲስ ተስፋዬ ፣ አቡበከር ወንድሙ እና ቹኩዌመካ ጎድሰንን ወደ ሜዳ አስገብተዋል።

ክፍት በነበረው እና ሁለቱም ቡድኖች ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ በደረሱበት የመጀመሪያ አጋማሽ መድኖች ገና በ 2ኛው ደቂቃ የሀዋሳን የተከላካይ መስመር ፈትነዋል። አቡበከር ወንድሙ በሳጥኑ የቀኝ ክፍል በጥሩ ሩጫ ይዞት የገባውን ኳስ ወደ ውስጥ ሲቀንሰው ግብ ጠባቂው ቻርለስ ሉካጎ አቋርጦበታል። በሦስት ደቂቃዎች ልዩነት ደግሞ ኃይቆቹ ተመሳሳይ የግብ ዕድል ፈጥረው ነበር። ዓሊ ሱሌይማን ከግራ መስመር ያሻገረለትን ኳስ ያገኘው ተባረክ ሒፋሞ ኳሱን በትክክል በግንባሩ ሳይገጨው ቀርቶ የግብ አጋጣሚውን ሳይጠቀምበት ቀርቷል።


ሀዋሳ ከተማዎች በረጃጅም ኳሶች ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ ጥረት ሲያደርጉ መድኖች በአንጻሩ በአጫጭር ቅብብሎች ዝግ ያለ የማጥቃት ሂደት ሲከተሉ ተስተውሏል። ሆኖም 19ኛው ደቂቃ ላይ ኃይቆቹ ጨዋታውን ለመምራት ተቃርበው ነበር። ኢዮብ ዓለማየሁ ከቀኝ መስመር በተሻገረለት ኳስ ለማስቆጠር ምቹ ቦታ ላይ ቢገኝም ሙከራውን ግብ ጠባቂው አቡበከር ኑራ አግዶበት ወርቃማውን የግብ ዕድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል።


ከወትሮው በተለየ በማጥቃት እንቅስቃሴያቸው ተዳክመው የቀረቡት መድኖች በመጀመሪያው አጋማሽ የመጨረሻ 10 ደቂቃዎች ቀጥተኛ ኳስ ወደ መጫወት ተሸጋግረው በመጠኑ መነቃቃት ሲያሳዩ በዚሁ እንቅስቃሴያቸውም 37ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ከግብ ጠባቂ ጋር የተገናኘው አቡበከር ወንድሙ የግብ ዕድሉን ዒላማውን ባልጠበቀ ሙከራ አባክኖታል።


ከዕረፍት መልስ ቀዝቃዛ በነበሩት የመጀመሪያ 30 ደቂቃዎች መድኖች የተጫዋቾች ቅያሪ በማድረግ በተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በተደጋጋሚ መደረስ ቢችሉም የመጨረሻ ኳሳቸው ግን ደካማ ነበር። በአጋማሹ ከነበራቸው ፈጣን እንቅስቃሴ ተቀዛቅዘው የቀረቡት ኃይቆቹ 49ኛው ደቂቃ ላይ የተሻለውን የግብ ዕድላቸውን መፍጠር ችለው ነበር። አቤኔዘር ዮሐንስ የመድኑ አማካይ አሚር ሙደሲር በስህተት ባቀበለው ኳስ ተከላካዮችን አታልሎ በማለፍ ያደረገውን ሙከራ ተከላካዮች ተደርበው አምክነውበታል።


በዝናባማ እና ለጨዋታ ምቹ በሆነ የዓየር ሁኔታ በቀለጠው ጨዋታ መድኖች 57ኛው ደቂቃ ላይ የአጋማሹን የመጀመሪያ ጥሩ የግብ ሙከራ አድርገዋል። ንጋቱ ገ/ሥላሴ ከሳጥን ውጪ ያደረገው ሙከራ በግቡ የግራ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል። ጨዋታው ለቀጣይ ሃያ ደቂቃዎች በተመሳሳይ ሂደት ቀጥሎም 77ኛው ደቂቃ ላይ በመድን በኩል ተቀይሮ የገባው ያሬድ ዳርዛ ከሳጥን አጠገብ መሬት ለመሬት በመምታት ግሩም ሙከራ ቢያደርግም በግቡ የቀኝ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል። ሆኖም ጨዋታው በቀሪ 15 ደቂቃዎች በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ ለመውሰድ የተሻለ ፉክክር ቢደረግበትም ተጠቃሽ የማጥቃት እንቅስቃሴ ሳይደረግበት ያለ ግብ ተጠናቋል።