ሪፖርት | የጣና ሞገዶቹ በሀብታሙ ታደሰ ግቦች ሠራተኞቹን ረተዋል

በምሽቱ ጨዋታ ባህርዳር ከተማ ሀብታሙ ታደሰ በመጀመሪያው አጋማሽ ባስቆጠራቸው ሦስት ግቦች ወልቂጤ ከተማን 3-0 ረቷል።

ምሽት ላይ የወልቂጤ ከተማ እና የባህርዳር ከተማ ጨዋታ ሲደረግ ባህርዳር ከተማዎች ከኢትዮጵያ ቡና ጋር አቻ ከተለያየው ቡድናቸው የሦስት ተጫዋችን ለውጥ አድርገዋል። ፍፁም ፍትህዓለሙን በፍራኦል መንግስቱ ፣ ቸርነት ገግሳን በአደም አባስ እና ፍሬው ሠለሞንን በአባይነህ ፊኖ ሲተኳቸው ከሀዲያ ጋር በተመሳሳይ አቻ ባስመዘገቡት ወልቂጤ በኩል በተደረገ የሦስት ተጫዋቾች ቅያሪ ተመስገን በጅሮንድ ፣ አብርሀም ኃይሌ እና ራምኬል ሎክ አርፈው ጌቱ ኃይለማርያም ፣ ጋዲሳ መብራቴ እና ስንታየሁ መንግሥቱ ወደ ሜዳ ገብተዋል።


የባህርዳር ከተማ ፍጹም የበላይነት በታየበት የመጀመሪያ አጋማሽ የጣና ሞገዶቹ 3ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ዓባይነህ ፌኖ መሳይ አገኘሁ ከቀኝ መስመር ባሻገረለት ኳስ ያደረገው ሙከራ በግብ ጠባቂው ተጨርፎ የግቡ አግዳሚ ገጭቶ ሲመልስበት ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ሆኖ ኳሱን ያገኘው አደም አባስ ወደ ግብ ሲሞክረው ኳሱን ያገኘው ሀብታሙ ታደሰ በቀላሉ ከመስመር በማሳለፍ ግብ አድርጎታል።

የሚታወቁበትን በፈጣን ሽግግር የማጥቃት እንቅስቃሴ እጅግ በተሻሻለ መንገድ ይዘው የቀረቡት ባህርዳሮች 8ኛው ደቂቃ ላይም ያሬድ ባየህ ከርቀት ያሸገረውን ኳስ የወልቂጤ ተከላካዮች ከጨዋታ ውጪ ነው ብለው በተዘናጉበት ቅጽበት ኳሱን የተቆጣጠረው ሀብታሙ ታደሰ በተረጋጋ አጨራረስ መረቡ ላይ አሳርፎታል።


የተጋጣሚያቸውን ጫና ተቋቁመው ከራሳቸው የግብ ክልል ተደራጅተው ለመውጣት የተቸገሩት ሠራተኞቹ የተሻለውን የግብ ዕድላቸውን 14ኛው ደቂቃ ላይ ፈጥረዋል። ስንታየሁ መንግሥቱ አመቻችቶ ባቀበለው ኳስ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ሆኖ ያገኘው አሜ መሐመድ በዘገየ ውሳኔ ሙከራ ሳያደርግ ኳሱን ግብ ጠባቂው ፔፔ ሰይዶ ይዞበታል።

የማያቋርጥ እና በጋለ የጨዋታ ስሜት የሚደረገው የጣና ሞገዶቹ የማጥቃት እንቅስቃሴ በተደጋጋሚ የተጋጣሚ ሳጥን በመድረስ በርካታ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ሲችሉ 38ኛው ደቂቃ ላይም ተጨማሪ ግብ አስቆጥረዋል። ዓባይነህ ፊኖ ከፍ አድርጎ ባቀበለው ኳስ ከአደም አባስ ጋር ሆኖ ያገኘው ሀብታሙ ታደሰ ኳሱን አመቻችቶ ያደረገው ሙከራ ግበሰ ጠባቂውን ፋሪስ አለውን ጥሶ መረቡ ላይ እንዲያርፍ አድርጎታል።


ካለፉት ጨዋታዎች አንጻር በኳስ ቁጥጥሩ እጅግ ተዳክመው የቀረቡት ወልቂጤዎች ለመነሳሳት በሚሞክሩበት ሰዓት 43ኛው ደቂቃ ላይ ወደ ጨዋታው ሊመለሱ የሚችሉበትን የተሻለውን አጋጣሚ አግኝተው ነበር። ያሬድ ባዬህ ወደ ግራው የሳጥኑ ክፍል እየገባ የነበረው አሜ መሐመድ ላይ በሠራው ጥፋት የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት አምበሉ ሳምሶን ጥላሁን ሲመታ ግብ ጠባቂው ፔፔ ሰይዶ መልሶበታል።

ከዕረፍት መልስ ሠራተኞቹ የተጫዋቾች ቅያሪ በማድረግ ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ የራስ መተማመን ተረጋግተው ለመጫወት በመሞከር በተሳኩ ቅብብሎች ከራሳቸው የግብ ክልል ለመውጣት ቢሞክሩም የመጨረሻ ኳሳቸው ፈታኝ አልነበረም።


ጨዋታውን በሰፊ የግብ ልዩነት መምራት በመቻላቸው በሁለተኛው አጋማሽ ወሳኝ ተጫዋቾቻቸውን በማሳረፍ የመሰለፍ ዕድል ላልነበራቸው ተጫዋቾች ዕድል የሰጡት ባህርዳሮች የነበራቸውን የማጥቃት እንቅስቃሴ በማቀዛቀዝ ኳሱን ለመቆጣጠር ሲሞክሩ በአጋማሹም አደም አባስ ከሳጥን ውጪ ካደረገው ሙከራ ውጪ የተሻለ ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል።

መሃል ሜዳው ላይ በኳስ ቁጥጥሩ ቅልጫ በመውሰድ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ሲታትሩ የነበሩት ሠራተኞቹ 74ኛው ደቂቃ ላይ ከክፍት ጨዋታ የተገኘውን የተሻለ የግብ ዕድል ፈጥረው ነበር። ዳንኤል መቅጫ አመቻችቶ ባቀበለው ኳስ ወደ ሳጥን መግባት የቻለው ራምኬል ሎክ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ፔፔ ሰይዶ በጥሩ ብቃት መልሶበታል።


በቀሪ 15 ደቂቃዎች ጨዋታው እየተቀዛቀዘ ሲሄድ በወልቂጤ ከተማ በኩል ራምኬል ሎክ ከሳጥን አጠገብ ያደረገው ዒላማው ያልጠበቀ ሙከራ በጣና ሞገዶቹ በኩል ደግሞ 95ኛው ደቂቃ ላይ መሳይ አገኘሁ ሞክሮት ግብ ጠባቂው ፋሪስ አለው ከመለሰበት ኳስ ውጪ ተጠቃሽ የማጥቃት እንቅስቃሴ ሳይደረግ ጨዋታው በባህርዳር ከተማ 3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።