“ሦስቱ ነጥቡ ይገባናል ብዬ አስባለሁ” አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው
“በመጀመሪያ ደቂቃዎች የነበረን አለመረጋጋት ሁሉን ነገር ሊረብሸው ችሏል።” አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት
የጣና ሞገዶቹ በሀብታሙ ታደሠ ሦስት ጎሎች ሠራተኞቹን ከረቱበት የምሽቱ ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ ሶከር ኢትዮጵያ ከአሰልጣኞቹ ጋር ቃለ ምልልስ አድርጋለች።
አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው – ባህርዳር ከተማ
ስለ ጨዋታው …
“ሦስት ነጥብ ያስፈልገን ነበር። ተጋጣሚያችን ወልቂጤ ልምድ ባላቸው ተጫዋቾች የተዋቀረ ጠንካራ ቡድን ነው። ማህበረሰቡም እግርኳስ በጣም የሚወድ ነው ፤ ደጋፊዎችም ሜዳ ተገኝተው ምን ያህል ለጨዋታው ድምቀት እንደሆኑ ያየንበት ሁኔታ ነው ያለው። እንደ ቡድን የተሻለ ነገር ለማድረግ ሞክረናል። ምናልባት ሦስቱ ነጥብ ይገባናል ብዬ አስባለሁ። ተጫዋቾቻችን ጥሩ ነበሩ። በተለይ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ በቁጥር በልጠን ለመገኘት የምናደርገው እንቅስቃሴ የተሳካ ነበር። እንደ አጠቃላይ የመከላከል አደረጃጀቱም ሆነ በማጥቃት እንቅስቃሴው ላይ የነበረው ሽግግር መልካም የሚባል ነው። እንደ ቡድን ብዙ ማሳደግ የሚገቡ ነገሮች እንዳሉ እናውቃለን። በተቻለ መጠን በድክመቶቻችን ላይ የበለጠ እየሠራን የተሻለ ነገር እናመጣለን ብዬ አስባለሁ ፤ እንደ ጨዋታ ግን መልካም ጨዋታ ነበር።”
የፍሬው ሠለሞን እና የቸርነት ጉግሳ አለመሰለፍ…
“ባለፈው ጨዋታ ጉዳት አስተናግደው ነው የወጡት። ምናልባት ‘ለቀጣይ ጨዋታ ይደርሳሉ አይደርሱም ?’ የሚለው ገና ወደፊት የሚታይ ነው የሚሆነው። ልምምድም እየሠሩ ያለበት ሁኔታ አይደለም ያለው ፤ ጠንከር ያለ ጉዳት ነው ያስተናገዱት። ፍሬው ሠለሞን የብሽሽት ጉዳት ፣ ቸርነት ደግሞ የሀምስትሪንግ ጉዳት ነው ያስተናገደው ጊዜ የሚፈልግ ነው ጉዳቱ። በተቻለ መጠን ቶሎ አገግመው ለቀጣይ ጨዋታዎች ቢደርሱልን ደስተኞች ነን ፤ የሚመጣውን ነገር ወደፊት ማየት ነው።”
ስለ ሀብታሙ ታደሠ ሦስት ጎሎች…
“ሀብታሙ ትልቅ አቅም ያለው ተጫዋች ነው። ከኳስ ጋር ምቾት ተሰምቶት የሚጫወት እንቅስቃሴው በጣም ቆንጆ ነው። ከጓደኞቹ ጋር በአንድ ሁለት ቅብብል የመጫወት ችግር የለበትም ከምንም በላይ ደግሞ የመጀመሪያ ተመራጭ አጥቂያችን ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ጎሎችን እያገባ በሄደ ቁጥር በራስ መተማመኑም የበለጠ ከፍ የሚያደርግለት ስለሆነ ለክለባችንም ለሀገርም የሚጠቅም ተጫዋች በመሆኑ ዛሬም ባሳየው ብቃት እጅግ በጣም ደስተኞች ነን ፤ እንኳን ደስ አለህ ማለት እፈልጋለሁ።”
ስለተጋጣሚያቸው ወልቂጤ ከተማ…
“ወልቂጤ ጠንካራ ቡድን ነው። ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች የተዋቀሩበት ቡድን ነው። ምንአልባት የእኛ ተጫዋቾች ለጨዋታው ተገቢውን ትኩረት ሰጥተው ሜዳ ከመግባታቸው ጋር ተያይዞ የመጀመሪያው አርባ አምስት ደቂቃ ገለን የወጣንበት ስለነበረ የእኛ ተጫዋቾች እንቅስቃሴ ጎልቶ በውጤት በመታጀቡ የወልቂጤን እንቅስቃሴ አጉልቶ ላያወጣው ይችላል ብዬ አስባለሁ። እንጂ ወልቂጤ በጣም ጥሩ ቡድን ነው ፣ ኳስ ይዘው ለመጫወት የሚሞክሩ ናቸው ፣ አደረጃጀታቸው በጣም ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ቡድን ነው። ወልቂጤ ከዚህ በላይ ይጓዛል ብዬ አስባለሁ።”
አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት – ወልቂጤ ከተማ
ስለ ጨዋታው…
“በመጀመሪያው አጋማሽ አለመረጋጋቶች ነበሩ ጎሎች ሲቆጠሩብን። ከዛ በኋላ ግን ወደ አቋማችን ለመመለስ ሰዓቶች ፈጅቶብን ነበር። ከዕረፍት በኋላ ግን መጠነኛ መሻሻሎች ታይተዋል።”
በመጀመሪያዎቹ አስር ደቂቃዎች ስለተፈጠሩ ነገሮች…
“ምንም የተፈጠረ ነገር የለም። ትኩረት አለማድረግ እና አለመረጋጋት እንጂ ምንም የተፈጠረ ነገር የለም ፣ የመጀመሪያ 10-15 ደቂቃ ውስጥ እንቆጣጠር ብለን ነበር ፤ እነሱን እንያቸው ብለን ነበር። ሆኖም አለመረጋጋት ስለነበረ በፈራነው በኩል እነሱም አጋጣሚውን አገኙ እና ተጠቀሙብን። ከዚያ በኋላም ለመመለስ ጥረት አድርገናል ፣ ፍፁም ቅጣት ምት ስተናል ሌሎች ኳሶችም አግኝተን ስተናል። ምንም ማድረግ ስለማይቻል ለቀጣዩ ጨዋታ ተዘጋጅተን እንመለሳለን።”
በኳስ ቁጥጥሩ ስለ መዳከማቸው…
“ምንም የተለየ ምክንያት የለውም። ዛሬ እነሱ በኳስ ቁጥጥሩ የተሻሉ ስለነበሩ በልጠውናል። በመጀመሪያ ደቂቃዎች የነበረን አለመረጋጋት ሁሉን ነገር ሊረብሸው ችሏል። እነሱ ደግሞ ያ በራስ መተማመን ስለሰጣቸው ፤ እንደምናውቀውም ባህርዳር ጠንካራ ቡድንም ነው በዛ ደረጃም ስለመጣ የተሻሉ ነበሩ።”