በበርካታ ደጋፊዎች ታጅቦ በተደረገው የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ ፋሲል ከነማ በአማኑኤል ገብረሚካኤል ግቦች ኢትዮጵያ ቡናን 2-0 ረቷል።
በሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ ፋሲል ከነማ እና ኢትዮጵያ ቡና ሲገናኙ ዐፄዎቹ ሲዳማን ከረቱበት አሰላለፍ የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገዋል። እዮብ ማቲያስ እና አማኑኤል ገብረሚካኤል በዮናታን ፍስሃ እና በናትናኤል ገብረጊዮርጊስ ተተክተው ሲገቡ ከባህርዳር ጋር ነጥብ በተጋሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች በኩል የካኮዛ ዴሪክን ቦታ መስፍን ታፈሰ ተረክቧል።
መጠነኛ ፉክክር በታየባቸው የመጀመሪያ 20 ደቂቃዎች ያን ያህል ተጠቃሽ የማጥቃት እንቅስቃሴ ባይደረግባቸውም በቁጥር በዝቶ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመግባቱ በኩል ዐፄዎቹ የተሻሉ ነበሩ። የጨዋታው የተሻለ የመጀመሪያ ሙከራም በእነርሱ አማካኝነት 5ኛው ደቂቃ ላይ ሲደረግ ሱራፌል ዳኛቸው ከቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ጋቶች ፓኖም ያደረገውን ሙከራ የኳሱ ኃይል-የለሽነት ተጨምሮበት ግብ ጠባቂው በረከት አማረ ይዞበታል።
ቀስ በቀስ ወደ ተሻለ የጨዋታ ግለት የመጡት ቡናማዎቹ በኳስ ቁጥጥሩ ጥሩ እንቅስቃሴ ማድረጋቸውን ቢቀጥሉም 26ኛው ደቂቃ ላይ አብዱልከሪም ወርቁ ከሳጥን አጠገብ ኳሱ በዓየር ላይ እንዳለ ወደ ግብ ሞክሮት ግብ ጠባቂው ሳማኬ ሚኬል ከያዘበት ኳስ ውጪ የጠሩ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲቸገሩ ተስተውሏል።
ከራሳቸው የግብ ክልል ተደራጅተው በመውጣት በፈጣን ሽግግር ለማጥቃት ሲሞክሩ የነበሩት ፋሲሎች 36ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን ለመምራት እጅግ ተቃርበው ነበር። ሱራፌል ዳኛቸው ከቀኝ መስመር የሰነጠቀለትን ኳስ በግራው የሳጥኑ ክፍል ሮጦ በመግባት ኳሱን የተቆጣጠረው ቃልኪዳን ዘላለም ከግብ ጠባቂ ጋር አንድ ለአንድ ቢገናኝም ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው በረከት አማረ መልሶበት ወርቃማውን የግብ ዕድል አባክኖታል። በአንድ ደቂቃ ልዩነትም ቡናዎቹ በተመሳሳይ ተጨማሪ የግብ ዕድል አግኝተው ነበር። መስፍን ታፈሰ ከቅጣት ምት በተነሳ ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ሙከራ ቢያደርግም በኳሱ አቅጣጫ የነበረው ግብ ጠባቂው ሳማኬ ሚኬል በቀላሉ ይዞበታል። ሆኖም አጋማሹ የተጠበቀውን ያህል ፉክክር ሳይደረግበት ተጠናቋል።
ከዕረፍት መልስ ጨዋታው እጅግ ተሻሽሎ ሲቀጥል አጋማሹ በተጀመረ በሴኮንዶች ውስጥ ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ ያደረጉት ፋሲሎች በጌታነህ ከበደ አማካኝነት ግብ አስቆጥረው ነበር። ሆኖም ሳጥን ውስጥ ጥፋት በመሠራቱ ግቡ ሲሻር በአንድ ደቂቃ ልዩነት ደግሞ ቡናማዎቹ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ነበር። ጋቶች ፓኖም ሲያቀብል በሠራው ሰህተት ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ሆኖ ኳሱን ያገኘው ብሩክ በየነ ያደረገው ሙከራ በግቡ የቀኝ ቋሚ በኩል ወጥቶበት የግብ ዕድሉን ሳይጠቀምበት ቀርቷል።
ጨዋታው 54ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ በዐፄዎቹ አማካኝነት ግብ ተቆጥሮበታል። ቃልኪዳን ዘላለም ከቀኝ መስመር ያሻገረለትን ኳስ ከሳጥኑ የግራ ጠርዝ ላይ ሆኖ ያገኘው አማኑኤል ገብረሚካኤል መሬት ለመሬት በመምታት መረቡ ላይ አሳርፎታል። ግብ ባስቆጠሩበት ቅፅበት የተሻለ መነቃቃት በፈጠሩት ፋሲሎች በኩል ግብ ካስቆጠሩ በአምስት ደቂቃዎች ልዩነትም ጋቶች ፓኖም ከሳጥን ውጪ አክርሮ በመምታት ግሩም ሙከራ ቢያደርግም በግቡ አግዳሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል።
ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ የአቻነት ግብ ፍለጋ መታተራቸውን የቀጠሉት ኢትዮጵያ ቡናዎች 65ኛው ደቂቃ ላይ በጠንካራ የማጥቃት እንቅስቃሴ ንጹህ የግብ ዕድል ፈጥረው ነበር። አብዱልከሪም ወርቁ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ግብ ጠባቂው ሳማኬ ሚኬል በጣቱ ከሸረፈው በኋላ ኳሱን የሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ሆኖ ያገኘው በፍቃዱ ዓለማየሁ ግሩም ሙከራ ቢያደርግበትም በግቡ የቀኝ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል።
አማኑኤል ዮሐንስን ቀይረው በማስገባት መሃል ሜዳው ላይ በተረጋጋ የኳስ ቁጥጥር መጠነኛ ብልጫ መውሰድ የቻሉት ቡናዎች 75ኛው ደቂቃ ላይም ከቆመ ኳስ ተጨማሪ የግብ ዕድል መፍጠር ችለው ነበር። አማኑኤል ዮሐንስ በግራ መስመር ከተገኘ የቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ ከአንድ ንክኪ በኋላ ዝግጁ ሳይሆን ያገኘው ጫላ ተሺታ በጉልበቱ የገፋው ኳስ በግቡ የግራ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቷል።
ወደ ራሳቸው የግብ ክልል በመጠጋት ውጤቱን ለማስጠበቅ ጨዋታውን ማረጋጋት የፈለጉት ዐፄዎቹ 80ኛው ደቂቃ ላይ ቡናማዎቹ በሙሉ የተጫዋች ቁጥር ለማጥቃት ወደ እነርሱ ግብ ክልል መምጣታቸውን ተከትሎ ባደረጉት የመልሶ ማጥቃት መሪነታቸውን አጠናክረዋል። አማኑኤል ገብረሚካኤል ከራሱ የሜዳ ክልል በፍጥነት በመውጣት ከመሃል ሜዳ ጀምሮ ኳሱን ለብቻው እየገፋ በመውሰድ በተረጋጋ አጨራረስ አስቆጥሮታል። በቀሪ ደቂቃዎችም ቡናማዎቹ በተሻለ የኳስ ቁጥጥር ወደፊት ተጭነው ለመጫወት ጥረት ቢያደርጉም ፋሲሎች በተረጋጋ እንቅስቃሴ ውጤቱን ማስጠበቅ ችለዋል። ጨዋታውም በፋሲል ከነማ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።