“ዕድለኛ በመሆናችን እንጂ የጠበቅነውን ያህል አይደለም የነበረው እንቅስቃሴ” አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ
“እነርሱ ዕድለኞች ነበሩ ውጤቱን አግኝተውታል” አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ
የሳምንቱ ማሳረጊያ በሆነው የጦና ንቦቹ እና የጦሩ ጨዋታ 1ለ0 በሆነ ውጤት በመቻል ድል አድራጊነት ከተፈፀመ በኋላ ሁለቱም አሰልጣኞች ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር የድህረ ጨዋታ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።
አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ – መቻል
ስለ ጨዋታው…
“ጨዋታውን በማሸነፋችን ደስተኞች ነን ፣ ዕድለኛ በመሆናችን እንጂ የጠበቅነውን ያህል አይደለም የነበረው እንቅስቃሴ ግን አንዳንዴም እንደዚህ ሆነህ ታሸንፋለህ እና በዛ ጥሩ ነው።”
ከዕረፍት በፊት የመጀመሪያ 15 እና 20 ደቂቃ ወደ ራሳቸው የግብ ክልል ተጠግተው ስለ ተጫወቱበት ሂደት..
“አንዳንዴ ተጫዋቾች ጨዋታውን እያነበቡ ነው የሚጫወቱት ስለዚህ የገጠማቸውን ችግር ለመፍታት ፣ መፍትሄ ማበጀት የተጫዋቾች ስራ ነው ።ከዛ አንፃር ነው የማየው ጥሩ ነው ያደረጉት ነገር ብዬ ነው የምናገረው።”
ዛሬ ቡድኑ ላይ ስለ ነበረው ጠንካራ ጎን እና ስለ በረከት ደስታ ድንቅ ጎል…
“ለእኔ በሁሉም ፣ ማሸነፍ በራሱ ጠንካራነት ነው ስለዚህ ጠንካራ ነን። ጥሩ ግብ ነው እንዲህ አይነት ግቦች አንዳንዴ ነው የሚገኙት ፣ ተጨማሪ ጎል ቢኖር ኖሮ ደስ ይለናል። በረከት የእውነት ጥሩ ነው እንቅስቃሴዎቹ በዚህ ሦስት ጨዋታዎች ላይ ከመስመር ተጫዋቾች ድንቅ ብቃት እያሳየ ያለ ተጫዋቾች ነው። በዚሁ ከቀጠለ ወደፊት የተሻለ ነገር ያመጣል ብዬ እላለሁ።”
አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ – ወላይታ ድቻ
ከነበረው የኳስ ቁጥጥር ብልጫ አንፃር የግብ ዕድሎችን የመፍጠር ውስንነቶች ስለመኖራቸው…
“ጠንካራ የመከላከል ቡድን ነበር የገጠመን መቻል በዛ ምክንያት ጎል የማግኘት ዕድሎቻችን ትንሽ ከሌሎቹ ቀናቶች ያነሱ ነበሩ። ያገኘናትም አንድ ሁለት አጋጣሚ ስተናል እና በዚህ ምክንያት እነርሱ ዕድለኞች ነበሩ ውጤቱን አግኝተውታል።”
ከአሰልጣኙ የጨዋታ መንገድ አንፃር አጥቂዎች በሚፈለገው መልኩ እየተጫወቱ ስላለመሆኑ…
“አይደለም ፣ በልምምድ ቦታ ላይ በጣም በተደጋጋሚ ጊዜ ከዚህ ከአጨራረስ ጋር በተገናኘ ስራዎች ሰርተናል ግን አሁን ላይ ወደ ሜዳ ላይ ለመተግበር ትንሽ የሚጎል ነገር አለና ፣ ያንን አሁንም ጠንክረን ሰርተን የግድ ውጤታማ ማድረግ ይጠበቅብናል።”
ስለ ቅያሪ ተጫዋቾች ስኬታማነት…
“ስኬታማ ናቸው ፣ ጨዋታውን ሙሉ ዘጠና ደቂቃ እንደውም በሁለተኛው አርባ አምስት እነርሱ ሜዳ ላይ ነው የጨረስነው ፣ እነርሱ ደግሞ የመከላከሉን ሐይል አብዝተው ገብተው ዘግተውብን ወደ ጎል የምንደርስባቸውን መንገዶች በሙሉ እያበላሹብን ነበር እና በዛ ምክንያት ጎል የማግባት ዕድሉን አላገኘንም።”
ግቧ ስትቆጥር ተከላካዮች የነበራቸው መዘናጋት…
“አንዳንድ ጊዜ በእግር ኳስ ሜዳ ከስህተቱ ነው ውበቱን የምታውቀው እና ያቺ ስህተት ዋጋ አስከፍላናለች።”
የጨዋታ መንገዱ በሚፈለገው መንገድ ስለ መሄዱ…
“የጨዋታ ሂደቱ እጅግ በምፈልገው አይነት እየሄደ ነው። ተጫዋቾቹ የተሰጣቸውን የስራ ሀላፊነት ሜዳ ላይ በትክክል እየተወጡ ነው። አሁን አንድ የጎደለችን ነገር ምንድናት የመጨረስ ችግር ነው ፣ ያን የመጨረስ ችግር ደግሞ ሳንታክት ሰርተን ወደ ውጤት ማምጣት ይጠበቅብናል።”