👉”ወደዚህ ሃላፊነት ስመጣም ህዝቡ በብሔራዊ ቡድኑ ውጤት እያነባ የታይታ ጨዋታ ቡድኔ እንዲጫወት አልፈልግም።”
👉”በተፈጥሮዬ እየነካኩ መዋልን አልወድም ፤ ቡድናችን በተወሰነ ጊዜ ውስጥ በዚህ ረገድ ለውጦች እንደምናይበት አምናለሁ።”
👉”ለብሔራዊ ቡድኑ የሚመጥን ሰው መድን ጋር ካለ ይመረጣል ከሌለ አይመረጥም።አስር ተጫዋቾች ከአንድ ክለብ ሊኖር ይችላል ከሌላ ክለብ ደግሞ ላይኖር ይችላል።….”
👉”በግሌ ብሔራዊ ቡድኑን ውጤታማ ለማድረግ ረጅም ጊዜ መውሰድ አለብኝ የሚል እምነት የለኝም።….”
👉”በ15 ቀን ውስጥ ተአምር እሰራለሁ አልላችሁም።…
👉”በሁለቱም ጨዋታዎች የማያሳፍር ውጤት ይዘን ለመምጣት እንጥራለን።”
👉”ህልሜን ለማሳካት ገና መንገዱን ጀምርያለሁ በአጭር ጊዜ ላይሳካ ቢችልም አንድ ቀን……”
ዛሬ ረፋድ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን መሰብሰቢያ አዳራሽ በተጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ ፌደሬሽኑ ከሰሞኑ ይፋዊ ባልሆኑ መንገዶች የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ መሆናቸው አይቀሬ ስለመሆኑ ሲነገርላቸው የነበሩትን አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌን በይፋ የብሔራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ አድርጎ መሾሙን አስታውቋል።
በፌደሬሽኑ የፅህፈት ቤት ሃላፊ በሆኑት አቶ ባህሩ ጥላሁን እና በአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ መሃል በይፋ በተፈረመ የውል ስምምነት ሰነድ ጅማሮውን ያደረገው መርሃግብሩ በማስከተል በአቶ ባህሩ ጥላሁን በኩል በውል ስምምነቱ ስለተካተቱ ዓበይት ሀሳቦች ገለፃ አድገዋል።
እንደ አቶ ባህሩ ገለፃ ከሆነ የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከአምስት ወራት በፊት ከአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ውል የነበረው ውል መጠናቀቁን ተከትሎ አሰልጣኝ ገብረመድህን ቀጣዩ የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ እንዲሆኑ በአንድ ድምፅ ተስማምተው መወሰናቸውን አንስተው ከክላባቸው ኢትዮጵያ መድን ጋር ረዘም ላለ ጊዜ የሚቆይ ቀሪ ውል የነበራቸው መሆኑን ተከትሎ ሁለቱን አካላት የማግባባቱ ሂደት ጊዜ እንደወሰደ እና በመጨረሻም ካሉ ነባራዊ ሁኔታዎች በመነሳት ሁለቱንም ስራ በጋራ እንዲሰሩ ስለመወሰኑ አንስተዋል።
በገለፃቸውም የአሰልጣኙ የቅጥር ውል ወደፊት ሊራዘም የሚችልበት አማራጭ ቢኖረውም ለአሁኑ ግን ከዛሬ አንስቶ ለመጪው አንድ ዓመት የሚቆይ እንደሆነ ገልፀው አሰልጣኙም በቆይታቸው ጥቅማጥቅሞችን ሳይጨምር በወር የተጣራ 250,000 ብር ወርሃዊ ደሞዝ የሚያገኙ ሲሆን በአንፃሩ አሰልጣኙ በቀጣይ በሚኖሩ የማጣርያ ጨዋታዎች ላይ በስነምግባር የታነፀ ጠንካራ እና ተፎካካሪ ብሔራዊ ቡድን የመገንባት ግዴታ እንዳለባቸውም ስለመቀመጡ ጠቅሰዋል።
በተጨማሪነትም አሰልጣኙ ለብሔራዊ የቴክኒክ አማካሪ ቡድን ተከታታይ ሪፖርቶች ሆነ ከህዝብ ግንኙነት ስራ ጋር በተያያዘ ተከታታይ ቅድመ እና ድህረ ጨዋታ መግለጫዎችን የመስጠት ግዴታ እንዳለባቸው ጠቅሰዋል።
አክለውም በሁለቱ አካላት የጋራ ፍላጎት ሆነ ከሁለቱ አካላት በአንዱ የተናጥል ፍላጎት ውል ሲቋረጥ ቀጣሪው ለአሰልጣኙ የአምስት ወራት ደሞዝ በመክፈል ወይንም አሰልጣኙ የአምስት ወር ደሞዛቸውን በመመለስ ማቋረጥ እንደሚቻል በስምምነታቸው ላይ ስለመደንገጉ ይፋ አድርገዋል።
በማስከተል ሀሳባቸውን ያጋሩት አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ በበኩላቸው ከስድስት ዓመታት በኃላ በተጫዋችነት ሆነ በአሰልጣኝነት ያገለገሉትን ብሔራዊ ቡድን ዳግም በአሰልጣኝነት እንዲመሩ የቀረበላቸውን ጥያቄ በደስታ ስለመቀበላቸው አንስተው የቅጥሩ ሂደት ይፋ ከመሆኑ በፊት በተወሰነ መልኩ መልክ ከያዘበት ወቅት አንስቶ ለቀጣይ መርሃግብሮች ተጫዋቾችን ሲመለምሉ መቆየታቸውንም ገልፀዋል።
አሰልጣኙ አያይዘውም ልምድ እና ወጣት ተጫዋቾን ያሰባጠረው የመጀመሪያ ስብስባቸው ዛሬ ማታ ይፋ እንደሚደረግ ገለፀው ቡድኑ ከመጪው እሁድ አንስቶ ልምምድ እንደሚጀምር ጠቁመዋል ፤ በብሔራዊ ቡድኑ በሚኖራቸው ቆይታ በስነምግባር ሆነ በታክቲካዊ ጉዳዮች ላይ ዲሲፕሊንድ የሆኑ ቡድን ለመገንባት እንደሚጥሩም ገለፀዋል።
በመቀጠል ረዘም ያለ ጊዜን በፈጀው በስፍራ ከተገኙ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በርከት ያሉ ጥያቄዎች ተነስተው በሁለቱ አካላት ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል መርሃግብሩ ተቋጭቷል።
ከተነሱት ጥያቄዎች መካከል
በአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ምላሽ የተሰጠባቸው
ብሔራዊ ቡድኑን እና ክለብን በተመሳሳይ ሰዓት ማሰልጠን ስለሚኖረው ጫና እና የጥቅም ግጭት
“ከዚህ ቀደም በነበረው ልምድ ሁለቱን ስራዎች ደርቦ መስራት የተለመደ ነበር ከጊዜያት በኃላ ግን ነገሮች ተቀይረው ሁለቱም በተናጥል በመሉ ሰዓት የሚሰሩበት ሁኔታ ተፈጥሯል።እውነት ለመናገር በጣም ፈታኝ ሃላፊነት ነው ፤ በጣም ብርታትን የሚጠይቅ ነው።አሁን ላይ ባለው የሊጉ የውድድር ቅርፅ ከበፊቱ በተለየ በአንድ ከተማ ላይ የመደረጉ ጉዳይ ከበፊቱ አንፃር ስራውን በተወሰነ መልኩ በተለይ ከምልመላ እና ተጫዋቾች ክትትል አንፃር ያቀለዋል።ወደ ውድድር በምንገባበት ጊዜ ሊጉ ስለሚቋረጥ በዚህ መሃል የሚኖሩትን ጊዜያትን ነው የምንጠቀመው በመሆኑም የተወሰኑ ጥቃቅን ችግሮች ቢኖሩም ካለው ሁኔታ አንፃር አቻችሎ መጓዝ ያስፈልጋል።”
“ከሁሉም በፊት የሚቀድመው የብሔራዊ ቡድኑ ጉዳይ ነው ፤ ለብሔራዊ ቡድኑ የሚመጥን ሰው መድን ጋር ካለ ይመረጣል ከሌለ አይመረጥም።አስር ተጫዋቾች ከአንድ ክለብ ሊኖር ይችላል ከሌለ ክለብ ደግሞ ላይኖር ይችላል።ቡድኑ ውጤታማ ቢሆን ከምንም በላይ ደስተኛም የምሆነው ተጠቃሚም የምሆነው እኔው ነኝ ፤ በመሆኑም ውጤት ሊያስገኝልኝ የሚችልን ሰው ትቼ ሌላ ሰው ይዤ አልሄድም።በመሆኑም ከጥቅም ግጭት ጋር የተነሳው ጉዳይ ከዚህ አግባብ ሊታይ ይገባል ብዬ አስባለሁ።”
በአጭር ጊዜ ውል ውጤታማ ቡድንን ስለመገንባት
“በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤት ማምጣት ሊከብድ ይችላል ከዚህ ቀደም በነበረኝ የአምስት ወራት ቆይታ ሁለት ጨዋታዎችን አድርገን ሁለቱንም ማሸነፍ ችለናል።በግሌ ብሔራዊ ቡድኑን ውጤታማ ለማድረግ ረጅም ጊዜ መውሰድ አለብኝ የሚል እምነት የለኝም። ከብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ጋር የሚኖርህ ቆይታ ምንግዜም አጭር ነው ከውድድር በኃላ ወደ ክለቦቻቸው ይበተናሉ በመሆኑም በሚኖርህ አጭር ጊዜ የቡድን ስራ ፣ ታክቲካዊ ሀሳቦች እና ሌሎች ጉዳዮችን በፍጥነት በማስረዝ በሂደት የማስቀጠል ስራ ነው የሚሆነው ለዛም ነው ከጥቂት የግለሰቦች ለውጥ ውጭ ብሔራዊ ቡድኖች የማይፈርሱት።ለእኔ አዲስ አሰልጣኝ ስለሆንኩ ምናልባት አስቸጋሪ ሊሆንብኝ ይችላል ለዚህም በ15 ቀን ውስጥ ተአምር እሰራለሁ አልላችሁም።ተጫዋቾች ውድድር ላይ ስለሆኑ የአካል ብቃት ስራዎችን አንሰራም በሚኖሩን ቀናት ከተጋጣሚዎቻችን መነሻነት ቡድኑ ቅርፅ ይዞ እንዲሄድ ለማስቻል እንሰራለን።በሁለቱም ጨዋታዎች የማያሳፍር ውጤት ይዘን ለመምጣት እንጥራለን።”
በብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝነት ስላላቸው ህልም
“ማንኛውም ኢትዮጵያዊ እንደሚመኘው በግሌ ለዚህ ቡድን ምኞቶች አሉኝ ፤ ለሀገሬ በቻልኩት መጠን ጥሩ ነገር ሰርቼ ማለፍ እፈልጋለሁ በክለብ ከከሰራኋቸው ስኬቶች ባሻገር ለሀገር መስራት በራሱ የተለየ ስሜት አለው።በዚህ ውስጥ ሀገርን ለተሻለ ደረጃ ማብቃት ስምን ከመትከል ባለፈ ትልቅ የአዕምሮ እርካታ አለው ስለዚህ ህልሜን ለማሳካት ገና መንገዱን ጀምርያለሁ በአጭር ጊዜ ላይሳካ ቢችልም አንድ ቀን ግን ሁሉንም ሊያስደስት የሚችል ነገር እንደምሰራ ተስፋ አደርጋለሁ።”
በእሳቸው እምነት ብሔራዊ ቡድኑ ጓድሎታል ብለው ስለሚያስቡት ነገር
“ምንም ጊዜም ስራ የሚሰራው በችግሮችህ ዙርያ ነው። እሱ እዚህ ላይ መዘርዘር አስፈላጊ ባይሆንም የለየናቸው ጉዳዮች አሉ።ስራዎቻችንም የሚያተኩሩት ያሉንን ነገሮች ጠብቀን ችግሮችን መቅረፍ ላይ ነው።ለምሳሌ በፈጣን እንቅስቃሴ ውስጥ ሆኖ ከሜዳው ቶሎ ለመመውጣት የሚቸገር ቡድን እንደሆነ አይተናል ስለዚህ በዚህ ጉዳይ ላይ የምንሰራቸው ነገሮች ይኖራሉ።ስለዚህ ቡድኑ ከራሱ ሜዳ ወደ ተጋጣሚ አጋማሽ ኳሱን በማፍጠን በፍጥነት የሚሸጋገርበትን መንገድ መፍጠር ይኖርብናል።”
በብሔራዊ ቡድኑ ሊተገብሩት ስለሚችሉት የጨዋታ መንገድ
“እኔ አንድ እና አንድ በየትኛውም መንገድ ውጤት ማምጣት ያስፈልጋል የሚል እምነት አለኝ።ወደዚህ ሃላፊነት ስመጣም ህዝቡ በብሔራዊ ቡድኑ ውጤት እያነባ የታይታ ጨዋታ ቡድኔ እንዲጫወት አልፈልግም።የእኔ ቡድኖች ይታወቃሉ ወደፊት ለመጫወት የተቃኙ ናቸው ብሔራዊ ቡድኑ ላይም ይህን መስራት እፈልጋለሁ።ምንግዜም ቢሆን ማጥቃት ላይ መሰረት ያደረገ ቡድኑን መስራት እፈልጋለሁ። በዚህ ውስጥ የኳስ ቁጥጥሩ ጥሩ ሆኖ ግን ደግሞ ቶሎ ቶሎ ወደፊት የሚደርስ ቡድን እንዲኖረን እፈልጋለሁ። ረዘም ላለ ጊዜ እንደ ግል ሳይሆን እንደ ቡድን ኳስ የሚይዝ ቡድንን እፈልጋለሁ በእኔ ቡድን ውስጥ ግለሰቦች ኳሶችን እንዲይዙ አልፈልግም ስንጫወት ኳሱ በቡድናችን ስር ሆኖ በፈጣን እንቅስቃሴ ቶሎ ቶሎ ወደፊት እንድንሄድ እፈልጋለሁ።በዚህ መንገድ ብንጫወት ምንጊዜም ደረጃችን የሚፈቅደውን ውጤት አናጣም ብዬ አስባለሁ።የምንሰራው እጃችን ላይ ያሉ ተጫዋቾችን ይዘን ነው ዝም ብለን ተነስተን እንዲህ ነው እንዲህ ነው ብንል ብዙም ትርጉም አይሰጥም።እየነካኩ መዋልን በተፈጥሮዬ አልወድም ፤ ቡድናችን በተወሰነ ጊዜ ውስጥ በዚህ ረገድ ለውጦች እንደምናይበት አምናለሁ።”
በአቶ ባህሩ ጥላሁን ምላሽ የተሰጠባቸው ጉዳዮች
ክለብን እና ብሔራዊ ቡድንን በጋራ ማሰልጠንን ስለሚከለክለው ህግ
“እውነት ነው ይህን የሚከለክል ህግ አለን ፤ ነገርግን ይህን ህግ ያወጣው የፌደሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ይህንን ቅጥር ግን እንደ ልዮ ሁኔታ ተመልክቶታል።በመሆኑም ለፌደሬሽኑም ሆነ ለብሔራዊ ቡድኑ ጥቅም ሲባል ይህን ውሳኔ ወስነናል።”
ስለውል ርዝመቱ አጭርነት
“በአንድ አመት ውል ሁለት ስራዎችን ደርበው እንዲሰሩ እንደመቀጠራቸው ጫና ውስጥ እንደሚሆኑ እናምናለን ፤ ከዛ መነሻነት አሰልጣኙ በውላቸው ላይ በግዴታነት የተቀመጡት አንቀፆች ይበልጥ በጥቅሉ እንዲቀመጡ የተደረገበትም ከዚህ መነሻነት ሊታይ ይገባል።ውሉ በይበልጥ ሁለቱን አካላት በሚጠቅም መልኩ የተዘጋጀ ነው ብለን እናምናለን።”
“አሰልጣኙ በክለብ ሀላፊነት ላይ ያሉ መሆናቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት ሁለቱን ነገሮች በጊዜያዊነት አስታርቆ ለመሄድ እንጂ ከአሰልጣኙ ጋር ያለን ስምምነት በአንድ አመት ብቻ የሚገደብ አይደለም በሚኖሩ ሂደቶች ላይ ተመስርተን የምናራዝመበት አግባብም በሚገባ በውሉ ላይ ተቀምጧል።”
“ውሉ ላይ ለምሳሌ የአለም ዋንጫ ማሳለፍ የሚል ብናካትትበት የማጣሪያዎቹ ሂደቶች በራሳቸው ለሁለት አመት የተጠጋ ጊዜን ይፈጃሉ ለዚህም በመፍትሔነት ያስቀመጥነው የስራ ነፃነት ለአሰልጣኙ በመስጠት በተቀመጠው ጊዜ ከአሰልጣኙ የሚፈለገውን ነገር የማግኘት ጉዳይ ነው።”
ከኢትዮጵያ መድን ጋር ስለነበራቸው ግንኙነት
“የኢትዮጵያ መድን የስፖርት ክለቡ ሆነ የተቋሙ የበላይ አመራሮች ጋር ተገናኝተን ተወያይተናል። የወሰድነው የውሳኔ አማራጭ ለሁለታችንም ጠቃሚ ነው ብለን ነው የምንወስደው በእነሱ በኩል ክለቡ የቀደመ ገናናነቱን ለመመለስ ከአሰልጣኙ ጋር መስራት የሚፈልጉት ትልቅ ፕሮጀክት ይዘው እየሰሩ ስለመሆኑ አስረድተውናል በእሱም ተማምነናል።እንደውም እነሱ አሰልጣኙን ፌደሬሽኑ ካለው ህጋዊ ስልጣን አንፃር በጉልበት የመውሰድ መብት አላችሁ ነበር ያሉን ነገር ግን እኛ ማድረግ የፈለግነው የሁለታችንንም ፍላጎት ያስታረቀ እንዲሁም የአሰልጣኙን ፍላጎት መሰረት ያደረ መንገድን መከተል መርጠናል።”