ለዓለም ዋንጫ ማጣርያ ዛሬ ዝግጅታቸው የጀመሩት ዋልያዎቹ በዝግጅታቸው አራት ተጫዋቾች አልተገኙም።
አሰልጣኝ ገብረመድኀን ኃይሌን በዋና አሰልጣኝነት የሾመው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በቀጣይ ኅዳር ወር መጀመርያ ላይ ከሴራልዮን እና ቡርኪናፋሶ ጋር በሞሮኮ ሀገር ለሚያደርገው የዓለም ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታዎች በቅርቡ ለ30 ተጫዋቾች ጥሪ በማድረግ ዛሬ በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም የመጀመርያ ዝግጅቱን ጀምሯል።
26 ተጫዋቾች በዛሬው ልምምዳቸው የተገኙ ሲሆን አራት ተጫዋቾች በዝግጅቱ ላይ እንዳልተሳተፉ አረጋግጠናል። እነርሱም ጌታነህ ከበደ፣ ሽመልስ በቀለ፣ ጋቶች ፓኖም እና ጉዳት ላይ የቆየው አቡበከር ናስር መሆናቸውን አረጋግጠናል።
ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር ዝግጅት ያልገቡበትን ተጫዋቾች ምክንያት ምን እንደሆነ ለማወቅ ያደረግነው ጥረት ለጊዜው ባይሳካም በቅርቡ ብሔራዊ ቡድኑን ሊቀላቀሉ እንደሚችሉ ይጠበቃል።