ለዓለም ዋንጫ ማጣርያ ትላንት ዝግጅቱን ከጀመረው የዋልያዎቹ ስብስብ ውስጥ ሁለት ተጫዋቾች ከቡድኑ ውጭ መሆናቸው ታውቋል።
በአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ በሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በዓለም ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታዎች ለሰላሳ ተጫዋቾች ጥሪ ቀርቦላቸው ነበር። ጌታነህ ከበደ ራሱን ከብሔራዊ ቡድን ማግለሉን ተከትሎ ከስብስቡ ውጪ መሆኑ ሲረጋገጥ ሌሎቹ ሁለት ተጫዋቾች ከቡድኑ ስብስብ ውጭ መሆናቸው ታውቋል።
ከስብስቡ ውጪ ከሆኑት አንደኛው አጥቂው አቡበከር ናስር ሲሆን ምንም እንኳን ከህመሙ አገግሞ መጠነኛ ልምምድ ቢጀምርም ለቀጣዩ ሁለት ጨዋታዎች ለመድረስ የሚያስችል የአካል ብቃት ደረጃ ላይ የማይገኝ በመሆኑ ከቡድኑ ስብስብ ውጪ መደረጉ ተገልፆል።
ሌላው አማካይ ሽመልስ በቀለ ሲሆን በተመሳሳይ በሊጉ አምስተኛ ሳምንት መቻል ከሀንበሪቾ ጋር ባደረገው ጨዋታ በመጀመርያው አጋማሽ የጡንቻ መሳሳብ ጉዳት በማስተናገዱ ተቀይሮ መውጣቱ ይታወሳል። በአሁኑ ወቅት ከዚህ ህመም ብዙ ባለማገገሙ ምክንያት ከብሔራዊ ቡድን ስብስብ ውጪ የሆነ ሌላኛው ተጫዋች ሆኗል።
ዋልያዎቹ በዚህ ሰዓት 27 ተጫዋቾችን በመያዝ ሁለተኛ ቀን ልምምዳቸውን በአዳማ ዩኒቨርስቲ ሜዳ እየሰሩ ይገኛሉ። በቡድኑ ልምምድ ዙርያ የሚኖሩ አዳዲስ መረጃዎችን ከቆይታ በኋላ ይዘን የምንመለስ ይሆናል።