ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ዝግጅታቸውን በአዳማ ከተማ እያደረጉ ያሉት ዋልያዎቹ የከተማ ለውጥ ማድረጋቸው ታውቋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለዓለም ዋንጫ ማጣርያ ጨዋታ ወደ ሞሮኮ ከማቅናትቱ በፊት መቀመጫውን አዳማ ከተማ ላይ በማድረግ ዝግጅቱን ከጀመረ ሦስተኛ ቀኑን አስቆጥሯል። አስቀድሞ በካኖፔ ሆቴል ማረፊያውን ቢያደርግም በትናትናው ዕለት የሆቴል ለውጥ በማድረግ ሲምለስ ሆቴል ያረፈ ሲሆን አሁን ደግሞ የዝግጅት ከተማውን መቀየሩ ተሰምቷል።
ብሔራዊ ቡድኑ ሦስተኛ ቀን ልምምዱን ዛሬ በአዳማ ዩኒቨርስቲ ሜዳ ሰርቶ ያጠናቀቀ ሲሆን ባረፉበት ሆቴል ምሳ ከተመገቡ በኋላ ጉዞ ወደ አዲስ አበባ በማድረግ በጁፒተር ሆቴል አርፈው በመዲናዋ ቀሪ ዝግጅታቸውን የሚከውኑ ይሆናል።
ዋልያዎቹ ቅዳሜ አመሻሽ ላይ ወደ ሞሮኮ የሚያቀኑ ሲሆን የመጀመርያው ጨዋታቸውን ከሴራሊዮን ኅዳር 5 ፣ ሁለተኛው ጨዋታ ከቡርኪና ፋሶ ጋር ኅዳር 11 የሚደርጉ ይሆናል።