የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ሦስተኛ ሳምንት ዛሬ በስድስት ጨዋታዎች ሲጀምር በምድብ ‘ለ’ ሸገር ከተማ ፣ ካፋ ቡና እና የካ ክፍለ ከተማ ድል ሲቀናቸው የምድብ ‘ሀ’ ሦስት ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል።
የ04:00 ጨዋታዎች ውጤት
አዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ላይ በሣምንቱ የመጀመሪያ መርሐግብር ንብ እና ሞጆ ከተማ ሲገናኙ በመጀመሪያው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ ለመውሰድ ብርቱ ፉክክር ቢደረግበትም የግብ ዕድሎች ግን በሁለቱም በኩል አልተፈጠሩም ነበር። ከዕረፍት መልስ መሃል ሜዳው ላይ የነበረው ፍልሚያ በመጠኑ ቢቀዛቀዝም ሁለቱም ቡድኖች ወደ ግብ ለመድረስ የተሻለ ጥረት አድርገዋል። በተለይም በሞጆዎች በኩል 50ኛው ደቂቃ ላይ ኢዮብ ዓለሙ ከናትናኤል አሸናፊ በተሰጠነቀለት ኳስ ሳጥን ውስጥ ደርሶ ግብ ጠባቂው የመለሰበት እና 63ኛው ደቂቃ ላይም ብርሃኑ ወልቂቶ ከረጅም ርቀት ከቅጣት ምት ሞክሮት ግብ ጠባቂው ሶፎንያስ ሰይፈ በድጋሚ ያስወጣበት ኳስ በንቦች በኩል ደግሞ የጨዋታው መጠናቀቂያ ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው አብዱሀኪም ሱልጣን ከቀኙ የሳጥን ጠርዝ ላይ የዓየር ላይ ኳስ ሞክሮ ግብ ጠባቂው ታሪኩ አረደ የያዘበት ኳስ ተጠቃሽ ነበሩ። ሆኖም ቀዝቃዛው ጨዋታ በመጨረሻም ያለ ግብ ተጠናቋል።
በምድብ ‘ለ’ ማለዳ ላይ በተደረገው ጨዋታ ሸገር ከተማ ጋሞ ጨንቻን 2-0 መርታት ችሏል። አላዛር ሽመልስ እና ፋሲል አስማማው በመጀመሪያው አጋማሽ 9ኛ እና 16ኛ ደቂቃ ላይ ያስቆጠሯቸው ጎሎች ሸገርን ባለድል አድርገዋል።
የ08:00 ጨዋታዎች
በምድብ’ሀ’ በዕለቱ ሁለተኛ በነበረው የቤንች ማጂ ቡና እና ስልጤ ወራቤ ጨዋታ በሁለቱም ቡድኖች ጥሩ እና ፈጣን እንቅስቃሴ ተመልክተናል። ኳስን በመቆጣጠርና ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ በመድረስ ጫና ለመፍጠር ሲሞክር የነበረው ስልጤ ወራቤ ነበር። በአንፃሩ ቤንች ማጂ ቡናዎች ረጃጅም ኳስን በተደጋጋሚ በማዝወተር በመስመሮች በኩል የግብ ዕድል ለመፍጠር ጥረት አርገዋል። በ20ኛው ደቂቃ የስልጤ ወራቤው ተጫዋች ብሩክ ሰማ ላይ በተሰራው ጥፋት ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት ማቲያስ ኤሊያስ ወደ ግብ ማስቆጠር ችሏል። ከግቧ መቆጠር በኋላ ስልጤ ወራቤ ጠንካራ የመከላከል አጨዋወት እና ቤንች ማጂ ቡና ግብ ለማስቆጠር ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ችሏል።
ከዕረፍት በኋላ ተመጣጣኝ እና እልህ የተሞላበት አጨዋወት ተመልክተናል። ቤንች ማጂ ቡና በፍጥነት ወደ ግብ ለመድረስ እና የግብ ዕድል ለመፍጠር ረጃጅም ኳሶችን ተጠቅመው ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል። በአንፃሩ ስልጤ ወራቤ ኳስን ለመቆጣጠር እና ለጥንቃቄ ቅድሚያ በመስጠት ግብ ላለማስተናገድ ጥረት አርገዋል። ሆኖም ቤንች ማጂ ቡና የስልጤ ወራቤን የግብ ክልል ለመድፈር ብዙ ጊዜ አልፈጀበትም። በ58ኛው ደቂቃ ቤንች ማጂ ቡና ያገኘውን የማዕዘን ምት አብዱልአዚዝ አማን ያሻማውን ኳስ አብዲ ራመቶ ግብ አስቆጥሯል። በጨዋታው መጠናቀቂያ ላይ የቤንች ማጂ ቡና ተጫዋች የሆነው ዘላለም በየነ አሰቃቂ ጉዳት አስተናግዶ ጨዋታው ለተወሰነ ደቂቃ ተቋርጦ የህክምና እርዳታ ሲደረግለት እንደነበር ተስተውሏል። ይህንን ተከትሎ ተጫዋቹን በጉዳት ያጣው ቤንች ማጂ ቡና ተጫዋች ቀይሮ በመጨረሱ ጨዋታውን በጎዶሎ ተጫዋች ለመጨረስ ተገዷል። ጨዋታውም በአቻ ውጤት ተጠናቋል።
በሀዋሳ ሰው ሰራሽ ሜዳ የምድብ ‘ለ’ ጨዋታዎች ቀጥለው ሲካሄዱ ከሰዓት 08:00 ላይ ካፋ ቡና እና ወሎ ኮምቦልቻ ተገናኝተዋል። በጨዋታው ሙሉቀን ተሾመ 65ኛው ደቂቃ ላይ ያስቆጠራት ጎል ብቸኛዋ ልዩነት ፈጣሪ ሆና ካፋ ቡናን የ1-0 አሸናፊ አድርጋለች።
የ10:00 ጨዋታዎች
አዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ላይ የዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ ወልድያን ከኮልፌ ክፍለ ከተማ ያገናኘ ቢሆንም ብዙም ፉክክር እና ሳቢ ጨዋታ ያልታየበት አጋማሽ ተመልክተናል። ወልድያዎች የኮልፌን ፈጣን አጨዋወት ለመከላከል ጥንቃቄን መርጠው ሲጫወቱ ተስተውሏል። በአንፃሩ ኮልፌ ክፍለ ከተማዎች በረጃጅም ኳሶች እና በመስመር በኩል ባደላ መልኩ ለመጫወት ሲሞክሩ ተስተውሏል። ከ35ኛው ደቂቃ በኋላ በሁለቱም በኩል ጥሩ የሚባል እንቅስቃሴ የታየ ቢሆንም ምንም ዓይነት የግብ ሙከራ ሳንመለከት የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ከዕረፍት መልስ በሁለቱም ቡድኖች በኩል የተጫዋች ቅያሪ በማድረግ ግብ ለማስቆጠር ጥረት አድርገዋል። ሆኖም የቡድኖቹ ጠንካራ የተከላካይ መስመር ግብ እንዳይቆጠር አድርጓል። ጨዋታውም ያለ ምንም ግብ ለመጠናቀቅ ተገዷል።
ሀዋሳ ላይ የምድብ ‘ለ’ ማሳረጊያ ጨዋታ በአዲስ ከተማ እና የካ ክፍለ ከተሞች መካከል ተከናውኗል። በውጤቱም ሚኪያስ ታምራት 15ኛው እንዲሁም ጁንዴክስ አወቀ 46ኛው ደቂቃ ላይ ባስቆጠሯቸው ግቦች የካ 2-0 ማሸነፍ ችሏል።