የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ሦስተኛ ሣምንት ዛሬ በምድብ ‘ሀ’ በተደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ሲጠናቀቅ ነቀምቴ ከተማ ድል ቀንቶታል።
የ04፡00 ጨዋታ
በዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር ኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅን ከሀላባ ከተማ አገናኝቷል። ጥሩ እና ሳቢ እንቅስቃሴ ባስመለከተን ጨዋታ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ግብ ለማስቆጠር ከፍተኛ ጥረት ታይቷል። ይህንንም ተከትሎ 10ኛው ደቂቃ ላይ ኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ ያገኘውን የግብ ዕድል ኃይሌ ዘመድኩን ግብ ሲያስቆጥረው 13ኛው ደቂቃ ላይ ሀላባ ከተማ በፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ ወደ ኦሮሚያ የግብ ክልል ውስጥ ገብተው በተረራባቸው ጥፋት የተገኘውን የፍጹም ቅጣት ምት ፀጋ ከድር ወደ ግብነት ቀይሮታል። ከግቡ መቆጠር በኋላ ሀላባ ከተማዎች የበላይነት ወስደው ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ ተስተውሏል። በአንፃሩ ኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ ወደኋላ በማፈግፈግ በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ጥረት አርገዋል። 27ኛው ደቂቃ ላይም ሀላባ ከተማ ከመስመር በመነሳት አሸናፊ በቀለ ወደ ግብ የሞከረው ኳስ የግቡን አግዳሚ ገጭቶ ሲመለስ መስመር አልፏል ወይስ አላለፈም የሚለውን ውዝግብ የዕለቱ ዳኛ መስመር አላለፈም በማለት ጨዋታውን አስቀጥለውታል። በውሳኔውም የሀላባ ከተማ የአሰልጣኝ ቡድን አባላት ቅሬታቸውን አሰምተዋል። በአጋማሹም ሌላ ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ከዕረፍት መልስ ልክ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ከፍተኛ የሆነ የመሸናነፍ ፉክክር የተመለከትንበት አጋማሽ የነበር ሲሆን ኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ በፈጣን ሽግግር እና ረጃጅም ኳስ በመጠቀም በርካታ የግብ ዕድል ሲፈጥር ሀላባ ከተማ ስኬታማ የሆነ የኳስ ቅብብል በማድረግ እና መስርተው በመውጣት የግብ እድል ለመፍጠር ሲሞክሩ ተስተውሏል። 63ኛው ደቂቃ ላይም ሀላባ ከተማ በጥሩ ቅብብል ያገኘውን ኳስ ወሰን ጌታቸው በጥሩ ሁኔታ ወደ ግብ መቀየር ችሏል። ጨዋታውም በዚው ሁኔታ ቀጥሎ 86ኛው ደቂቃ ላይ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ ተጫዋች የሆነው ዳንኤል ዳርጌ ግብ አስቆጥሮ ጨዋታው 2-2 እንዲጠናቀቅ ማድረግ ችሏል።
የ07፡00 ጨዋታ
በሣምንቱ የመጨረሻ መርሐግብር ነቀምቴ ከተማ እና ጅማ አባ ቡና ተገናኝተዋል። በሁለቱም በኩል በፈጣን የማጥቃት ሽግግር ቶሎ ቶሎ ወደ ጎል የመድረስ ፍላጎት በታየበት የመጀመሪያ አጋማሽ ነቀምቴዎች ገና በ 3ኛው ደቂቃ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ኢብሳ በፍቃዱ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ሆኖ የቀነሰውን ኳስ ያገኘው ተመስገን ዱባ መረቡ ላይ አሳርፎታል። ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ በዘላለም አበበ አማካኝነት ሁለት ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ማድረግ የቻሉት አባ ቡናዎች 14ኛው ደቂቃ ላይ አቻ ሆነዋል። ግቧንም ወደ ቀኙ የሜዳ ክፍል ካጋደለ ቦታ ከሳጥኑ ጠርዝ ላይ ያሬድ መሐመድ በግሩም አጨራረስ ማስቆጠር ችሏል።
ከዕረፍት መልስ ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ ቢቀዘቅዝም በሁለቱም በኩል ማራኪ የሆኑ ስኬታማ ቅብብሎች ተደርገዋል። ሆኖም ጨዋታው በአቻ የተገባደደ ቢመስልም 83ኛው ደቂቃ ላይ የጅማው ያሬድ መሐመድ በቀኙ የሳጥን ክፍል ይዞት በገባው ኳስ ወርቃማ ዕድል ቢያገኝም ሳይጠቀምበት ሲቀር በአንድ ደቂቃ ልዩነት ነቀምቴዎች ግብ አስቆጥረዋል። ቦና ቦካ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ሆኖ ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ኢብሳ በፍቃዱ በግንባሩ በመግጨት መረቡ ላይ አሳርፎታል። ጨዋታውም በነቀምቴ ከተማ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።