በአራተኛው ሳምንት ከአሰልጣኙ ጋር የተለያየው ሻሸመኔ ከተማ አዲስ አሰልጣኝ ለመቅጠር መቃረቡን አውቀናል።
ከረዥም ዓመታት በኋላ ዘንድሮ ወደ ሊጉ የተመለሱት ሻሸመኔ ከተማዎች ከከፍተኛ ሊግ ካሳደገቸው አሰልጣኝ ፀጋዬ ወንድሙ ጋር መለያየታቸው ይታወሳል። ይህን ተከትሎ ቡድኑ ለአንድ ጨዋታ በጊዜያዊነት በምክትል አሰልጣኙ በቀለ እየተመራ የመጀመርያ አንድ ነጥቡን ማግኘት ችሎም ነበር።
ሆኖም ክለቡ በቋሚነት ዋና አሰልጣኝ ለመቅጠር የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ትናንት ከተለያዩ አሰልጣኞች ጋር ሲደራደር ቆይቶ በስተመጨረሻ በዛሬው ዕለት የክለቡ ቦርድ ከማለዳ ጀምሮ ከአሰልጣኝ ዘማርያም ጋር አብሮ ለመስራት ያደረገው ድርድር በስምምነት ተቋጭቷል። በዚህም መሰረት ነገ በፌዴሬሽን በመገኝት ውላቸውን በፊርማ የሚያረጋግጡ ሲሆን በአሁን ሰዓት አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደ ጊዮርጊስ በኢትዮጵያ ዋንጫ ሀዋሳ ከተማ ላይ ሻሸመኔ ከተማ ከከፋ ቡና ጋር የሚያደርጉትን ጨዋታ ለመከታተል ወደ ስፍራው እያቀኑ መሆኑን አውቀናል።
የአሰልጣኙን ይፋዊ ቅጥር አስመልክቶ ነገ ዝርዝር መረጃዎችን የምናደርስ ይሆናል።