ከጀመረ ሁለተኛ ሳምንቱን ባስቆጠረው የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ በመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች አዳማ ከተማ እና ቦሌ ክ/ከተማ ድል ሲያደርጉ አርባምንጭ ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ ነጥብ ተጋርተዋል።ረፋድ 4 ሰዓት ላይ አርባምንጭ ከተማ ከድሬዳዋ ጋር በተገናኙበት መርሃ ግብር የመጀመሪያ አጋማሽ ተሽሎ የተገኙት ድሬዳዋ ከተማዎች ገና ጨዋታ ከመጀመሩ በዘጠነኛው ደቂቃ ቃልኪዳን ጥላሁን በርቀት አክርራ የመታችው ኳስ ከመረብ ጋር ተገናኝተው መሪ መሆን ችለው ነበር።በመልሰው ማጥቃት ብዙ እድሎችን መጠቀም ያልቻሉት አርባምንጭ ከተማዎቹ በ35ኛው ደቂቃ በእርስ በእርስ ቅብብሎሽ ሰርካም ካሣ ባስቆጠረቺው ግቢ በአቻ ውጤት ወደመልበሻ ክፍል አምርተዋል።በሁለተኛው አጋማሽ አርባምንጭ ከተማዎች ጠንከር ብለው የገቡ ሲሆን በ61ኛው ደቂቃ ፎዚያ መሐመድ ከመስመር የተሻገራትን ኳስ በግንባር ገጭታ በማስቆጠር 2ለ1 መምራት እንድችሉ አድርጋለች።ብዙ ወደግብ ክልል የሚሄዱ ኳሶች በታዩት በዚህ ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማዎች መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ግዜ ሊጠናቀቅ 5 ደቂቃ ቀርቶ እያለ ያገኙትን ቅጣት ምት ቃልኪዳን ጥላሁን ወደግቢነት አስቀይራ ጨዋታው 2ለ2 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።ከሰዓት 8:00 በጀመረው በሁለተኛ ጨዋታ አዳማ ከተማን ከ ይርጋጨፌ ቡና ባደረጉት ጨዋታ በአዳማ ፍፁም የበላይነት የታየበት ጨዋታ ነበር። ከጅማረው ጥሩ እንቅስቃሴ ያደረጉት አዳማ ከተማዎች በ21ኛው ደቂቃ ሄለን እሸቱ ባስቆጠረችው ግቢ ቀዳሚ የሆኑ ሲሆን የመጀመሪያ አጋማሽ 1ለ0 በሆነ ውጤት መጠናቅ ችሎ ነበር።በሁለኛው አጋማሽ በ76ኛው ደቂቃ ርብቃ ጣሰው በአንድ ሁለት ቅብብሎሽ ባስቆጠረችው ግቢ አዳማ ከተማ 2ለ0 መምራት የቻሉ ሲሆን ይርጋጨፌ ቡና በበኩሉ የተቀዛቀዘ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ተመልክተናል። በ79ኛው እና በ89ኛው ደቂቃ በጨዋታው ጎልታ መታየት የቻለችው ሳባ ኃይለሚካኤል ባስቆጠረቻቸው ሁለት ግቦች አማካኝነት አዳማ ከተማ 4ለ0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል።በ10:00 ጨዋታ በሁለት አዲስ አበባ ክፍለ ከተሞች መሀከል በተደረገው ጨዋታ በቦሌ ክፍለ 3ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል።በመጀመሪያ አጋማሽ ሁለቱም ጥሩ ሆነው በገቡበት ጨዋታ 11ኛው ደቂቃ ትዕግስት ወርቁ ባስቆጠረቺው ቆንጆ ግብ ቦሌዎች መምራት ችለው ነበር።በ25ኛው ደቂቃ ከመስመር የተሻገረላትን ኳስ ህዳይት ካሡ ወደ ግብነት ቀይራ በአቻ ውጤት ወደመልበሻ ክፍል አምርተዋል።በሁለኛው አጋማሽ ቦሌ ክፍለከተማ ጨዋታውን በበላይነት ተቆጣጥረው የተጫወቱ ሲሆን ልደታ በአንፃሩ ትንሽ ተዳከመው ነበር።በ70 ደቂቃ ጤናዬ ሌታሞ ፍፁም ከመስመር የሸገረላት ኳስ ወደግብነት አስቀይራ ቦሌዎችን መምራት እንዲችሉ አድርጋለች። በ80ኛ ደቂቃ ደግሞ ከመስመር የተሻገረውን ኳስ ይዲዲያ አጫ አስቆጥራ ቦሌዎች ጨዋታውን በ3-1 የላይነት እንዲያጠናቅቁ ሆኗል።