በከፍተኛ ውጥረት በታጀበው ጨዋታ የጣና ሞገዶቹ የሊጉን መሪ ፈረሰኞቹን በመርታት ወደ ሰንጠረዡ አናት የተጠጉበትን ወሳኝ ድል ተቀዳጅተዋል።
ቅዱስ ጊዮርጊሶች ሊጉ ወደ ዕረፍት ከማምራቱ በፊት በመጨረሻ ጨዋታቸው ከተጠቀሙት የመጀመሪያ 11 ተጫዋቾች ውስጥ ሶስት ለውጦችን ሲያደርጉ በዚህም ብሩክ ታረቀኝ ፣ ሻሂዱ ሙስጠፋ እና ፍሪምፖንግ ክዋሜ አሳርፈው በምትካቸው አማኑኤል ተርፉ ፣ ረመዳን የሱፍ እና በረከት ወልዴን በምትካቸው ሲጠቀሙ በአንፃሩ ባህር ዳር ከተማዎች ደግሞ ባደረጉት ብቸኛ ለውጥ መሀል ሜዳ ላይ ፍሬው ሰለሞንን በአባይነህ ፊኖ ብቻ ተክተው ለጨዋታው ቀርበዋል።
በሁለቱም ቡድኖች በኩል ከፍ ባለ የማጥቃት ፍላጎት በጀመረው ጨዋታው ገና በ7ኛው ደቂቃ ላይ ግን የጨዋታው ሂደት የቀየረ አጋጣሚ ተፈጥሯል ፤ የቅዱስ ጊዮርጊሱ የፊት መስመር አጥቂ ሞሰስ አዶ ከኳስ ውጭ በተፈጠረ እሰጥአገባ መሳይ አገኘሁን በግንባር በመምታቱ የተነሳ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግዷል።
ቅዱስ ጊዮርጊሶች ምንም እንኳን ሜዳ ላይ በቁጥር ከተጋጣሚያቸው ቢያንሱም አጋማሹን እንደ ቡድን ከፍ ባለ ትጋት ተደራጅተው በመከላከል ሆነ በቀጥተኛ ቅብብሎች እንዲሁም አልፎ አልፎ ከተከላካዮች ጀርባ በሚጣሉ ኳሶች ይበልጥ አደገኛ ሆነው የተመለከትንበት ነበር።
በአንፃሩ ጨዋታውን ለመቆጣጠር የተቸገሩት ባህር ዳር ከተማዎች በ13ኛው እና በ21ኛው እንዲሁም በ29ኛው ደቂቃ ሀብታሙ ታደሰ ፣ ፍፁም ጥላሁን እና አለልኝ አዘነ ከሳጥን ውጭ ከሞከራቸው ኳሶች ውጭ የተደራጀውን የጊዮርጊስ የመከላከል መዋቅር ለማስከፈት ተቸገግረው ተመልክተናል። በ37ኛው ደቂቃ በቅዱስ ጊዮርጊሶች በኩል ተገኑ ተሾመ በደረሰበት ግጭት ተቀይሮ ለመውጣት ሲገደድ በምትኩ ጉዳት ላይ የሰነበተው ቢኒያም በላይ ተክቶት በመግባት በውድድር ዘመኑ የመጀመሪያ ጨዋታውን ማድረግ ችሏል።
በሂደት እየተቀዛቀዘ በመጣው ጨዋታ በ43ኛው ደቂቃ ቢኒያም በላይ ከማዕዘን ምት ያሻማውን ኳስ ነፃ አቋቋም ላይ ሆኖ የገጨው አማኑኤል ተርፉ ሳይጠቀምበት ቀረ እንጂ ፍፁም ያለቀለት አጋጣሚ ነበር።
የመጀመሪያ አጋማሽ ተጠናቆ በተጨመሩት አምስት ደቂቃዎች ውስጥ ባህር ዳር ከተማዎች ቀዳሚ የሆኑበትን ግብ አግኝተዋል። አባይነህ ፊኖ ከቀኝ የሳጥን ጠርዝ ወደ ውስጥ ያሻማውን ኳስ ሳጥን ውስጥ የተገኘው ፍራኦል መንግሥቱ በቀኝ እግሩ በግሩም ሁኔታ በማስቆጠር ባህር ዳሮች እየመሩ ወደ መልበሻ ቤት እንዲያመሩ አስችሏል።
በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ቅዱስ ጊዮርጊሶች የአቻነቷን ግብ ፍለጋ ጫና ፈጥረው በመጫወት ቢጀምሩም ባህር ዳር ከተማዎች ግን በ53ኛው ደቂቃ በፈጣን መልሶ ማጥቃት መሪነታቸውን አሳድገዋል። አባይነህ ፊኖ ያመቻቸለትን ኳስ ተጠቅሞ ቸርነት ጉግሳ የቀድሞ ክለቡ ላይ በቀላል አጨራረስ ግቧን አስቆጥሯል።
ከሁለተኛዋ ግብ በኋላ ባህር ዳር ከተማዎች በተሻለ ነፃነት ጨዋታውን መቆጣጠር የቻሉ ቢመስልም ቅዱስ ጊዮርጊሶች ግን አሁን ቢሆን ጫና ፈጥረው ለመጫወት ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ አስተውለናል።
በ75ኛው ደቂቃ በጨዋታው ሁለት ግብ የሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ ያቀበለው አባይነህ ፊኖ ከአለልኝ አዘነ የደረሰውን ኳስ አስቆጠረ ተብሎ ሲጠበቅ ሙከራውን አማኑኤል ተርፉ ተንሸራቶ ሊያድንበት ችሏል። በ79ኛው ደቂቃ ላይ ፈረሰኞቹ መሀል ሜዳ አካባቢ ካገኙት የቅጣት ምት ኳስ የተሻማውን ኳስ በጨዋታው ከፍተኛ ጥረትን ሲያሳይ የነበረው አማኑኤል ተርፉ በግንባር በመግጨት ለቡድኑ ተስፋ ልትፈነጥቅ የምትችል ግብ ማስቆጠር ቢችልም ከግቧ መቆጠር በኋላ በነበሩት ቀሪ የጨዋታ ደቂቃዎች ባህር ዳር ከተማዎች የጨዋታውን ሂደት ዝግ በማድረግ ከፍ ባለ ጥንቃቄ የተጫወቱ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊሶች ደግሞ የአቻነቷን ግብ ፍለጋ ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ ጨዋታው በባህር ዳር ከተማዎች 2ለ1 አሸናፊነት ሊጠናቀቅ ችሏል።
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በሁለቱ አሰልጣኞች በተሰጡ አስተያየቶች አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ በጎዶሎ ሰው በአመዛኙ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ለመጫወት የተገደዱት ተጫዋቾቹ ባሳዩት ጥረት ስለመኩራታቸው ተናግረው በዳኝነቱ ላይ ቅር ስለመሰኘታቸውም አልሸሸጉም በአንፃሩ አሰልጣኝ ደግዓረግ ይግዛው ደግሞ ከጠንካራ ተጋጣሚ ጋር ባደረጉት ጠንካራ ጨዋታ ትልቅ ድል በማሳካታቸው ደስተኛ ስለመሆናቸው ገለፀዋል።