አዳማ ከተማዎች የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ሽንፈት በቀመሱበት ጨዋታ መቻል ተከታታይ አራተኛ ጨዋታውን አሸንፏል።
መቻሎች መድንን አንድ ለባዶ ካሸነፈው ስብስብ በቀይ ካርድ ከሜዳ የወጣው ግሩም ሐጎስ በግርማ ዲሳሳ ተክተው ሲገቡ አዳማ ከተማዎች ደግሞ ኢትዮጵያ ቡናን ካሸነፈው ስብስባቸው አድናን ረሺድና አቡበከር ሻሚል በአህመድ ረሺድና ቻርለው ሪባና ተክተው ገብተዋል።
በጥቂት ሙከራዎችና በርካታ ጥፋቶች ታጅቦ የተካሄደው የመጀመርያው አጋማሽ በአዳማ ከተማዎች ብልጫ ቢጀምርም የኋላ ኋላ ግን ተመጣጣኝ የሆነ ፉክክር ታይቶበታል። በአጋማሹ አዳማ ከተማዎች የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ለመውሰድ ጥረት ስያደርጉ መቻሎች በበኩላቸው ከሁለቱም መስመሮች ወደ አጥቂዎች በሚሻገሩ ኳሶች የግብ ዕድል ለመፍጠር ጥረት አድርገዋል።
ሆኖም ሁለቱም ሊጠቀስ የሚችል ትልቅ የግብ ሙከራ አላስመለከቱም። በአዳማ ከተማ በኩል መስዑድ መሐመድ ከቅጣት ምት አሻግሯት ከግቡ አፋፍ የነበረው ዮሴፍ ታረቀኝ በግንባሩ ገጭቶ ወደ ውጭ ያወጣት ኳስ የተሻለ ለግብ የቀረበች ነበረች። በመቻል በኩልም ቺጂኦኪ ናምዲ በሁለት አጋጣሚዎች የሞከራቸው ሙከራዎች ይጠቀሳሉ። በተለይም ከግራ መስመር ተሻግሮለት በደካማ ውሳኔ አሰጣጥ ችግር ያልተጠቀመበት ኳስ የተሻለው ዕድል ነበር። መጀመርያው አጋማሽም የመቻሉ ግብ ጠባቂ ናፍያን አልዮንዚ አዳማ አማካዮች ከተከላካዮች ጀርባ ያለው ክፍት ቦታ ለመጠቀም ያደረጉት ጥረት በማክሸፍ ጥሩ ተንቀሳቅሷል።
ሁለቱም ቡድኖች ባደረጓቸው የተጫዋቾች ለውጥ የጀመረው ሁለተኛው አጋማሽ የተሻለ ፉክክር የታየበት ነበር። በተለይም ሽመልስ በቀለ እና ከነዓን ማርክነህ ቀይረው ያስገቡት መቻሎት ይበልጥ ተሻሽለው ቀርበዋል። ሆኖም በ48ኛው ደቂቃ ላይ አዳማዎች ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ከራሳቸው የግብ ክልል ፍቅሩ ዓለማየሁ በረጅሙ ያሻገረውን ኳስ ከሳጥኑ የቀኝ ጠርዝ ላይ የነበረው ቻርለስ ሪባኑ በግሩም የመጀመሪያ ንክኪ በአጋማሹ ተቀይሮ ለገባው ነቢል ኑሪ አቃብሎት ነቢልም ወደ ውስጥ ሲያሾልከው በተከላካይ የተጨረፈችውን ኳስ ያገኘው ቢኒያም ዓይተን የግብ ጠባቂውን አልዌንዚ ናፊያን እጅ ጥሳ የገባች ግብ አስቆጥሯል።
ከቅያሪዎቹ በኋላ በተሻለ አጥቅተው ለመጫወት የሞከሩት መቻሎች የመሀል ሜዳ ብልጫ ከማስመለስ አልፈው ሙከራዎች አድርገዋል። ሳሙኤል ሳሊሶ ከግራ መስመር በጥሩ መንገድ ወደ ሳጥን አሻምቷት መጀመርያ ምንይሉ ቀጥሎም ሽመልስ ወደ ግብነት ያልቀየሯት ኳስ መቻልን አቻ ለማድረግ ተቃርባ ነበር። በስልሣ ሦስተኛው ደቂቃ ላይም መቻሎች በሳሙኤል ሳሊሶ አማካኝነት ግብ አስቆጥረው አቻ ሆነዋል። ተጫዋቹ ሽመልስ በቀለ ከቅጣት ምት ያሻማው ኳስ በግንባሩ ገጭቶ በማስቆጠር ነበር ቡድኑን አቻ ያደረገው።
ከአምስት ደቂቃዎች በኋላም ተጨማሪ ግብ አስቆጥረው ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። የመጀመርያውን ግብ አመቻችቶ ያቀበለው ሽመልስ በቀለ በተጋጣሚ ሳጥን ጠርዝ ያገኛትን የቅጣት ምት ኳስ በቀጥታ በማስቆጠር ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል። ግቧም ከአስራ ሦስት ዓመታት በፊት ልክ በዚህ ሳምንት ዲሰምበር 2 በሴካፋ ዋንጫ ኬንያ ላይ ያስቆጠራት ግሩም የቅጣት ምት ግብ ተመሳሳይነት አላት። መቻሎች ከግቧ በኋላም በዩዳሄ አማካኝነት የግብ ልዩነቱን የሚያሰፉበት ዕድል አግኝተው ግብ ጠባቂው ሰይድ ሀብታሙ መልሶቸዋል።
እንደ መጀመርያው አጋማሽ ብልጫ መውሰድ ያልቻሉት አዳማዎች ጥቂት የጠራ የግብ ዕድል የፈጠሩባቸው አጋጣሚዎች ጥቂት ነበሩ። አሸናፊና ሀይደር ከቆመ ኳስ ያደረጓቸው ሙከራዎችም ይጠቀሳሉ።
ጨዋታው በመቻል አሸናፊነት መጠቀቁን ተከትሎ የሳምንቱ ቀሪ ጨዋታዎች እንዳሉ ሆነው ቡድኑ የሊጉን መሪ መሆን ችሏል፤ አዳማም የውድድር ዓመቱ የመጀመርያው ሽንፈት አስተናግዷል።
አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ ከጨዋታው በኋላ በሰጡት አስተያየት ጨዋታው ቀድመው እንደገመቱት ከባድ እንደ ነበር ገልፀው የገቡት የቆሙ ኳሶች በመከላከል ችግር እንደተቆጠሩ ገልፀዋል። አሰልጣኙ ጨምረውም ጨዋታው የመጀመርያው አጋማሽ ላይ አጠናቀው የሚወጡበት ዕድል እንደነበር ጠቅሰዋል። አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ በበኩላቸው እንደጠበቁት አይነት እንቅስቃሴ እንዳላዩ ገልፀው ግን መጥፎ የሚባል እንዳሆነ ተናግረዋል። አሰልጣኙ ጨምረውም በሁለተኛው አጋማሽ የተጋጣሚያቸው የአማካይ ክፍል ብልጫ መግታታቸው አሸናፊ እንዳደረጋቸው ገልፀዋል።