ሪፖርት | ሀዲያ እና መድን ነጥብ ተጋርተዋል

ምሽት ላይ በሀዲያ ሆሳዕና እና ኢትዮጵያ መድን መካከል የተደረገው የዕለቱ ብቸኛ መርሐግብር 1-1 ተጠናቋል።

ምሽት 12 ሰዓት ላይ በተጀመረው ጨዋታ መጠነኛ ፉክክር በተደረበት የመጀመሪያ አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ከራቃቸው ድል ጋር ለመታረቅ በመጓጓት ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ቢችሉም ባለመረጋጋታቸው በርካታ የጠሩ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲቸገሩ ተስተውሏል።

የጨዋታው የመጀመሪያ የተሻለ ሙከራ 14ኛው ደቂቃ ላይ በነብሮቹ አማካኝነት ሲደረግ ዳዋ ሆቴሳ ከራሳቸው የግብ ክልል በተሻገረ እና በተከላካዩ በርናንድ ኦቼንግ በተመለሰ ሁለተኛ ኳስ አክርሮ በመምታት ጥሩ ሙከራ ቢያደርግም በግቡ አግዳሚ በኩል ወጥቶበታል።


ከወትሮው በተለየ በ 4-4-2 አሰላለፍ ወደ ጨዋታው የቀረቡት መድኖች ያሬድ ካሳዬ ከግራ መስመር አሻምቶት ቹኩዌመካ ጎድሰን ባልተጠቀመበት ኳስ የተሻለውን የግብ ዕድል መፍጠር ቢችሉም ለግብ የቀረበ ብቸኛ ሙከራቸውን ግን 30ኛው ደቂቃ ላይ አድርገዋል። በዚህም ንጋቱ ገ/ሥላሴ ከረጅም ርቀት አክርሮ በመምታት ያደረገውን ግሩም ሙከራ ግብ ጠባቂው ያሬድ በቀለ አስወጥቶበታል።


በኳስ ቁጥጥሩ መጠነኛ ብልጫ ይወሰድባቸው እንጂ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በጥቂት ቅብብሎች በመግባት ግብ ፍለጋ መታተራቸውን የቀጠሉት ሀዲያዎች 36ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ብሩክ ማርቆስ ከራሱ የግብ ክልል በረጅሙ ያሻገረውን ኳስ በጥሩ ቦታ አያያዝ የተቆጣጠረው ዳዋ ሆቴሳ ከሳጥኑ አጠገብ አክርሮ በመምታት እጅግ ማራኪ ግብ አድርጎታል።

ከዕረፍት መልስ ያሬድ ዳርዛን ቀይረው በማስገባት እና አሰላለፋቸውን ወደ 4-3-3 በመቀየር በተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ የቀረቡት ኢትዮጵያ መድኖች 57ኛው ደቂቃ ላይ ተሳክቶላቸዋል። የሀዲያው ዳዋ ሆቴሳ ከቅጣም ምት ያደረገው ሙከራ በግቡ የግራ ቋሚ በኩል ሲወጣበት በፍጥነት ያስጀመሩትን እና በረጅሙ ያሻገሩትን ኳስ ያገኘው ቹኩዌመካ ጎደሰን ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ከዳዋ ሆቴሳ ጋር ተመሳሳይ ያላት ግብ ማስቆጠር ችሏል።


ብርቱ ፉክክር እየተደረገበት በቀጠለው ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች በፈጣን እና ረጃጅም ኳሶች የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት ሲያደርጉ በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ በመውሰድ በቁጥር በዝተው ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በተደጋጋሚ መግባት የቻሉት መድኖች 67ኛው ደቂቃ ላይም ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። ዋና ዳኛው ባሕሩ ተካ በኳስ ጥቅም ያስቀጠሉትን ጨዋታ ወገኔ ገዛኸኝ ለቹኩዌመካ ጎድሰን አቀብሎት ተከላካይ አታልሎ በማለፍ ከማቀበል አማራጭ ጋር ጥሩ ዕድል ያገኘው ጎድሰን ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ያሬድ በቀለ መልሶበታል።

ቀስ በቀስ በመጀመሪያው አጋማሽ ወደ ነበራቸው ጥሩ የማጥቃት እንቅስቃሴ የተመለሱት ነብሮቹ በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያውን ዒላማውን የጠበቀ ሙከራቸውን 74ኛው ደቂቃ ላይ ሲያደርጉ ግርማ በቀለ ተጭኖ የቀማው ኳስ ያገኘው ዳዋ ሆቴሳ ከሳጥን ውጪ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው አቡበከር ኑራ አስወጥቶበታል። አጥቂው ከሦስት ደቂቃዎች በኋላም ከቅጣት ምት ተጨማሪ ሙከራ አድርጎ በተመሳሳይ በግብ ጠባቂው ተመልሶበታል።


የመጨረሻዎቹ 15 ደቂቃዎች መጠነኛ ፉክክር ሲደረግባቸው 85ኛው ደቂቃ ላይ ሀዲያ ሆሳዕናዎች የጠራ የግብ ዕድል ፈጥረው ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። በረከት ወልደዮሐንስ በግሩም ሩጫ ወደ ሳጥኑ የቀኝ ጠርዝ በመድረስ ወደ ውስጥ ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ተቀይሮ የገባው የኋላሸት ሰለሞን ኳሱን ሙሉ በሙሉ ሳያገኘው ቀርቶ ዒላማውን ባልጠበቀ ሙከራ አባክኖታል። ሆኖም ጨዋታው 1-1 ተጠናቋል።

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የኢትዮጵያ መድኑ አሰልጣኝ ገብረመድን ኃይሌ ጨዋታውን ለማሸነፍ ጥረት እንዳደረጉ እና ከነበሩበት ሁኔታ አንጻር አንዱ ነጥብ በቂ እንደሆነ ሲናገሩ የሀዲያ ሆሳዕናው አሰልጣኝ ግርማ ታደሰ በበኩላቸው ተጋጣሚያቸው ኳስ ይዞ የሚጫወት ቡድን በመሆኑ ስህተታቸውን ለመጠቀም አስበው መግባታቸውን ገልጸው የተከላካዮቻቸው የቀደመ ጥንካሬ ዛሬ አለመኖሩን እና በስህተት ግብ ማስተናገዳቸውን ተናግረው ሦስት ነጥቡ ይገባቸው እንደነበር ጠቁመዋል።