ስምንተኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ነገ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ጅማሮውን ያደርጋል ፤ ጨዋታዎቹን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው ቀርበዋል።
ሀዋሳ ከተማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ
ፈረሰኞቹ ከመሪዎች ላለመራቅ፤ ኃይቆቹም ሦስተኛ ተከታታይ ጨዋታ ላለመሸነፍ የሚያደርጉት ፍልምያ የጨዋታ ሳምንቱ መክፈቻ ይሆናል።
ሽንፈት ሳያስተናግዱ ከቆዩ በኋላ በስድስተኛውና ሰባተኛው ሳምንት ላይ ተከታታይ ሽንፈት ያስተናገዱው ሀዋሳዎች ወደ ድል ለመመለስ ፈረሰኞቹን ይገጥማሉ። ኅልይቆቹ እስከ ቅርብ ሳምንታት የቡድኑ ዋነኛ የጀርባ አጥንት የነበረው የመከላከል አደረጃጀታቸው ጥንካሬ ማስቀጠል አልቻሉም። ባህር ዳር ከተማን በገጠሙበት የመጨረሻው ጨዋታ ላይም ይህ ችግር በሰፊው ታይቷል። በተለይም በጨዋታው የመጀመርያ አጋማሽ ላይ የተጋጣሚን የማጥቃት እንቅስቃሴ ለመመከት ሲቸገሩ ተስተውለዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ቡድኑ ለአራት ተከታታይ ጨዋታዎች ግቡን ሳያስደፍር ከወጣ በኋላ በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ብቻ አምስት ግቦች ማስተናገዱ የመከላከል አደረጃጀቱ መዳከም ማሳያ ነው። ኃይቆቹ የተከላካይ ክፍላቸው ጥንካሬ ማስመለስ ቀዳሚ ሥራቸው ይሆናል ተብሎ ይገመታል። ተጋጣምያቸው በሊጉ ከፍተኛ የግብ መጠን ያስቆጠረ ቡድን መሆኑም ሌላው ፈተናው ትልቅ የሚያደርገው ጉዳይ ነው። አሰልጣኝ ዘርዓይ ከተጠቀሰው ክፍተት በተጨማሪ የቡድኑ የማጥቃት ክፍል ላይ ማስተካከያ ማድረግም ይጠበቅባቸዋል። ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ሁለት ግቦች ብቻ ያስቆጠረው የአጥቂ ክፍልም ለውጦች እንደሚፈግ የባለፉት ሳምንታት እንቅስቃሴው ጠቋሚ ነው።
በመጨረሻው ጨዋታ ላይ በባህር ዳር ከተማ የሁለት ለአንድ ሽንፈት በማስተናገድ በውድድር ዓመቱ የመጀመሪያው ሽንፈታቸው ያስተናገዱት ፈረሰኞቹ ወደ ድል መንገድ ለመመለስ ኃይቆቹን ይገጥማሉ። በሊጉ ጠንካራ የአጥቂ ጥምረት ካላቸው ቡድኖች በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱት ጊዮርጊሶች በጨዋታ በአማካይ 2.3 ግቦች ያስቆጠረ ጥምረት አላቸው፤ ይህ ቁጥርም በሊጉ ቀዳሚ ያደርጋቸዋል።
በነገው ጨዋታም በሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች በአማካይ 2.5 ግቦች ካስተናገደው የሀዋሳው ተከላካይ ክፍል ትልቅ ፈተና ይጠብቃቸዋል ተብሎ ባይገመትም ከስድስት ጨዋታዎች በአንዱ ብቻ ግቡን ሳያስደፍር የወጣው የመከላከል አደረጃጀተው ላይ ግን ውስን ማስተካከያ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ለምን ቢባል የአሰልጣኝ ዘርአይ ሙሉ ቡድን ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ሁለት ግቦች ብቻ ቢያስቆጥርም
በእንቅስቃሴ ደረጃ ግን ዝቅተኛ ግምት የሚሰጠው ጥምረት አደለም።
በጨዋታው ሀዋሳዎች በጉዳትም ሆነ በቅጣትም የሚያጡት ተጫዋች የለም ፤ ጊዮርጊስም ቅጣት ላይ ካለው ሞሰስ አዶ ውጪ ሙሉ ቡድኑ በጥሩ ጤንነት ይገኛል።
ሁለቱ ቡድኖች ነገ ለ48ኛ ጊዜ ይገናኛሉ። በእስካሁኖቹ ጨዋታዎቻቸው 81 ግቦችን ያስቆጠሩት ቅዱስ ጊዮርጊሶች 28 ጊዜ ባለድል ሲሆኑ 35 ግቦች ያሏቸው ሀዋሳ ከተማዎች ደግሞ 7 ጊዜ አሸንፈዋል። ቀሪዎቹ 12 ጨዋታዎች ደግሞ ነጥብ በመጋራት ተጠናቀዋል።
ጨዋታውን በመሐል ዳኝነት ኢንተርናሽናል ዳኛ አሸብር ሰቦቃ ሲመራው ፣ ፋሲካ የኋላሸት እና ሙስጠፋ መኪ ረዳቶች ፣ ኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሠ አራተኛ ዳኛ በመሆን ተመድቧል።
ወልቂጤ ከተማ ከ መቻል
ተከታታይ ድሎች አስመዝግበው ደረጃቸውን ማሻሻል የቻሉት ቡድኖች የሚያገናኘውን ጨዋታ ምሽት 12:00 ላይ ይከናወናል።
በንግድ ባንክ የሁለት ለባዶ ሽንፈት ከገጠማቸው ወዲህ ባደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች ተከታታይ ድሎች ያስመዘገቡት ወልቂጤዎች ከወራጅ ቀጠናው ይበልጥ ለመራቅ ተከታታይ ድል ካስመዘገበው እና እስካሁን በሊግ ግንኙነታቸው ካልረቱት መቻል ጋር ይፋጠጣሉ። ሰራተኞቹ ባለፉት ጨዋታዎች ውስን የአጨዋወት ለውጥ አድርገዋል። ከዚህ ቀደም የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ለመውሰድ ሲታትር የተመለከትነው ቡድን ባለፉት ጨዋታዎች በውስን መልኩ ከቀጥተኛ ኳሶች ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት አድርጓል። በተለይም ሀምበርቾን ባሸነፉበት ጨዋታ የቡድኑ ለውጥ በጉልህ ታይቷል።
የአጨዋወቱ የጥራት ደረጃ ለመገምገም ጊዜው ገና ቢሆንም አሰልጣኝ ሙልጌታ ምህረት የቡድኑ ችግሮች ለመቅረፍ የሄደበት መንገድ ግን ያስወድሰዋል። በውጤት ረገድ ቡድኑ ያስመዘገበው ተከታታይ ድልም ሌላው ማሳያ ነው። ከዚህ በተጨማሪ እስከ አምስተኛ ሳምንት ባካሄዳቸው ጨዋታዎች በአንዱ ብቻ ግቡን ሳያስደፍር ወጥቶ የነበረው የተከላካይ ክፍል በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች ምንም ግብ ሳያስተናግድ በመውጣት መሻሻሎች አሳይቷል። በነገው ዕለትም በጥሩ የማሸነፍ ሥነ ልቦና ውስጥ ካለው መቻል የሚገጥመውን ፈተና መክቶ ከወራጅ ቀጠናው የመሸሽ የቤት ሥራ ይጠብቀዋል።
መቻሎች ተከታታይ አራት ጨዋታዎች ካሸነፉ በኋላ ደረጃቸውን ከማሻሻል አልፈው ከሊጉ መሪ ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ወደ አንድ ማጥበብ ችለዋል። ነገም መሪነቱን ለመረከብ ወይም ልዩነቱን አስጠብቆ ለመጓዝ አልመው ወደ ሜዳ ይገባሉ። መቻሎች በውጤት ረገድ የተሳካ ጊዜ በማሳለፍ ላይ ይገኛሉ። በእንቅስቃሴ ረገድ ግን ውስን የወጥነት ችግር ይታይባቸዋል። አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ በአማካዮቹ ጉዳት አስገዳጅነት የቡድኑ የማጥቃት አጨዋወት ይበልጥ ወደ መስመሮች እንዲዘነብል አድርገውት ቆይተዋል። አሁን ግን የአማካይ ጥምረቱ ወሳኝ ተጫዋቾች ከጉዳት መመለሳቸው ተከትሎ አጨዋወቱ ላይ ለውጦች ሊኖር የሚችልበት ዕድል የሰፋ ነው። ቡድኑም ከመስመሮች ይልቅ ወደ ቀደመ አማካዮቹ ላይ የተመሰረተ ፈጣን ሽግግር ሊመለስ ይችላል ተብሎ ይገመታል።
የመቻል ተከላካይ ክፍል ከሦስት ጨዋታዎች ቆይታ በኋላ ግብ ቢያስተናግድም አሁንም ጥንካሬውን እንደተላበሰ ነው። ቡድኑ በመጀመርያዎቹ ሁለት ጨዋታዎች አራት ግቦች ካስተናገደ ወዲህ ባደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች ሁለት ግቦች ብቻ ማስተናገዱ የጥንካሬው ውጤት ነው። በጨዋታው የጣት ስብራት ያጋጠመው ሙሃባ አደም እና በቀይ ካርድ ምክንያት ቅጣት ላይ የሚገኘው ግሩም ሐጎስ ከነገው ጨዋታ ውጪ ናቸው።
ወልቂጤ እና መቻል በሊጉ እስካሁን አራት ጊዜ ሲገናኙ ጦሩ ሁለቴ ድል አድርጎ ሁለት ጊዜ ነጥብ ተጋርተዋል። በጨዋታዎቹ መቻል ስድስት ወልቂጤ ደግሞ ሁለት ግቦች አስቆጥረዋል።
በመሐል ዳኝነት እያሱ ፈንቴ ፣ በረዳትነት ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ትግል ግዛው እና አሸብር ታፈሰ ፣ አራተኛ ዳኛ በመሆን ደግሞ ኃይለየሱስ ባዘዘው ተሰይመዋል።