የአሰልጣኞች አስተያየት | ሀዋሳ ከተማ 0-3 ቅዱስ ጊዮርጊስ

“ከዚህም በላይ ጎሎች መግባት ነበረባቸው” አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ

“ዕርምጃም እየወሰድን ጭምር ቡድናችንን ለማስተካከል እንሞክራለን” አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ

አቤል ያለው በመጀመሪያው አጋማሽ ባስቆጠራቸው ሦስት ጎሎች ቅዱስ ጊዮርጊስ ሀዋሳ ከተማን 3ለ0 ከረታበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ አሰልጣኞች ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታን አድርገዋል።


አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ስለ ጨዋታው ..?

“ጨዋታው በጣም ጥሩ ነበር። የፈለግነውን ነገር ሰርተን የመጣንበትን ነገር ተጫዋቾቼ ላይ አይቻለሁ በጣም ኮርቼባቸዋለሁ። ጥሩ እንቅስቃሴ ነበር በመጀመሪያው አጋማሽ ብዙ ነገሮችን አድርገን ከዚህም በላይ ጎሎች መግባት ነበረባቸው ፣ ማድረግ ያለብንን አድርገን ሦስት ለዜሮ አሸንፈናል ፣ በጣም ደስተኛ ነኝ።”

ከዕረፍት በፊት ጨዋታው ስለ ማለቁ እና በሁለተኛው አጋማሽ ስለ መቀዛቀዛቸው…?

“መቀዛቀዝ አይደለም ፣ ማድረግ ያለብንን አድርገናል። ፈርስት ሀፍ ብዙውን ነገር ስለጨረስን ተጫዋቾቼ በራሳቸው መጫወትን ነው የፈለጉት ፣ በዛውም ጥሩ ነገር ነበር። ሰከንድ ሀፍም ጥሩ ነገር ሰርተናል ጎሎች አልገቡም እንጂ ጨዋታው ላይ።”

አቤል እና ዳዊት በፈጠሩት ቅንጅት ሶለ ተቆጠሩት ጎሎች …?

“የአቤል እና የኦዚል መቀናጀት ብቻ አይደለም ፣ የቡድኑ መቀናጀት ነው። ትልቁ ፕሮሰሱ ከየት ነው የጀመረው ? ከየት መጣ ? ምን መደረግ ነበረበት ? ይህን ሰርተን ነው ያመጣነው። ለሁሉም ትልቅ ምስጋና አለኝ ከዚህም በላይ ማድረግ ይችላሉ። አቅም አላቸው ቅዱስ ጊዮርጊስን ማገልገል ይችላሉ እና አሁንም ወደፊትም በርቱ ይሄንን አጠናክረው እንዲያደርጉ ነው የማደርገው።”


አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ – ሀዋሳ ከተማ

ስለ ጨዋታው …?

“እስከ አሁን ካደረግነው ቡድናችን ጥሩ ያልነበረበት ብዬ ገልፀዋለሁ ፣ በተለይ የመጀመሪያ አርባ አምስት ደቂቃ። ይሄ ሦስተኛ ጨዋታችን ነው ስንሸነፍ በሦስቱም ጨዋታ የማየው የምነሳው ከዕረፍት በኋላ ጎሎች ከገቡ በኋላ ነው። በልምምድ ለማረም ሞክረናል ፣ ተነጋግረናል ግን ተመሳሳይ ስህተቶቸ ናቸው እየተሰሩ ያሉት ከዚህ በኋላ ተደጋጋሚ አንዳንድ ሰዎች ስህተት የሚሰሩ ከሆነ ያለው ዕድል ሌላ አማራጮችን መጠቀም ነው። ስለዚህ ዕርምጃም እየወሰድን ጭምር ቡድናችንን ለማስተካከል እንሞክራለን። ደስተኛ አይደለሁም በዛሬው እንቅስቃሴ በፍፁም።”

በሁለተኛው አጋማሽ ስለ ተደረጉት የሦስት ተጫዋቾች ቅያሪ ፣ በሁለተኛው አጋማሽ ሶላደረጉት እንቅስቃሴ …?

“መጀመሪያ የጊዮርጊስ ቡድን ረጃጅም ኳሶችን ስለሚጫወት ቆመው የሚጫወቱ ተከላካዮችን ፈልገን ነበር። ይሄንንም ያደረግነው በተደጋጋሚ ከዕረፍት በፊት እየጣልን ስለሆነ ጥንቃቄን መርጠን ነበር የጀመርነው ግን በተቃራኒው ነው የሆነው ፣ ከዕረፍት በኋላ ግን አንድ ለአንድ ተከላካዮቹ እንዲያሸንፉ ነው ያደረግነው እና ያንን ነገር አድርገዋል ብዙ ኳሶችንም አምክነናል ብዙ ደርሰናል። ግን ቡድኑን ያወረደው መጀመሪያ የገቡት ኳሶች ናቸው ቢያንስ ያ ባይሆን ኖሮ በምናገኘው አጋጣሚ መጠቀም ይቻላል። ከዕረፍት በኋላ በሰፊው እንነሳለን ከዕረፍት በፊት ግን በጣም ተራ ስህተት በቃ እኛ ጠንካራ ተከላካዮች አለን እያልን ነው ግን በግል እንጂ በግሩፕ የሚሰሩት ስራ መታረም አለበት ብዬ አስባለሁ። ከሆነ በኋላ ነው እየተነሳን ያለነው ትርጉም የሌለው ነው ይሄ ደግሞ ስለዚህ ቀጣይ እንዴት እንደምናስተካክል በሰፊው አውርተን ዕርምጃዎችንም እየወሰድን ጭምር ቡድኑን ለማስተካከል ጥረት እናደርጋለን።”