ምሽት ላይ በተደረገው ጨዋታ መቻሎች በከነዓን ማርክነህ እና ቺጂኦኬ ናምዲ ግቦች ወልቂጤ ከተማን 2-0 ረተዋል።
በዕለቱ ሁለተኛ መርሐግብር ወልቂጤ ከተማ እና መቻል ሲገናኙ ሠራተኞቹ በሰባተኛው ሣምንት ሀምበሪቾን 1-0 ከረቱበት አሰላለፍ የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ ሄኖክ ኢሳይያስ እና ዳንኤል ደምሱ በበቃሉ ገነነ እና ጋዲሳ መብራቴ ተተክተው ገብተዋል። መቻሎችም አዳማን 2-1 ሲያሸንፉ ከተጠቀሙት አሰላለፍ በተመሳሳይ የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገዋል። በዚህም ከነዓን ማርክነህ እና ሽመልስ በቀለ በአቤል ነጋሽ እና ቺጂኦኬ ናምዲ ተተክተው ጀምረዋል።
ምሽት 12፡00 ሰዓት ላይ በተጀመረው ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ 20 ደቂቃዎች መቻሎች የተሻለ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ መውሰድ ሲችሉ ወልቂጤዎች በአንጻሩ ወደ ራሳቸው የግብ ክልል በመጠጋት እና በመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ኳሶችን ወደ ስንታየሁ መንግሥቱ በማድረስ ለመጫወት ጥረት ሲያደርጉ ቢስተዋልም በሁለቱም በኩል የጠሩ የግብ ዕድሎች አልተፈጠሩም ነበር።
የጨዋታው የመጀመሪያ ለግብ የቀረበ ሙከራ 34ኛው ደቂቃ ላይ በመቻሎች አማካኝነት ሲደረግ ሽመልስ በቀለ ከግራ መስመር በቀኝ እግሩ ወደ ቀኙ የግቡ ቋሚ በኩል ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ፋሪስ አለው አስወጥቶበታል። በቀሪ ደቂቃዎችም በሁለቱም በኩል ተጠቃሽ የማጥቃት እንቅስቃሴ ሳይደረግበት ጨዋታው ያለ ግብ ወደ ዕረፍት አምርቷል።
ከዕረፍት መልስም ጨዋታው በተመሳሳይ ሂደት ሲቀጥል 53ኛው ደቂቃ ላይ ሽመልስ በቀለ ለከነዓን ማርክነህ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ከነዓን በውሳኔ መዘግየት ሲያመነታ ወንድማገኝ ማዕረግ ተደርቦ ያገደበት ኳስ በመቻሎች በኩል አስቆጪ አጋጣሚ ነበር።
ደቂቃዎች በሄዱ ቁጥር ጥሩ የመከላከል አደረጃጀት የነበራቸው ወልቂጤዎች ውጤቱን አስጠብቀው አንድ ነጥብ ለማግኘት ጥረት ሲያደርጉ የታየ ሲሆን በሚያገኙት ኳስ ሁሉ ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ ለማድረግ የሚሞክሩት መቻሎችም ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ ውጤታማ መሆን ሲቸገሩ ተስተውሏል።
ጨዋታው 80ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ ግብ ተቆጥሮበታል። በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በቁጥር በመብዛት መድረስ የቻሉት መቻሎች በመጨረሻም ተሳክቶላቸዋል። ምንይሉ ወንድሙ በቀኝ መስመር ከቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ከነዓን ማርክነህ በግሩም አጨራረስ በግንባሩ ገጭቶ መሬት ላይ በማንጠር ግብ አድርጎታል።
ወልቂጤ ከተማዎች ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ በተለይም ከሄኖክ ኢሳይያስ በሚነሱ ኳሶች የአቻነት ግብ ፍለጋ መታተራቸውን ቢቀጥሉም ሳይሳካላቸው ቀርቶ በመቻል በኩል ተቀይሮ የገባው ቺጂኦኬ ናምዲም 90+5ኛው ደቂቃ ላይ ተጨማሪ ግብ አስቆጥሮ ጨዋታው በመቻል 2-0 አሸናፊነት እንዲጠናቀቅ አስችሏል። ውጤቱም መቻልን የኢትዮጵያ ዋንጫ ጨዋታን ጨምሮ ለተከታታይ አምስተኛ ጊዜ ድል እንዲቀዳጅ ያስቻለ ሆኗል።