ሀድያ ሆሳዕና ፋሲል ከነማን ሁለት ለአንድ በማሸነፍ የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ድላቸው አስመዝግቧል።
ሀድያዎች አቻ ከተለያየው ስብስብ ያሬድ በቀለ፣ ዳግም ንጉሴ፣ ካሌብ በየነ፣ በረከት ወልደዮሐንስ፣ ቴዎድሮስ ታፈሰ፣ ፀጋአብ ግዛውና ዳዋ ሆቴሳ በታፔ አልዛየር፣ ቃልአብ ውብሸት፣ አስጨናቂ ፀጋዬ፣ መለሰ ሚሻሞ፣ ሳሙኤል ዮሐንስ፣ ደስታ ዋሚሾና ሰመረ ሀፍታይ ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል።
ዐፄዎቹ በበኩላቸው በወላይታ ድቻ ሽንፈት ከገጠመው ስብስብ ኤልያስ ማሞና ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ በይሁን እንደሻውና አማኑኤል ገብረሚካኤል ተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል።
ብዙም ማራኪ ባልነበረው የመጀመርያው አጋማሽ በጣም ጥቂት የግብ ሙከራዎች እና በርከት ያሉ ጥፋቶች የተመለከትንበት ነበር። በአጋማሹ በሁሉም ረገድ ብልጫ የወሰዱት ዐፄዎቹ ወደ ሳጥኑ ተጠግቶና በቁጥር በዝቶ ለመከላከል የመረጠውን ጠጣሩ የሀድያ ሆሳዕና ተከላካይ ክፍል አልፈው የግብ ዕድሎች መፍጠር አልቻሉም።
ሱራፌል ዳኛቸው ከቆመ ኳስ አክርሮ መቷት ግብጠባቂው እንደምንም ወደ ውጭ ያወጣት ኳስም በአጋማሹ የታየች ብቸኛ ለግብ የቀረበች ሙከራ ነበረች። በጨዋታው ጅማሮ ላይ በረዣዥም ኳሶች ዕድሎች ለመፍጠር ጥረት ያደረጉት ሀድያዎችም ከውስን ጥረቶች በኋላ ፊታቸውን ወደ መከላከሉ ለማዞር መርጠዋል፤ በዚህ የተነሳ በአጋማሹ ይህ ነው የሚባል የግብ ዕድል አልፈጠሩም። ሆኖም ከኳስ ውጭ የነበራቸው ጥቅጥቅ ብሎ የመከላከል ጥንካሬ የአጋማሹ የቡድኑ ጥንካሬ ነበር።
ከመጀመርያው አጋማሽ የተሻለ እንቅስቃሴና ፉክክር የታየበት ሁለተኛው አጋማሽ በተመሳሳይ የዐፄዎቹ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የታየበት ነበር፤ ሆኖም ግብ በማስቆጠር ቅድምያ የያዙት በመጀመርያው አጋማሽ ዝቅተኛ የማጥቃት ፍላጎት የነበራቸው ሀዲያ ሆሳዕናዎች ነበሩ።
ሁለተኛው አጋማሽ በተጀመረ በአንድ ደቂቃ ውስጥም በፈጣን የማጥቃት ሽግግር ግብ አስቆጥረዋል። ግቡንም ተመስገን ብርሃኑ በሳጥኑ የቀኝ ጠርዝ እየገፋ የወሰደውን ኳስ በግሩም አጨራረስ የግቡን የግራ ቋሚ ገጭቶ መረቡ ላይ እንዲያርፍ አድርጎታል።
ነብሮቹ ከአምስት ደቂቃዎች በኋላም ጨዋታውን በሁለት ግቦች ልዩነት የሚመሩበት ዕድል አግኝተዋል፤ ሳሙኤል ዮሐንስ ከመአዝን ያሻገራት ኳስ በጨዋታው ጥሩ እንቅስቃሴ ያደረገው ግርማ በቀለ በጥሩ ቅልጥፍና አስቆጥሮ የቡድኑ መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችሏል።
እንደወሰዱት የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የግብ ዕድሎች መፍጠር ያልቻሉት ፋሲሎች በሁለተኛው አጋማሽም ጠጣሩን የመከላከል አደረጃጀት አልፈው በርከት ያሉ ሙከራዎች ማድረግ አልቻሉም። ከቆሙ ኳስ የተደረጉ የግብ ማግባት ሙከራዎች የተሻሉ ነበሩ፤ በተለይም ጌታነህ ከበደ ከቅጣት ምት ሞክሯት ታፔ ያወጣት ኳስ የተሻለች ነበረች። ከዚህ በተጨማሪ ናትናኤል አሻምቷት ከተከላካዮች ጀርባ የነበረው አለምብርሀን ይግዛው በግንባር ያደረጋት ሙከራም ተጠቃሽ ነች። በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በተሻለ ድፍረት ለማጥቃት የመረጡት ፋሲሎች በሰማንያ ሰባተኛው ደቂቃ ላይ የግብ ልዩነቱን ያጠበቡበት ግብ አግኝተዋል። ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ ወደ ግራው የሜዳ ክፍል ካጋደለ ቦታ ላይ ሳጥን ውስጥ ለነበረው ፍቃዱ ዓለሙ አሻግሮለት አጥቂው ኳሱን በጥቂት ንክኪ ግብ ጠባቂው ትኩረት ባጣበት ቅፅበት ግብ እንዲሆን አድርጎታል።
ፋሲሎች ከግቡ በኋላም ተጨማሪ ጎሎች ለማግኘት ጥረት ቢያደርጉም በሀድያ ተከላካዮችና ግብ ጠባቂው ጥረት ከሽፈዋል። ይህንን ተከትሎም ሀድያዎች የውድድር ዓመቱ የመጀመርያ ድላቸው አስመዝግበዋል።