ምሽት ላይ በተደረገው ጨዋታ ባህር ዳር ከተማ ድሬዳዋ ከተማን 2-1 በማሸነፍ ወደ መሪዎቹ የተጠጋበትን ድል አስመዝግቧል።
ምሽት ላይ ድሬዳዋ ከተማ እና ባህርዳር ከተማ ሲገናኙ ብርቱካናማዎቹ በሰባተኛው ሣምንት ሲዳማ ቡናን 2-0 ሲያሸንፉ ከተጠቀሙት አሰላለፍ የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገዋል። በዚህም ሄኖክ አንጃው እና ዘርዓይ ገ/ሥላሴ በያሬድ ታደሰ እና በተመስገን ደረሰ ተተክተው ገብተዋል። በተመሣሣይ ሣምንት ሀዋሳ ከተማን 2-1 ባሸነፉት የጣና ሞገዶቹ በኩል ደግሞ ፍሬው ሰለሞን በሀብታሙ ታደሰ ምትክ ጨዋታውን ጀምሯል።
በመጀመሪያዎቹ 30 ደቂቃዎች በኳስ ቁጥጥሩም ይሁን በማጥቃት እንቅስቃሴው በኩል ብልጫ የነበራቸው የጣና ሞገዶቹ በተደጋጋሚ ጊዜ ወደ ተጋጣሚ የግብ ሳጥን ቢደርሱም የጠሩ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ግን ሲቸገሩ ተስተውሏል። ሆኖም ግን 10ኛው ደቂቃ ላይ ፍራኦል መንግሥቱ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ፍጹም ጥላሁን ዓየር ላይ እንዳለ በተረከዙ ያደረገው ሙከራ በግቡ አግዳሚ በኩል ወጥቶበታል።
ጨዋታው 33ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ የባህርዳር ከተማ ጥረት ፍሬ አፍርቶ ግብ ተቆጥሯል። በግሩም ቅብብል ከራሳቸው የግብ ክልል የወሰዱትን ኳስ በመጨረሻም አለልኝ አዘነ በረጅሙ በግራ መስመር ለነበረው ፍራኦል መንግሥቱ ሲያቀብለው በሳጥኑ የግራ ክፍል የገባው የመስመር ተከላካዩ ለማሻማት በሚመስል መልኩ ያሻገረው ኳስ የግብ ጠባቂው ዳንኤል ተሾመ መዘናጋት ተጨምሮበት መረቡ ላይ አርፏል።
ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ በመጠኑ የተነቃቁት ድሬዳዋ ከተማዎች 42ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን በተሻማ እና ፍሬዘር ካሳ በግንባሩ ገጭቶት በግቡ የግራ ቋሚ በኩል በወጣበት ኳስ ተጨማሪ ግብ ለማስተናገድ ተቃርበው የነበሩ ቢሆንም በአንድ ደቂቃ ልዩነት ግን የአቻነት ግብ አስቆጥረዋል። ሄኖክ አንጃው መሃል ሜዳ ላይ ከተገኘ የቅጣት ምት ወደ ሳጥኑ ያሻገረውን ኳስ ያሬድ ባዬህ በግንባሩ ገጭቶ ለግብ ጠባቂው ለማቀበል ሲሞክር በተፈጠረ አለመግባባት ኳሱ የራሱ መረብ ላይ አርፏል።
ከዕረፍት መልስ ጨዋታው በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ ለመውሰድ ብርቱ ፉክክር ቢደረግበትም የግብ ዕድሎች ግን በሁለቱም በኩል አልተፈጠሩም ነበር። በጣና ሞገዶቹ በኩል 59ኛው ደቂቃ ላይ ፍሬው ሰለሞን ከቅጣት ምት ሞክሮት በግቡ አግዳሚ በኩል የወጣበት በብርካናማዎቹ በኩል ደግሞ 63ኛው ደቂቃ ላይ ቻርለስ ሙሴጌ ከሳጥን ውጪ በግራ እግሩ ሞክሮት ግብ ጠባቂው ፔፔ ሰይዶ በቀላሉ የያዘበት ኳስ የተሻሉት ሙከራዎች ነበሩ።
ዕረፍት የለሽ በሆነ እንቅስቃሴ ለተመልካች ማራኪ ሆኖ በቀጠለው ጨዋታ በማጥቃት እንቅስቃሴያቸው እየተቀዛቀዙ የሄዱት ባህርዳሮች 69ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። ቸርነት ጉግሣ በሳጥኑ የግራ ክፍል አስደናቂ በሆነ ክህሎት ኢያሱ ለገሠን አታልሎ በማለፍ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ዳንኤል ተሾመ አስወጥቶበታል።
ዳዊት እስጢፋኖስን እና ሙኸዲን ሙሳን ቀይረው በማስገባት በማጥቃት እንቅስቃሴያቸው ላይ ነፍስ መዝራት የቻሉት ድሬዎች 85ኛው ደቂቃ ላይ እጅግ ወርቃማ የግብ ዕድል ፈጥረው ነበር። ዳዊት እስጢፋኖስ በግሩም ዕይታ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ለማስቆጠር ምቹ ቦታ ላይ ሀኖ ያገኘው ቻርለስ ሙሴጌ እጅግ ደካማ በሆነ የመጀመሪያ ንክኪ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።
ጨዋታው በዚሁ ውጤት ለመጠናቀቅ የተቃረበ ቢመስልም 90ኛው ደቂቃ ላይ የጣና ሞገዶቹ የማሸነፊያ ግብ አስቆጥረዋል። ኢያሱ ለገሠ በሳጥኑ የግራ ክፍል ኳስ ይዞ በሚገባው ቸርነት ጉግሣ ላይ በሠራው ጥፋት የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት ራሱ መረብ ላይ ግብ አስቆጥሮ የነበረው ያሬድ ባዬህ በተረጋጋ ሁኔታ ግብ ጠባቂው ዳንኤል ተሾመ እንደቆመ በግቡ የቀኝ ክፍል መረቡ ላይ አሳርፎታል። በዚህም ጨዋታው በባህርዳር ከተማ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የድሬዳዋ ከተማው አሰልጣኝ አሥራት አባተ በሁለተኛው አጋማሽ ተጭነው ለመጫወት መሞከራቸውን ገልጸው ያደረጓቸው ቅያሪዎች ውጤታማ እንደነበሩ በመናገር ያገኙትን የግብ ዕድል ባለመጠቀማቸው ለሽንፈት መዳረጋቸውን ጠቁመዋል። ድል የቀናቸው የባህር ዳር ከተማው አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው በበኩላቸው በሚፈልጉት መንገድ መንቀሳቀሳቸውን ጠቁመው በተጫዋቾቻቸው ላይ ያዩትን ተነሳሽነት አድንቀዋል።