ሪፖርት | ሻሸመኔ እና አዳማ ነጥብ ተጋርተዋል

የሣምንቱ ብቸኛ የአቻ ውጤት በተመዘገበበት የምሽቱ መርሐግብር ሻሸመኔ እና አዳማ 1-1 ተለያይተዋል።

በሣምንቱ የመጨረሻ መርሐግብር ሻሸመኔ እና አዳማ ሲገናኙ ሻሸመኔዎች በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 2-1 ሲሸነፉ ከተጠቀሙት አሰላለፍ የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገዋል በዚህም  አቤል ማሞ እና ማይክል ኔልሰን በኬን ሳይዲ እና ጌታለም ማሙየ ተተክተው ገብተዋል። አዳማዎች በአንጻሩ በመቻል 2ለ1 ሲሸነፉ ከተጠቀሙት አሰላለፍ በሱራፌል ዐወል ምትክ ነቢል ኑሪን አስገብተው ለጨዋታው ቀርበዋል።

በመጀመሪያዎቹ 30 ደቂቃዎች በኳስ ቁጥጥሩ የአዳማ ከተማ ፍጹም የበላይነት የታየበት ሲሆን የግብ ዕድሎች ግን በሁለቱም በኩል አልተፈጠሩም ነበር። በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ የተወሰደባቸው ሻሸመኔዎችም በሚያገኙት ኳስ ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ ለማድረግ ሲሞክሩ ተስተውሏል።

ጨዋታው 34ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ በመጀመሪያው ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ግብ ተቆጥሮበታል። መስዑድ መሐመድ ከረጅም ርቀት ከተገኘ የቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ዮሴፍ ታረቀኝ በግንባሩ በመግጨት ግብ አድርጎት አዳማ ከተማን መሪ ማድረግ ችሏል።

ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ በማራኪ የማጥቃት እንቅስቃሴ በርካታ የግብ ዕድሎችን የፈጠሩት ሻሸመኔዎች 45ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። አለን ካይዋ በነጠረ ኳስ በግራ እግሩ ከረጅም ርቀት ያደረገውን ግሩም ሙከራ ግብ ጠባቂው ሰዒድ ሀብታሙ አስወጥቶበታል።

ይበልጥ እየተጋጋሉ በመሄድ ተጭነው መጫወታቸውን የቀጠሉት ሻሸመኔዎች አጋማሹ ሊጠናቀቅ በተጨመሩ ደቂቃዎች ውስጥም ሁለት ጥሩ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ችለዋል። በቅድሚያም 45+2′ ላይ አሸናፊ ጥሩነህ ከግራ መስመር ከማዕዘን ያሻገረው ኳስ የቻላቸው መንበሩን ጉልበት ነክቶ አደገኛ ኳስ ሆኖ ቢሄድም በግቡ የግራ ቋሚ ሲመለስ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላም አሸናፊ ጥሩነህ ከቀኝ መስመር ከቻላቸው መንበሩ የተሻገረለትን ኳስ ገጭቶ ለማስቆጠር ነጻ ቦታ ላይ ቢገኝም ዒላማውን ባልጠበቀ ሙከራ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ተሻሽሎ ቀጥሎ የመጀመሪያው የግብ ዕድል 53ኛው ደቂቃ ላይ በአዳማዎች አማካኝነት ሲፈጠር ጀሚል ያዕቆብ ከፈጣን የማጥቃት ሽግግር የተገኘውን ኳስ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ሆኖ ወደ ውስጥ ለቢኒያም ዓይተን ለማሻገር ሲሞክር ተከላካዩ ምንተስኖት ከበደ በጥሩ ቦታ አያያዝ አቋርጦበታል።

 

ወደ ዕረፍት ከማምራታቸው በፊት የነበራቸውን በፈጣን ሽግግር የማጥቃት እንቅስቃሴ ያስቀጠሉት ሻሸመኔዎች 57ኛው ደቂቃ ላይ የአቻነት ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ነበር። ከሀይደር ሸረፋ ተጭነው የቀሙትን ኳስ ያገኘው ሀብታሙ ንጉሤ ተረጋግቶ ያደረገውን ሙከራ የግቡ የቀኝ ቋሚ መልሶበታል።

አዳማዎች የነበራቸው የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ተወስዶባቸው የተጋጣሚያቸውን የማጥቃት እንቅስቃሴ ወደ ራሳቸው የግብ ክልል ተጠግተው ለመመከት ሲገደዱ 73ኛው ደቂቃ ላይም ግብ ሊያስተናግዱ ነበር። ቻላቸው መንበሩ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው አሸናፊ ጥሩነህ በግንባሩ ገጭቶ ያደረገው ሙከራ ለጥቂት ወጥቶበታል።

ከወትሮው በተለየ ረፍት የለሽ የሆነ እንቅስቃሴ በማድረግ ተደጋጋሚ የማጥቃት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የነበሩት ሻሸመኔዎች 83ኛው ደቂቃ ላይ ተሳክቶላቸዋል በአሸናፊ ጥሩነህ ከግራ መስመር ከማዕዘን የተሻማውን ኳስ ከአንድ ንክኪ በኋላ ያገኘው ተቀይሮ የገባው ሙሉቀን ታሪኩ መረቡ ላይ አሳርፎታል። ይህም የተሻለው የመጨረሻ ትዕይንት ሆኖ ጨዋታው 1-1 ተጠናቋል።

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች በአጨራረስ ዙሪያ ከፊት ያለው የቡድኑ ግንባታ በሂደት ላይ መሆኑን የተናገሩት የሻሸመኔ ከተማው አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ የቡድናቸውን የጨዋታ ፍላጎት እና ተነሳሽነት አድንቀው ውጤቱ ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል። የአዳማ ከተማው አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ በበኩላቸው በአጨዋወት ደረጃ ትዕግስት ማድረግ እንዳለባቸው ተነጋግረው ቢገቡም ሁለተኛው አጋማሽ ላይ እንዳሰቡት እንዳልሄደላቸው አንስተው የአጥቂዎቻቸው አፈፃፀም በሂደት እንደሚሻሻል አንስተዋል።