የኢትዮጵያ ዋንጫ ሦስተኛ ዙር ጨዋታዎች ዛሬ ሲጠናቀቁ ወደ ሩብ ፍጻሜው የተቀላቀሉ ስምንት ቡድኖች ሙሉ በሙሉ ተለይተዋል።
በዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር ሀዋሳ ከተማ እና መቻል ሲገናኙ ቀዝቃዛ በነበረው የመጀመሪያ አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ የመድረስ ፍላጎት ቢታይም የግብ ዕድሎች ግን አልተፈጠሩም ነበር። ሆኖም የተሻለው ሙከራ 15ኛው ደቂቃ ላይ በመቻሎች አማካኝነት ሲደረግ በረከት ደስታ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ሆኖ ወደ ውስጥ የቀነሰውን ኳስ ሮጦ በመግባት ያገኘው ሽመልስ በቀለ ያደረገውን ሙከራ በኳስ አቅጣጫ የነበረው ግብ ጠባቂው ቻርለስ ሉክዋጎ ይዞበታል።
ደቂቃዎች እየገፉ በሄዱ ቁጥር በማጥቃት እንቅስቃሴያቸው መጠነኛ መሻሻል ያሳዩት ኃይቆቹ አጋማሹ ሊጠናቀቅ በተጨመረው አንድ ደቂቃ ውስጥ ግብ አስቆጥረዋል። ዓሊ ሱሌይማን ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ከአዲሱ አቱላ በተሻገረለት ኳስ ተከላካይ እና ግብ ጠባቂ በግሩም ክህሎት በመሸወድ እና ከፍ አድርጎ (ቺፕ) በመምታት ማስቆጠር ችሏል።
ከዕረፍት መልስ መቻሎች በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫውን በመውሰድ ተጭነው መጫወት ሲችሉ 50ኛው ደቂቃ ላይ ምንይሉ ወንድሙ ከረጅም ርቀት ከቅጣት ምት ያደረገው እና በግቡ የግራ ቋሚ ለጥቂት የወጣው ኳስም የተሻለው ለግብ የቀረበ ሙከራቸው ነበር። ሆኖም 54ኛው ደቂቃ ላይ ኃይቆቹ በፈጣን የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ተጨማሪ ግብ አስቆጥረዋል። ዓሊ ሱሌይማን ከተባረክ ሄፋሞ የተቀበለውን ኳስ ከሳጥን አጠገብ ሆኖ በተረጋጋ አጨራረስ መረቡ ላይ አሳርፎታል።
በመቻሎች በኩል በሁለተኛው አጋማሽ ብቸኛ መልካም አጋጣሚያቸው ለረጅም ጊዜ ጉዳት ላይ የነበረው ፍጹም ዓለሙ 78ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ በመግባት ወደ ሜዳ መመለሱ ሲሆን ሆኖም ግን ወሳኙ አማካያቸው በገባበት ቅፅበት ተጨማሪ ግብ አስተናግደዋል። ሀዋሳዎች ከራሳቸው የግብ ክልል በረጅሙ ያሻገሩትን ኳሰ ዓሊ ሱሌይማን ተከላካዩን አስቻለው ታመነን ከኋላ ተነስቶ በግሩም ፍጥነት በመቅደም እና ኳሱን ተቆጣጥሮ በሳጥኑ የቀኝ ክፍል በመግባት ለራሱም ሆነ ለክለቡ ሦስተኛ ግብ አስቆጥሮ ሐት-ትሪክ መሥራት ችሏል።
በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎችም በርካታ የግብ ዕድሎች ሲፈጠሩ 81ኛው ደቂቃ ላይ በኃይሉ ኃይለማርያም ጥሩ ሙከራ አድርጎ በግብ ጠባቂው ቻርለስ ሉክዋጎ ሲመለስበት በኃይቆቹ በኩል ደግሞ ዓሊ ሱሌይማን እና ተባረክ ሄፋሞ ያለቀላቸው ኳሶች አግኝተው ሳይጠቀሙባቸው ቀርተው ጨዋታው በሀዋሳ ከተማ 3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎም ሀዋሳ ወደ ሩብ ፍጻሜው የተቀላቀለ ሰባተኛው ቡድን መሆን ችሏል።
በሦስተኛው ዙር የመጨረሻ ጨዋታ ኮልፌ ክ/ከተማ እና ኢትዮጵያ ቡና ሲገናኙ 09፡30 ላይ በተጀመረው ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ ኢትዮጵያ ቡናዎች በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ በመውሰድ ዝግ ባለ የማጥቃት እንቅስቃሴ ለመጫወት ጥረት ሲያደርጉ ኮልፌዎች በአንጻሩ ወደ ራሳቸው የግብ ክልል ተጠግተው ለመጫወት ሲሞክሩ ተስተውሏል። ሆኖም በሁለቱም በኩል ለግብ የቀረበ ሙከራ ሳይደረግ ጨዋታው ወደ ዕረፍት አምርቷል።
ከዕረፍት መልስ እጅግ ተሻሽለው የቀረቡት ቡናማዎቹ አጋማሹ በተጀመረ በአንድ ደቂቃ ውስጥ በሁለት አጋጣሚዎች ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ነበር። በቅድሚያም መስፍን ታፈሰ ያደረገውን ግሩም ሙከራ የግቡ አግዳሚ ሲመልስበት በሴኮንዶች ልዩነት ደግሞ ጫላ ተሺታ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ብሩክ በየነ ወደ ግብ ሲሞክረው በተከላካይ እና በግብ ጠባቂ የተጨረፈው ኳስ የግቡን አግዳሚ ገጭቶ ተመልሷል። ያንኑ ኳስ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ሆኖ ያገኘው መስፍን ታፈሰም ያደረገው ሙከራ የግቡን የግራ ቋሚ ገጭቶ ወጥቶበታል።
ተደራጅተው ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ የተቸገሩት ኮልፌዎች የተሻለውን የግብ ሙከራቸውን 58ኛው ደቂቃ ላይ ሲያደርጉ ቃለጌታ ምትኩ ከረጅም ርቀት በግራ መስመር ከተገኘ የቅጣት ምት ያደረገው ሙከራ በግቡ አግዳሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል። በሚያገኙት ኳስ ሁሉ በፈጣን የማጥቃት ሽግግር ተጭነው መጫወታቸውን የቀጠሉት ኢኢትዮጵያ ቡናዎች 78ኛው ደቂቃ ላይ ተሳክቶላቸዋል። አማኑኤል ዮሐንስ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ሆኖ ያሻማውን ኳስ መስፍን ታፈሰ በግንባር ገጭቶት የግቡ የቀኝ ቋሚ ሲመልስበት ያንኑ ኳስ ያገኘው ተቀይሮ የገባው መሐመድኑር ናስር በጥሩ አጨራረስ መረቡ ላይ አሳርፎታል።
በርከት ያሉ ተጫዋቾችን ለውጥ ያደረጉት ቡናዎች መምራት ከጀመሩ በኋላም በተሻለ የራስ መተማመን ጨዋታውን መቆጣጠር ሲችሉ ጨዋታው ሊጠናቀቅ በተጨመሩ አምስት ደቂቃዎች ውስጥ አምስተኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው መላኩ አየለ ከመሃል ሜዳ ከቅጣት ምት ባሻገረው እና መሐመድኑር ናስር በግንባሩ ገጭቶ ባስቆጠረው ግብ ጨዋታውን 2-0 ማሸነፍ ችለዋል። ውጤቱን ተከትሎም ኢትዮጵያ ቡና የኢትዮጵያ ዋንጫን ሩብ ፍጻሜ የተቀላቀለ ስምንተኛው ቡድን ሆኗል !
– የሩብ ፍጻሜ ተፋላሚዎችም ሙሉ በሙሉ የተለዩ ሲሆን ቀጣዩ ፕሮግራም ይህንን ይመስላል 👇
ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ወላይታ ድቻ
አዳማ ከተማ ከ ኢትዮጵያ መድን
አርባምንጭ ከተማ ከ ሀዋሳ ከተማ
ፋሲል ከነማ ከ ኢትዮጵያ ቡና
ጨዋታዎቹ የካቲት ወር ላይ እንደሚደረጉ ይጠበቃል።