👉 “ደርቢ ለደጋፊ ምን ማለት እንደሆነ አውቀዋለሁ።”
👉 “እንደየትኛውም ጨዋታ እኩል አድርጌ ነው የማስበው።”
👉 “ከአሁን በኋላ በሚኖሩ ጊዜያቶች እናሻሽላለን።”
በሁሉም የስፖርት አፍቃርያን ዘንድ በታላቅ ጉጉት የሚጠበቀው አርባ ሰባተኛው የሸገር ደርቢ ነገ በአዳማ ዩኒቨርስቲ ሜዳ ይካሄዳል። ይህን ጨዋታ መሰረት በማድረግ የተለያዮ ቃለ መጠይቆችን እያደረስን ሲሆን አሁን ደግሞ ዓምና ወደ ዋናው ቡድን ቢያድግም ብዙም የመሰለፍ ባያገኝም ዘንድሮ ግን በተጫወተባቸው ጨዋታዎች ጥሩ አቋሙን እያሳየ የሚገኘው ወጣቱ አማካይ ኤርሚያስ ሹምበዛ ከነገው ጨዋታ በተገናኘ ከሶከር ያደረገውን ቆይታ ወደ እናተ እናደርሳለን።
የእግር ኳስ አጀማመርህ እንዴት ነበር ?
“እንደ ማንኛውም እግርኳስ ተጫዋች ሰፈር ውስጥ እየተጫወትኩ ነው ያደኩት የተወለድኩትም ጉንችሬ የሚባል አካባቢ ነው። ከሁለት ዓመት በፊት የወልቂጤ ከተማ ከ17 ዓመት በታች ቡድንን ተቀላቀልኩ። ከዛም አሰልጣኝ ዮሴፍ ተስፋዬ በኢትዮጵያ ቡና ዕድል ሰጠኝ እና ለኢትዮጵያ ቡና ከ20 ዓመት በታች ቡድን አንድ ዓመት ተጫወትኩ በሚቀጥለው ደግሞ ወደ ዋናው ቡድን አደኩ እና በመጨረሻው ጨዋታ ጥቂት ደቂቃዎች ላይ ብቻ የመጫወት ዕድል አገኘሁ።”
ስለወቅታዊ ብቃትህ…
“በግሌ ያለኝ አቋም አሪፍ ነው ብዬ አስባለሁ ነገር ግን እንደ ቡድን ጥሩ ውጤት ላይ አይደለንም። ቡድናችን ብዙ እየሠራ ቢሆንም ውጤት ላይ ብዙም አይደለንም። ነገር ግን ፈጣሪ ይረዳናል ብዬ አስባለሁ ከአሁን በኋላ በሚኖሩ ጊዜያቶች እናሻሽላለን።”
ለደርቢው ጨዋታ እንዴት እየተዘጋጃችሁ ነው ?
“የደርቢን ጨዋታ ከታዳጊነቴ ጀምሮ በትንሹም ቢሆን ስሜቱን አውቀዋለሁ። ከተጫዋች በበለጠ ደግሞ ለደጋፊ ምን ማለት እንደሆነ አውቀዋለሁ እና ለዛም በጣም ጥሩ ዝግጅት እያደረግን ነው። ከእግዚአብሔር ጋር እናሸንፋለን ብዬ አስባለሁ።”
ስለተጋጣሚያችሁ ቅዱስ ጊዮርጊስ…
“ሸገር ደርቢ ሲባል ኢትዮጵያ ውስጥ አሉ ከሚባሉ ጨዋታዎች በጣም ትልቁ ጨዋታ ነው። ነገር ግን ኢትዮጵያ ቡና ሲባል ሁሌም ዝግጁ ነን ብዬ አሰባለሁ። የነገሮች አለመገጣጠም ሆኖ ውጤት አጣን እንጂ ቡድናችን እስካሁን ባለው ነገር በጣም ምርጥ ላይ ነን። ከጊዮርጊስ አሁን ያለበት ደረጃ ጥሩ ቢሆንም እኛም የተሻልን እንደሆነ አስባለው።
ስለ ነገው ጨዋታ ግምት…
ሁሌም ቢሆን ለእያንዳንዱ ከፊታችን ለሚጠብቀን ጨዋታ ጥሩ ዝግጅት እናደርጋለን። ነገ በሚኖረን ጨዋታም በጣም የተሻለ ነገር አሳይተን እናሸንፋለን ብዬ አስባለሁ።”
ከ20 ዓመት በታች የደርቢ ጨዋታ ላይ ተሳትፎ ነበረህ በዋናው ቡድንስ እንዴት ነው ስሜቱ ?
“ብዙም የተለየ ስሜት ባይኖረኝም እንደየትኛውም ጨዋታ እኩል አድርጌ ነው የማስበው። ምናልባትም ለደጋፊዎቹ የተለየ ስሜት ይኖረው ይሆናል ፤ ለእኛ ግን ሁሉንም ጨዋታ እኩል አድርገን ነው የምናስበው። ሸገር ደርቢ ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ የሚጠበቅ ጨዋታ ስለሆነ ትኩረት አድርገን በጥንቃቄ ተጫውተን እናሸንፋለን።”