በሣምንቱ ቀዳሚ መርሐግብር ሲዳማ ቡና በይገዙ ቦጋለ ብቸኛ ግብ ኢትዮጵያ መድንን 1ለ0 በመርታት ተከታታይ ድል ተቀዳጅቷል።
በ9ኛ ሣምንት የመጀመሪያ መርሐግብር ኢትዮጵያ መድን እና ሲዳማ ቡና ሲገናኙ ሁለቱም ቡድኖች ሊጉ ከመቋረጡ በፊት ከተጠቀሙት አሰላለፍ በተመሳሳይ በሁለት ተጫዋቾች ላይ ለውጥን አድርገዋል። ኢትዮጵያ መድን ዮናስ ገረመው እና ኦሊስማ ቼኔዱን አሳርፈው በወገኔ ገዛኸኝ እና አሚር ሙደሲር ሲተኩ ሲዳማ ቡና ከወላይታ ድቻ ድላቸው አንፃር ሙሉቀን አዲሱን በቡልቻ ሸራ ፣ ይገዙ ቦጋለን በማይክል ኪፖሩል ተክተው ለጨዋታው ቀርበዋል።
9 ሰዓት ላይ በኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ ፊሽካ በተጀመረው ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ 20 ደቂቃዎች በተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ ተጭነው የተጫወቱት ሲዳማዎች 7ኛው ደቂቃ ላይ የመጀመሪያውን ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ሲያደርጉ ቡልቻ ሹራ ከማይክል ኪፖሩል ጋር በተቀባበለው ኳስ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው አቡበከር ኑራ ይዞበታል። በተመሳሳይ ሂደት በቀጠለው ጨዋታ ሲዳማዎች 17ኛው ደቂቃ ላይም ተጨማሪ ፈታኝ ሙከራ አድርገዋል። ማይክል ኪፖሩል ከሳጥኑ የግራ ጠርዝ ላይ አክርሮ የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው አቡበከር አስወጥቶበታል።
ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው በመመለስ በቁጥር በዝተው ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መታተር የጀመሩት መድኖች የጠሩ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲቸገሩ 32ኛው ደቂቃ ላይም በአጋማሹ የተሻለውን ሙከራቸውን አድርገዋል። ቹኩዌሜካ ጎድሰን ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ከተከላካይ ጋር ታግሎ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው መሐመድ ሙንታሪ መልሶበታል። በቀሪ ደቂቃዎችም ያን ያህል ተጠቃሽ የማጥቃት እንቅስቃሴ ሳይደረግ ጨዋታው ወደ ዕረፍት አምርቷል።
ከዕረፍት መልስ በሲዳማ አሰልጣኝነት በውድድር ዓመቱ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን የመሩት አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ሀብታሙ ገዛኸኝን አሳርፈው ይገዙ ቦጋለን ሲያስገቡ ቅያሪያቸው ውጤታማ ለመሆን ከአራት ደቂቃዎች በላይ አልፈጀም። በዛብህ መለዩ ከሳጥኑ የግራ ጠርዝ ላይ መሬት ለመሬት የመታውን ኳስ ተቀይሮ የገባው ይገዙ ቦጋለ አቅጣጫ አስቀይሮ በግቡ የቀኝ ክፍል በኩል መረቡ ላይ አሳርፎታል።
በሁለቱም በኩል ቶሎ ቶሎ በሚቆራረጡ ቅብብሎች ታጅቦ በቀጠለው ጨዋታ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ዝግ ብለው ወደ ጨዋታው ግለት የተመለሱት መድኖች 70ኛው ደቂቃ ላይ በአብዱልከሪም መሐመድ 74ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ በቹኩዌሜካ ጎድሰን ከረጅም ርቀት ጥሩ ሙከራ ማድረግ ቢችሉም በተደራጀ የማጥቃት እንቅስቃሴ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመግባት ተቸግረው ተስተውሏል።
በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ መውሰድ የቻሉት ኢትዮጵያ መድኖች 81ኛው ደቂቃ ላይ ንጋቱ ገብረሥላሴ ከሳጥን አጠገብ መሬት ለመሬት መትቶት ግብ ጠባቂው ከመለሰበት ኳስ ውጪ የተሻለ የግብ ዕድል ለመፍጠር ሳይችሉ ሲቀሩ ወደ ራሳቸው የግብ ክልል ተጠግተው መጫወትን እየመረጡ የሄዱት ሲዳማዎች ግን በመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ በቀጥተኛ ኳሶች በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ የግብ ሳጥን ቢደርሱም ሳይጠቀሙባቸው ቀርተዋል። ጨዋታውም በሲዳማ ቡና 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።