ሽመልስ በቀለ ከአስራ አምስት ዓመታት በላይ ካገለገለበት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ራሱን ማግለሉን ይፋ አድርጓል።
የእግር ኳስ ጅምሩን ከሀዋሳ ከተማ ካደረገ በኋላ በመቀጠል በቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ሊቢያ በማምራት ለአሊተሀድ ፣ ለሱዳኑ ኤልሜሪክ እና እንዲሁም ረጅም ዓመት ወዳሳለፈበት ግብፅ በማቅናት ፔትሮጀክት ፣ ኤልጉና ፣ ምስር ኤልመካሳ እና ኤን ፒፒ አይ ተጫውቶ ካሳለፈ በኋላ ከአስር ዓመታት የውጪ ቆይታ በኋላ ወደ ሀገሩ በመመለስ ለመቻል ክለብ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በመጫወት ላይ የሚገኘው አማካዩ ሽመልስ በቀለ በይፋ አስራ አምስት ዓመታትን ካሳለፈበት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ግልጋሎት ራሱን በይፋ አግልሏል። ተጫዋቹ ራሱን ከብሔራዊ ቡድን ማግለሉን አስመልክቶ በማህበራዊ ገፁ ተከታዩን ሀሳብ አጋርቷል።
“ጊዜው አሁን እንደሆነ ይሰማኛል ፣ ብሔራዊ ቡድኑን የምሰናበትበት ወቅት የምወደውን እና የምጓጓለትን አረንጓዴ ፣ ቢጫ እና ቀዩን ሰንደቅ አላማ ወክዬ የምጫወትበት ጊዜ እንዳበቃ ይሰማኛል። ከትልቅ አክብሮት ጋር የብሔራዊ ቡድን ጉዞዬን እዚህ ጋር ለማብቃት ወስኛለሁ ፣ ይህን ውሳኔ ላይ ስደርስ እና ለስፖርት አፍቃሪው ሳጋራ ከትልቅ ከበሬታ ጋር ነው። የሀገራችንን ባንዲራ ከፍ ለማድረግ በተጫወትኩበት አጋጣሚዎች ሁሉ ከቡድን አጋሮቼ ጋር ያሳለፍናቸውን አጋጣሚዎች ሁሌም የማልረሳቸው እና በታሪክነት ይህ አርማ ፣ ማልያ እና ስፖርት አፍቃሪው እንዲሁም መላው ኢትዮጵያዊ ለሀገሬ በምጫወትበት እያንዳንዱ አጋጣሚ ያሳያችሁኝ ፍቅር ሁሌም ደስተኛ አድርጎኛል።
ሀገሬን እንድወከል የመጀመሪያውን ጥሪ ካቀረቡልኝ አሰልጣኝ አብርሀም ተክለማርያም _ ጀምሮ እስከ መጨረሻው አሰልጣኝ ገብረ መድህን ሀይሌ እና በብሔራዊ ቡድን ያሰለጠናችሁኝ መላው አሰልጣኞች እና የአሰልጣኝ ቡድን አባላት ያለኝን አክብሮት እና ምስጋና ለመግለፅ እወዳለሁ። በብሔራዊ ቡድን ቆይታዬ ከሰላሳ አንድ ዓመታት በኋላ ለአፍሪካ ዋንጫ ሲያልፍ የቡድን አባል መሆኔ አሁንም ሳስበው ልዩ ስሜትን ይፈጥርልኛል። በቆይታዬ ብሔራዊ ቡድናችንን ህዝቡ እንደሚጠብቀው በአለም ዋንጫ መሳተፍ እና በአፍሪካ ዋንጫ ውድድር የተሻለ ውጤት አለማስመዝገባችን የሚያስከፋኝ እና የሚቆጨኝ ነው።
“በቀጣይ የሚመጣው ትውልድ እና የቡድን አጋሮቼ ይህን እንደሚያሳዩ ትልቅ እምነት ያለኝ ሲሆን እኔም ይህ እንዲሳካ ከተጫዋችነት ውጪ ባለኝ ከጎን መሆን እንደምችል አረጋግጣለሁ። በዚህ ጉዞዬ ውስጥ የነበሩ የ ኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንቶች ፣ ስራ አስፈፃሚ እና መላው ሰራተኞች ታሳዩኝ ለነበረው ፍቅር አክብሮቴን እገልፃለሁ። በቀጣይም ከሀገሬ እና ብሔራዊ ቡድኑ ጎን በመሆን በስሜት እና በኩራት ዋልያዎቹን የማበረታታ መሆኑን ለመግለፅ እወዳለሁ። ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻዋ ቀን በእኔ እምነቱ ኖሯችሁ ከጎኔ ለነበራችሁ ሁሉ ልባዊ ምስጋናዬ ይድረሳችሁ።” ሲል በይፋ ስንብቱን አሳውቋል።