በምድብ ‘ሀ’ 10ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ ሦስት ጨዋታዎች ተደርገው ስልጤ ወራቤ ፣ ንብ እና አዲስ አበባ ከተማ ድል ቀንቷቸዋል።
ረፋድ 3:30 ላይ የተደረገው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የመጀመሪያ ቀን የመጀመሪያ ጨዋታ ወልዲያን ከስልጤ ወራቤ አገናኝቶ በስልጤ ወራቤ አሸናፊነት ተጠናቋል።
የመጀመሪያው አጋማሽ ወልዲያ ጥሩ የሚባል እንቅስቃሴ እና የኳስ ቅብብል አስመልክተውናል። በአንፃሩ ስልጤ ወራቤ ረጃጅም ኳሶችን በመጠቀም በመልሶ ማጥቃት ግብ ለማስቆጠር ጥረት ሲያረጉ ተስተውሏል። ጨዋታው በተጀመረ በ2ኛ ደቂቃ የወልዲያ ተጫዋች የሆነው በኃይሉ ተስፋዬ ወደ ግብ አንጥሮ የመታውን ኳስ የስልጤ ወራቤ ተጫዋች የሆነው ደስታ ጊቻሞ ከመስመር አውጥቶ ግብ እንዳይቆጠር ማድረግ ችሏል። አጋማሹ መጠናቀቂያ አከባቢ ስልጤ ወራቤ ግብ ለማስቆጠር ጫና ፈጥረዋል። ይህንን ተከትሎ በ42ኛው ደቂቃ የስልጤ ወራቤ ተጫዋች የሆነው ብሩክ ሰማ ከአማኑኤል ተስፋዬ ጋር ተቀባብሎ ከርቀት ወደ ግብ የመታው ኳስ ወደ ግብ ተቀይሮ ቡድኑን መሪ አድርጓል።
ሁለተኛው አጋማሽ ወልዲያ ባለው ኃይል የተወሰደበትን የግብ ብልጫ ለመቀልበስ ጫና ፈጥሮ ሲጫወት የነበረ ሲሆን በአንፃሩ ስልጤ ወራቤ ያገኘውን የግብ ብልጫ ለማስጠበቅ ወደ ኋላ በማፈግፈግ የሚያገኘውን ኳስ በመልሶ ማጥቃት የግብ ዕድል ለመፍጠር ጥረት ሲያረጉ ተስተውሏል። በ80ኛው ደቂቃ የስልጤ ወራቤ ተጫዋች የሆነው ሥዩም ደስታ ከጥልቀት የተሻገረለትን ኳስ በግል ጥረቱ ወደ ውስጥ በመግባት አስቅቆ የስልጤ ወራቤን አሸናፊነት አረጋግጧል። ጨዋታውም በስልጤ ወረቤ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። በውጤቱም ሥልጤ ወራቤ የዓመቱን ሦስተኛ ድል በማሳካት ከሰንጠረዡ ግርጌ ፈቀቅ ማለት ችሏል።
ከዚህ ጨዋታ በመቀጠል 5:30 ላይ በተደረገው መርሀግብር ንብ በጨዋታው መጀመሪያ ባስቆጠረው ብቸኛ ግብ ማሸነፍ ችሏል ።
ኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅን ከንብ ያገናኘው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ በ3ኛው ደቂቃ የንብ ተጫዋች የሆነው ይበልጣል ሽባባው ከመስመር ያሻገረውን ኳስ ምስክር መለስ የተሻገረውን ኳስ መሬት ሳያወርድ ወደ ግብ በመምታት ግብ ማስቆጠር ችሏል። ከግቡ መቆጠር በኋላ ኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ ግብ ለማስቆጠር መጠነኛ እንቅስቃሴ ቢያሳዩም ንብ የመከላከል ስፍራውን በማጠናከር ግብ እንዳይቆጠርበት ጥረት ሲያደርግ ተስተውሏል። ብዙም የግብ ሙከራ ያላየንበት አጋማሽ ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ሁለተኛው አጋማሽ ንብ ጥንቃቄን በመጨመር የወሰደውን የግብ ብልጫ ለማስጠበቅ ከፍተኛ ጥረት አድርጓል። ኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ ግብ ለማስቆጠር ከፍተኛ ጥረት ቢያረግም የንብ የተከላካይ መስመርን መስበር ተስኖታል። በ78ኛው ደቂቃ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሌጅ ተጫዋች የሆነው ዳንኤል ዳርጌ ጥፋት ተሰርቶበት ያገኘውን ፍፁም ቅጣት ምት ሳይጠቀምበት ቀርቶ ጨዋታው በንብ 1-0 አሸናፊነት ተቋጭቷል።
የዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ 07:30 ላይ የጀመረ ሲሆን ጅማ አባ ጅፋርን ከአዲስ አበባ ከተማ አገናኝቶ የመዲናውን ቡድን ባለድል አድርጓል።
የመጀመሪያው አጋማሽ ጅማ አባ ጅፋር በኳስ ቁጥጥሩ ተሽለው ተገኝተዋል። በአዲስ አበባ ከተማ በኩል ኃይል የቀላቀለ እና ተጋጣሚውን ጫና ውስጥ ሊከት የሚችል አጨዋወት አስመልክተውናል። ወደ ግብ ለመድረስም ጅማ አባ ጅፋር በጥሩ ቅብብል የተጋጣሚውን የተከላካይ መስመር ሰብሮ ለመግባት ጥረት ቢያደርጉም ማሳካት ተስኗቸዋል። በአንፃሩ አዲስ አበባ ከተማ የጅማ አባ ጅፋርን አጨዋወት በማበላሸት የሚገኘውን ኳስ በመልሶ ማጥቃት ወደ ግብ ሲደርሱ ተስተውሏል። ይህንንም ተከትሎ መደበኛው ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በተጨማሪ ደቂቃ ተጨራርፎ የተገኘውን ኳስ አዲስ አበባ ከተማ በቢንያም ፀጋዬ አማካኝነት አስቆጥሮ አጋማሹን በአዲስ አበባ ከተማ መሪነት ተጠናቋል። ከግቡ መቆጠር በኋላ የጅማ አባ ጅፋር ተጫዋቾች የግቡ መፅደቅን ተቃውመው ከመሀል ዳኛው ጋር አለመግባባት ተፈጥሮ ተስተውሏል።
ሁለተኛው አጋማሽ አዲስ አበባ ከተማ የተጫዋች ቅያሪ በማድረግ ራሱን ማጠናከር ችሏል። ጅማ አባ ጅፋሮችም ግብ ለማስቆጠር ከፍተኛ ጥረት ያደረጉ ቢሆንም የአዲስ አበባ ከተማን የመከላከል መስመር ማስከፈት ተስኗቸዋል። ጨዋታውም በአዲስ አበባ ከተማ አሸናፊነት ተጠናቋል።
ውጤቱን ተከትሎ አዲስ አበባ ከተማ ያለመሸነፍ ጉዞውን ሲያስቀጥል ጅማ አባ ጅፋር ከሦስት ተከታታይ ድል በኋላ ሽንፈት አስተናግዷል።