ሪፖርት | ቅዱስ ጊዮርጊስ እና መቻል አቻ ተለያይተዋል

በፈረሠኞቹ እና በጦሩ መካከል የተደረገው የምሽቱ ተጠባቂ ጨዋታ 1-1 ተጠናቋል።

በምሽቱ ተጠባቂ መርሐግብር ቅዱስ ጊዮርጊስ እና መቻል ሲገናኙ ፈረሠኞቹ በሰባተኛ ሣምንት ተስተካካይ የሸገር ደርቢ ጨዋታቸው ከተጠቀሙት አሰላለፍ በረከት ወልዴን አሳርፈው ፍሪምፖንግ ክዋሜን ሲተኩ መቻሎችም በስምንተኛው ሣምንት ወልቂጤ ከተማን 2ለ0 ሲያሸንፉ ከተጠቀሙት አሰላለፍ ሳሙኤል ሳሊሶን አስወጥተው በረከት ደስታን ተክተዋል።

12፡00 ሲል በተደረገው ጨዋታ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለ15 ዓመታት የተጫወተው እና ዛሬ በይፋ ራሱን ከብሔራዊ ቡድኑ ያገለለው ሽመልስ በቀለ በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ እና በሌሎች የክብር እንግዶች ፊት በክብር ተሸኝቷል።

ብርቱ ፉክክር በተደረገበት የመጀመሪያ አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች በጋለ እና ዕረፍት የለሽ በሆነ እንቅስቃሴ ለተመልካች ሳቢ የሆነ ጨዋታ ሲያሳዩ የመጀመሪያው የጠራ የግብ ዕድልም 12ኛው ደቂቃ ላይ በመቻሎች አማካኝነት ሲፈጠር በረከት ደስታ ከግራ መስመር ባሻገረለት ኳስ ግብ ጠባቂውን በድንቅ ክህሎት አታልሎ መሸወድ የቻለው ሽመልስ በቀለ ያደረገውን ሙከራ ፍሪምፖንግ ክዋሜ ከመስመር አግዶበታል።

በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በማጥቃት እንቅስቃሴው የተሻሉ የነበሩት መቻሎች 20ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ሽመልስ በቀለ በድንቅ ዕይታ ሰንጥቆ ያቀበለውን ኳስ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ያገኘው ምንይሉ ወንድሙ በግሩም አጨራረስ በግቡ የግራ ቋሚ በኩል አስቆጥሮታል።

 

በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ በመውሰድ የማጥቃት እንቅስቃሴያቸውን እያጠናከሩ የሄዱት ጊዮርጊሶች 28ኛው ደቂቃ ላይ ተሳክቶላቸዋል። አቤል ያለው በግራ መስመር በተሠራበት ጥፋት የተሰጠውን የቅጣት ምት ዳዊት ተፈራ ሲያሻማው ፍሪምፖንግ ሜንሱ በግንባሩ በመግጨት መረቡ ላይ አሳርፎታል።

በአጋማሹ ቀሪ ደቂቃዎችም መጠነኛ ፉክክር እየተደረገ የጨዋታው ግለት በመጠኑ እየተቀዛቀዘ ሲሄድ 43ኛው ደቂቃ ላይ በመቻል በኩል በረከት ደስታ በቀኝ መስመር ከማዕዘን ያሻማው እና ከነዓን ማርክነህ በግንባሩ ገጭቶት በግቡ የቀኝ ቋሚ በኩል የወጣበት ኳስ የተሻለው የግብ ሙከራ ነበር።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው በመጠኑ ተቀዛቅዞ ሲቀጥል በመጀመሪያዎቹ 20 ደቂቃዎች የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የወሰዱት ፈረሠኞቹ 53ኛው ደቂቃ ላይ ለግብ የቀረበ ሙከራ አድርገዋል። ቢኒያም በላይ ያመቻቸውን ኳስ በሳጥኑ የቀኝ ክፍል ሮጦ በመግባት ያገኘው ሄኖክ አዱኛ ሁለት ጊዜ ያደረጋቸውን ሙከራዎች ግብ ጠባቂው አልዌንዚ ናፊያን መልሶበታል።

መቻሎች ቀስ በቀስ ለ10 ደቂቃዎች ያህል በተሻለ የኳስ ቁጥጥር ወደፊት ተጭነው ለመጫወት ቢሞክሩም የጠራ የግብ ዕድል ለመፍጠር ሲቸገሩ በድጋሚ በመጨረሻዎቹ 15 ደቂቃዎች ወደ ግለታቸው የተመለሱት ፈረሠኞቹ 76ኛው ደቂቃ ላይም ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ነበር። አቤል ያለው ከረጅም ርቀት በተሰነጠቀለት ኳስ ግሩም ሩጫ በማድረግ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው አልዌንዚ ናፊያን በጥሩ ቦታ አያያዝ አግዶበታል።

ደቂቃዎች በገፉ ቁጥር ጊዮርጊሶች በተደጋጋሚ በቁጥር በመብዛት ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ ቢችሉም 93ኛው ደቂቃ ላይ አቤል ያለው በግራ እግሩ ሞክሮት በግቡ አግዳሚ ለጥቂት ከወጣበት ኳስ ውጪ ሁለቱም ቡድኖች የጠራ የግብ ዕድል መፍጠር ሳይችሉ ቀርተው ጨዋታው በመጀመሪያ አጋማሽ በተቆጠሩ ግቦች 1-1 ተጠናቋል።