ዐፄዎቹ በሁለተኛው አጋማሽ ባስቆጠሯቸው ሦስት ግቦች ድሬዳዋ ከተማን 3-0 ረተዋል።
በዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር ድሬዳዋ እና ፋሲል ከነማ ሲገናኙ በሊጉ ስምንተኛ ሳምንት ድሬዳዋ ከባህርዳር ጋር ካደረገው ጨዋታ የሁለት ተጫዋቾችን ለውጥ ሲያደርግ ቻርለስ ሙሴጌ እና ዘርዓይ ገብረሥላሴ አርፈው ዳዊት እስጢፋኖስ እና ሙኸዲን ሙሳ ሲተኳቸው በሀድያ ሆሳዕና ተረተው በነበሩት ፋሲል ከነማዎች በኩል በተደረጉ ሦስት ለውጦች እዮብ ማቲያስ ፣ ይሁን እንዳሻው እና አማኑኤል ገብረሚካኤል አርፈው በአምሳሉ ጥላሁን ፣ አቤል እንዳለ እና ቃልኪዳን ዘላለም ቅያሪ ተደርጎባቸዋል።
እጅግ ቀዝቃዛ በነበረው የመጀመሪያ አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ፈታኝ የማጥቃት እንቅስቃሴ ለማድረግ ሲቸገሩ በኳስ ቁጥጥሩ እና ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በቁጥር በዝቶ በመድረሱ በኩል ዐፄዎቹ መጠነኛ ብልጫ ነበራቸው። ሆኖም ግን 10ኛው ደቂቃ ላይ ምኞት ደበበ ከማዕዘን ተሻምቶ በተመለሰ ኳስ ተገልቦጦ በሴኮንዶች ልዩነት ደግሞ ሱራፌል ዳኛቸው ከሳጥን ውጪ ያደረጓቸው ሙከራዎች የተሻሉት ነበሩ።
ወደ ራሳቸው የግብ ክልል ተጠግተው መጫወትን የመረጡት ብርቱካናማዎቹ የተደራጀ የመከላከል ቅንጅት ማሳያት ቢችሉም ከራሳቸው የግብ ክልል በቁጥር በዝተው ለመውጣት ግን ሲቸገሩ ተስተውሏል። 44ኛው ደቂቃ ላይ ዳዊት እስጢፋኖስ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ኤልያስ አህመድ ያደረጓቸው ሙከራዎችም ግብ ጠባቂውን ሳማኬ ሚኬልን የሚፈትኑ አልነበሩም።
ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ተሻሽሎ ሲቀጥል በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ በመውሰድ ተጭነው መጫወታቸውን የቀጠሉት ዐፄዎቹ በተደጋጋሚ ከቆሙ ኳሶች የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት ሲያደርጉ በተለይም 57ኛው ደቂቃ ላይ ጌታነህ ከበደ ከቅጣት ምት ያደረገውን ግሩም ሙከራ የግቡ የቀኝ ቋሚ መልሶበታል።
ጨዋታው 63ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ ግብ ተቆጥሮበታል። በፋሲል ከነማ የማጥቃት እንቅስቃሴ ውስጥ ቁልፍ የነበረው ጌታነህ ከበደ ከተደጋጋሚ ጥረቶች በኋላ ያገኘውን የቅጣት ምት ኳስ በአስደናቂ ሁኔታ በመምታት መረቡ ላይ አሳርፎታል።
ብርቱካናማዎቹ ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ ፈጣን የተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ ከራሳቸው የግብ ክልል በጥቂት ንክኪዎች በመውጣት የማጥቃት እንቅስቃሴያቸውን ለማነቃቃት ሲሞክሩ 76ኛው ደቂቃ ላይ ግን በተሻለ የራስ መተማመን ላይ በነበሩት ፋሲሎች ተጨማሪ ግብ አስተናግደዋል። ሽመክት ጉግሳ የሰነጠቀለትን ኳስ የድሬዳዋ ተጫዋቾች ከጨዋታ ውጪ ነው ብለው በተዘናጉበት ቅጽበት ያገኘው ጌታነህ ከበደ በሳጥኑ የቀኝ ክፍል ይዞት በመግባት በተረጋጋ አጨራረስ ግብ አድርጎታል።
በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎችም ፍጹም ብልጫ በመውሰድ ጨዋታውን ማረጋጋት የቻሉት ፋሲል ከነማዎች 83ኛው ደቂቃ ላይ በጌታነህ ከበደ አማካኝነት ከሳጥን ውጪ ሙከራ አድርገው በግብ ጠባቂው ዳንኤል ተሾመ ቢያዝባቸውም ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ሦስተኛ ግብ አስቆጥረዋል። ወደ ኋላ ተስቦ በመጫወት ድንቅ ልዩነት መፍጠር የቻለው ሽመክት ጉግሳ ሰንጥቆ ያቀበለውን ኳስ ተቀይሮ የገባው ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ በግሩም አጨራረስ መረቡ ላይ አሳርፎታል። ጨዋታውም በፋሲል ከነማ 3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።