ለተመልካች ማራኪ ፉክክር በተደረገበት የምሽቱ ጨዋታ ቡናማዎቹ መስፍን ታፈሰ የቀድሞ ክለቡ ላይ ባስቆጠራቸው ግቦች ኃይቆቹን 2ለ1 ረተዋል።
በምሽቱ ተጠባቂ ጨዋታ ሊጉ ከመቋረጡ በፊት ሀዋሳ ከተማ በቅዱስ ጊዮርጊስ ሲረታ ከተጠቀመው አሰላለፍ በአራቱ ላይ ለውጥን በማድረግ ሚሊዮን ሠለሞን ፣ እንየው ካሳሁን ፣ ታፈሠ ሠለሞን እና አማኑኤል ጎበና ወጥተው አቤኔዘር ዮሐንስ ፣ ማይክል ኦቱሉ ፣ አዲሱ አቱላ እና ሲሳይ ጋቾ ሲተኳቸው ኢትዮጵያ ቡና በተስተካካዩ የሸገር ደርቢ ጨዋታ ድል የቀናውን ቡድን ሳይቀይር ቀርቧል።
ምሽት 12 ሰዓት ላይ በተጀመረው ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ 30 ደቂቃዎች በኳስ ቁጥጥሩ ፍጹም ብልጫ የነበራቸው ቡናማዎቹ በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ የግብ ሳጥን መድረስ ሲችሉ 13ኛው ደቂቃ ላይም ጨዋታውን ለመምራት እጅግ ተቃርበው ነበር። ጫላ ተሺታ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ለማስቆጠር ምቹ ቦታ ላይ ሆኖ ያገኘው መሐመድኑር ናስር በግንባሩ ገጭቶ ያደረገው ሙከራ በግቡ የግራ ቋሚ በኩል ዒላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል።
በመስመር የማጥቃት እንቅስቃሴ በተሻለ ቦታ አያያዝ ኳሶችን ሲያገኝ የነበረው መሐመድኑር 17ኛው እና 18ኛው ደቂቃ ላይም በግንባሩ በመግጨት እና ከሳጥን ውጪ ተከላካዮችን አታልሎ በማለፍ ያደረጋቸው ሙከራዎች በግብ ጠባቂው ቻርለስ ሉክዋጎ ተይዘዋል።
ሀዋሳዎች ወደ ራሳቸው የግብ ክልል በመጠጋት የሚያገኙትን ኳስ ለዓሊ ሱሌይማን በረጅሙ በማሻገር የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት ሲያደርጉ 41ኛው ደቂቃ ላይም ጨዋታውን ለመምራት እጅግ ተቃርበው ነበር። አቤኔዘር ዮሐንስ ያሻገረለትን ኳስ ያገኘው ዓሊ ሱሌይማን ያደረገውን ሙከራ የግቡ የላይ አግዳሚ ሲመልስበት በሴኮንዶች ልዩነት ደግሞ ዓሊ ሱሌይማን ያመቻቸለትን ኳስ ከሳጥንኑ የቀኝ ክፍል ላይ ሆኖ ያገኘው አዲሱ አቱላ ያደረገው ሙከራም በተመሳሳይ በግቡ አግዳሚ ተመልሷል።
እንዳላቸው የኳስ ቁጥጥር ብልጫ እና ማራኪ እንቅስቃሴ በርከት ያለ የጠራ የግብ ዕድል ለመፍጠር የተቸገሩት ቡናማዎቹ 45ኛው ደቂቃ ላይ ተሳክቶላቸው ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። በፍቃዱ ዓለማየሁ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ብሩክ በየነ ሊጠቀምበት ሲል የመስመር ተከላካዩ መድኃኔ ብርሃኔ በሠራው ጥፋት የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት መስፍን ታፈሰ ግብ ጠባቂውን አታልሎ በግራ በኩል አስቆጥሮታል።
ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ተጋግሎ ሲቀጥል ኃይቆቹ ተሻሽለው በመግባት የተወሰደባቸውን የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በማስመለስ ተጭነው ለመጫወት ጥረት ሲያደርጉ 52ኛው ደቂቃ ላይ ተሳክቶላቸዋል። አዲሱ አቱላ ከሳጥን አጠገብ መሬት ለመሬት የመታውን ኳስ ግብ ጠባቂው በረከት አማረ አስወጥቶበታል። ያንኑ ኳስ ኢዮብ ዓለማየሁ በቀኝ መስመር ከማዕዘን አሻምቶት ኳሱን ያገኘው ዓሊ ሱሌይማን ወደ ግብ ሲመታው አቤኔዘር ዮሐንስ ኳሱን በግንባር ገጭቶ አቅጣጫ በማስቀየር መረቡ ላይ አሳርፎታል።
ኃይቆቹ የአቻነት ግብ ካስቆጠሩ በኋላም በጥሩ ንቃት ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በተደጋጋሚ መድረስ ሲችሉ 55ኛው ደቂቃ ላይም ኢዮብ ዓለማየሁ ከሳጥን አጠገብ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ አድርጎ ግብ ጠባቂው በረከት መልሶበታል። ከአንድ ደቂቃ በኋላም የመስመር ተከላካዩ መድኃኔ ብርሃኔ በሳጥኑ የቀኝ ክፍል ኳስ ይዞ ሲገባ በነበረው መስፍን ታፈሰ ላይ በሠራው ጥፋት በሁለት ቢጫ ከሜዳ ተወግዷል።
የተጫዋች ቁጥር ብልጫ ያገኙት ኢትዮጵያ ቡናዎች በድጋሚ ወደ ነበራቸው ግለት በመመለስ 63ኛው ደቂቃ ላይ በድጋሚ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ሀዋሳዎች ያገኙትን የቅጣት ምት አዲሱ አቱላ ሲያሻማው ኳሱን በመመለስ ፈጣን በሆነ የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ አማኑኤል ዮሐንስ ለአብዱልከሪም ወርቁ አቃብሎት አብዱልከሪምም በፍጥነት ለመስፍን ታፈሰ ሲያመቻችለት በቀኝ መስመር ከሳጥኑ ጠርዝ የደረሰው መስፍንም የግብ ጠባቂውን መውጣት ተጠቅሞ መሬት ለመሬት በመምታት ግብ አድርጎታል።
በቀሪ ደቂቃዎችም ሁለቱም ቡድኖች ዕረፍት የለሽ በሆነ የማጥቃት እንቅስቃሴ ለተመልካች ማራኪ ፉክክር ሲያደርጉ በቡናማዎቹ በኩል 88ኛው ደቂቃ ላይ በፍቃዱ ዓለማየሁ በግራ መስመር ከተገኘ የማዕዘን ምት ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ጫላ ተሺታ በግንባር ገጭቶ ያደረገውን ሙከራ የግቡ አግዳሚ ሲመልስበት በሴኮንዶች ልዩነት ደግሞ የሀዋሳው ዓሊ ሱሌይማን ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝቶ በደካማ አጨራረስ ግብ ጠባቂው በረከት አማረ ይዞበት አባክኖታል። በጭማሪ ደቂቃዎችም ቡናማዎቹ ተጨማሪ ወርቃማ ዕድል አግኝተው አንተነህ ተፈራ በግሩም ክህሎት ተከላካይ አታልሎ በማለፍ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ቻርለስ ሉክዋጎ ሲመልስበት ያንኑ ኳስ ያገኘው ተቀይሮ የገባው አማኑኤል አድማሱም ሳይጠቀምበት ቀርቷል።
የዳኛው ፊሽካ ሲጠበቅም በተፈጠረ ሰጣ ገባ ከኃይቆቹ ኢዮብ ዓለማየሁ ከቡናማዎቹ ወልደአማኑኤል ጌቱ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግደዋል። ጨዋታውም በኢትዮጵያ ቡና 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።